1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምክር ቤታዊ ምርጫ በሌሶቶ

ቅዳሜ፣ የካቲት 21 2007

በደቡባዊ አፍሪቃ በምትገኘው ንዑሷ ሀገር ሌሶቶ ወይም በሌላ አጠራሯ ባሶቶ ውስጥ በዛሬው ዕለት ምክር ቤታዊ ምርጫ ተካሄደ። ከታቀደለት ጊዜ አስቀድሞ የተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ቀደም ሲል የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገባትን ሀገር ያረጋጋል ተብሎ ታስቧል።

https://p.dw.com/p/1EizX
Wahlen in Lesotho Afrika
ምስል DW/Poppendieck

በሌሶቶ ባለፈው ነሀሴ፣ 2014 ዓም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተደረገ እና የሀገሪቱ ጦር የጠቅላይ ሚንስትር ቶማስ ታባኔ መኖሪያ ቤት ከከበበ እና ታባኔ ላጭር ጊዜ በደቡብ አፍሪቃ ተገን እንዲጠይቁ ካስገደደ በኋላ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ስርዓት አልባነት ለማረጋጋት ሲባል ነው ምርጫው ሁለት ዓመታት አስቀድሞ እንዲደረግ የተወሰነው።ባለፈው ነሀሴ መፈንቅለ መንግሥቱ በከሸፈበት ጊዜ በሌሶቶ ጦር ኃይል እና በፖሊስ መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ አንድ የፕሬዚደንቱ ጠባቂ ወታደር ተገድሎዋል።

Putsch-Versuch in Lesotho 30.08.2014
መፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራምስል Getty Images/Afp/Mujahid Safodien

ለጥምሩ መንግሥት መፍረስ እና ምርጫውም አስቀድሞ እንዲደረግ ምክንያት የሆነው በጥምሩ መንግሥት የተጠቃለሉት ሶስት ፓርቲዎች መሪዎች፣ ማለትም፣ የጠቅላላ የባሶቶ ኮንቬንሽን መሪ ጠቅላይ ሚንስትር ቶማስ ታባኔ፣ የሌሶቶ ዴሞክራቲክ ኮንግረስ መሪ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ሞቴትጆዋ ሜትሲንግ እና የባሶቶ ብሔራዊ ፓርቲ መሪ ፣ በስፖርት ሚንስትር ቴሴሌ ማሴሪባን መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ነበር።

Thomas Thabane 16.08.2014
የቀድሞው ጠ/ሚንስትር ቶማስ ታባኔምስል Imago/Xinhua

የሌሶቶ ጥምር መንግሥት ከፈረሰ በኋላ ነበር የደቡባዊ አፍሪቃ መንግሥታት የልማት ትብብር ድርጅት፣ በምሕፃሩ ሳዴክ፣ በሀገሪቱ ፖለቲካዊው መረጋጋት ይመለስ ዘንድ ምርጫውን እንደ ጊዚያዊ መፍትሔ ያቀረበው። ስለዚህ ምርጫው የሀገሪቱን መንግሥት መልሶ ለማቋቋም የታሰበ ነው። በደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም ተንታኝ ዲምፎ ሞታሳማይ ግን ምርጫው በሌሶቶ ለተፈጠረው ውዝግብ መፍትሔ ይሆናል ብለው አያስቡም።

« ያሁኑ ምርጫ ለሌሶቶ ቀውስ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም። ምናልባት የዴሞክራቲክ ኮንግረስ ፓርቲበምርጫው ከፍተኛ የመራጭ ድምፅ ያገኝ ይሆናል፣ ግን የብዙኃኑን ድምፅ አያገኝም። እና እንዳለፈው ምርጫ ፓርቲዎቹ ህብረት መፍጠር እና ሌላ ጥምር መንግሥት ማቋቋም ይኖርባቸዋል። »

28.08.2014 DW Online Karusell Lesotho Maseru eng

በደቡብ አፍሪቃ የተከበበችው የሁለት ሚልዮን ሕዝብ የሚኖርባት ሌሶቶ በመጨረሻ ምርጫ ያካሄደችው እአአ በ2012 ዓም ነበር። ያኔ የስልጣኑ ሽግግር በሰላማዊ ሁኔታ ተካሂዶ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ጥምር መንግሥት የተመሠረተበት ድርጊት በተራራማዋ ሀገር ውስጥ ዘላቂ መረጋጋት ያስገኛል የሚል ብሩሕ ተሰፋ ፈንጥቆ ነበር። ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ሞቴትጆዋ ሜትሲንግ እአአ ሰኔ፣ 2014 ዓም በጠቅላይ ሚንስትሩ ቶማስ ታባኔ ላይ በምክር ቤቱ ውስጥ የእማኝነት ድምፅ እንዲሚያካሂዱ ባስታወቁበት እና ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ምክር ቤቱን በበተኑበት ጊዜ ነበር ጥምሩ መንግሥት ችግር ያጋጠመው። ጠቅላይ ሚንስትሩ ምክትላቸው ከጦር ኃይሉ ጋር በመተባበር ከሥልጣን ሊያስወግዱዋቸው ሞክረዋል በሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል፣ ሜትሲንግ ግን ወቀሳውን መሠረተ ቢስ ሲሉ አጣጥለውታል።

Mothejoa Metsing Lesotho Congress for Democracy 2012
የቀድሞው ም/ጠቅላይ ሚንስትር ሞቴትጆዋ ሜትሲንግምስል Getty Images/AFP/Alexander Joe

በመዲናይቱ ማዜሩ የሚገኘው «ትራንስፎርሜሽን ሪሶርስ ሴንተር » የተባለው ለሰብዓዊ መብት የሚሟገተው መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት የቀድሞ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆሉ ንያን ምርጫው ለአሳሳቢ ፀጥታ ጉዳዮች መፍትሔ ማስገኘቱን እና ቀውሱን ማብቃቱን ይጠራጠሩታል።

« የዚህ ምርጫ ዋና ዓላማ በሀገሪቱ መንግሥት በማቋቋሙ ሂደት ላይ የተደቀነውን ችግር ማስወገድ ይመስለኛል። ምክንያቱም 2014 ዓም ከገባ ጀምሮ ተጣማሪዎቹ ፓርቲዎች በአንድም ጉዳይ ላይ ማለት ይቻላል መስማማት ባለመቻላቸው ጥምሩ መንግሥት አዳጋች ጊዜ ነበር ያሳለፈው። »

የሌሶቶ ፖለቲካ ቀውስ እንዲያበቃ እና በደቡብ አፍሪቃ ላጭር ጊዜ የሸሹት ጠቅላይ ሚንስትሩም ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ከፍተኛ የሽምግልና ጥረት በማድረግ የሀገሪቱ ተቀናቃኝ ወገኖችን ባለፈው ጥቅምት ወር ማስማማት የቻሉት የደቡብ አፍሪቃ ምክትል ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ እንደነበሩ ሆሉ ንያን ያስታውሳሉ። ከዚያ በዚህ በተያዘው የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ የሳዴክ አባል ሀገራት መሪዎች በሌሶቶ ጉዳይ ላይ የመከሩበትን ጉባዔ ባስተናገዱበት ጊዜ ሌሶቶ በዛሬው ዕለት ምርጫ እንድታካሂድ እና ራማፎዛም የምርጫውን ሂደት እንዲከተታተሉ መወሰኑን ንያን ገልጸዋል።

« በዚሁ የምርጫ ጉዳይ ላይ የተገኙት ዓበይት ውሳኔዎች ሁሉ የሌሶቶን ውዝግብ በማብቃቱ ጥረት ላይ ሚና በተጫወቱት በደቡብ አፍሪቃ ምክትል ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ ነበሩ።

ታዛቢ ቡድኖች የተከታተሉት ብሔራዊው ምክር ቤታዊ ምርጫ ሳዴክ ባሠማራቸው ካካባቢው ሀገራት የተውጣጡ 400 ፖሊሶች በጠንካራ የፖሊስ ጥበቃ ተካሂዶዋል። የሌሶቶ መከላከያ ኃይል ሚና ግልጽ ባለመሆኑ በጦር ሠፈሩ እንዲቆይ መታዘዙን ሆሉ ንያን አመልክተዋል።

« ጦር ኃይሉ አሁንም በሀገሪቱ መረጋጋት ላይ ስጋት እንደደቀነ ይገኛል። እና የደቡባዊ አፍሪቃ ሀገራት የፖሊስ ድጋፍ በመስጠቱ እና የጦር ኃይሉ በሠፈሩ እንዲቆይ በማዘዙ ሁኔታዎች እንደሚረጋጉ እና ጦሩም ትዕዛዙን እንደሚያከብር ተስፋ እናደርጋለን። »

ሌሶቶ ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ እአአ በ1996 ዓም ከተላቀቀች ወዲህ በርካታ ጊዜ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባት ሲሆን፣ ከምርጫው በኋላ ሊነሳ የሚችል ሁከት በዚህ ዓመት በአምስት ከመቶ ሊያድግ ይችላል የሚባለውን የሀገሪቱን ኤኮኖሚ እንዳይጎዳ አስግቷል።

አርያም ተክሌ/ዩኒስ ዋንጂሩ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ