1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርጫ በናሚቢያ

ሐሙስ፣ ኅዳር 18 2007

ናሚቢያን ላለፉት 24 ዓመታት የመራት የደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ ሕዝባዊ ድርጅት በእንግሊዘኛ ምኅጻሩ SWAPO በዘንድሮው የናሚቢያ የምክር ቤት እና የፕሬዚዳንት ምርጫ የማሸነፍ ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ተገምቷል። ሆኖም በአንዳንድ የፓርቲው አባላት ዘንድ ይኽ መነቃቃት ደብዛዛ መሆኑ ተጠቅሷል።

https://p.dw.com/p/1DuCt
ምስል picture-alliance/AP Photo/Themba Hadebe
የምክር ቤት እና የፕሬዚዳንት ምርጫ ዓርብ ኅዳር 19 ቀን፣ 2007 ዓም በመላ ናሚቢያ ይከናወናል። ናሚቢያ በምርጫ ታሪኳ ከኹለት ዐሥርት ዓመት በላይ አመራር ላይ የቆየው አንድ ፓርቲ ቢሆንም፥ ሀገሪቱ እጅግ ዘመናዊ የምርጫ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ትታወቃለች። በዓርቡ ምርጫ ብዙም አዲስ ነገር እንደማይጠበቅ ከወዲሁ ተነግሯል። የደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ ሕዝባዊ ድርጅት በእንግሊዘኛ ምኅጻሩ SWAPO በሀገር አቀፉ ምርጫ አሸናፊ ሆኖ እንደሚወጣ ግምት ተሰጥቶታል። የተቃዋሚዎች ጠንክሮ አለመውጣት እንደ አንድ ምክንያት እንደሚጠቀስ በናሚቢያ ዩኒቨርሲቲ የማሕበረሰብ ጥናት ክፍል ምሁሩ ዶር አርማስ ሺካንጎ ይገልጣሉ።
«በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉን፤ ግን አብዛኞቹ በአሁኑ ወቅት ስዋፖን ለማሸነፍ ጠንከር ብለው ራሳቸውን ማቅረብ አልተቻላቸውም።»
ስዋፖ ናሚቢያን ለ24 ዓመታት ሲመራ ቆይቷል። ሀገሪቱ እጎአ በ1990 ከቅኝ አገዛዝ ተላቃ ነፃነቷን እንድትቀዳጅ የያኔው ነፃ አውጪ ንቅናቄ ግንባር ሚና ተጫውቷል። ለእዚያም ነው የፖለቲካ ድርጅቱ መምረጥ ከሚችለው 1, 2 ሚሊዮን ናሚቢያዊ መካከል ዛሬም ድረስ በርካታ ደጋፊዎችን ሊያፈራ የቻለው። የስዋፖ፥ የወጣቶች ሊግ የማስታወቂያ ክፍል ጸሐፊ ጆብ ሺፑሉሎ አሙፓንዳ የድርጅታቸው ከፍተኛ ድጋፍ ምንጩ ይኸው የነፃነት ዘመን ንቅናቄ እና አመራር ውጤት እንደሆነ ይገልጣሉ።
ምርጫ በናሚቢያ
ምርጫ በናሚቢያምስል picture-alliance/dpa/Gao Lei
«እነዚህ ሰዎች አሁንም ድረስ ድምጽ የሚሰጡት ነፃነት እንዴት እንደተቀዳጁ በማሰብ ታማኝነታቸውን ለማሳየት ነው። በናሚቢያ እጅግ ጠንካራ ገዢ ፓርቲ እና እጅግ ደካማ ተቃዋሚ ነው ያለን። ይኼ ዲሞክራሲያዊ መግባባትን እና ዲሞክራሲን ሲበዛ አስቸጋሪ አድርጎታል።»
የአፍሪቃ ወቅታዊ የፖለቲካ ይዞታዎችን በሚመዝነው አፍሮባሮሜትር በተባለው ድርጅት በቅርቡ የተከናወነው የሕዝብ መጠይቅ የሚያሳየውም ይኽንኑ ነው፥ አብዛኞቹ የስዋፖ መራጮች ድምጽ የሚሰጡት የፖለቲካ ድርጅቱን በቅጡ አውቀውት ሳይሆን፥ ለስዋፖ ታማኝ በመሆናቸው ብቻ ነው። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሥራ አጡ ቁጥር 27 ከመቶ ደርሷል፤ ድህነቱም የበርካታ ናሚቢያኖች መማረሪያ ከሆነ ሰነባብቷል። እንዲያም ሆኖ የናሚቢያ መንግሥት ሀገሪቱ ተረጋግታ እንድትቆይ ማድረጉ ተሳክቶለታል። በደቡብ አፍሪቃ የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ሔኒን ሜልበር።
«የስዋፖ የምርጫ መርሐ-ግብር እንዲህ ይላል፦ እኛ ስዋፖዎች መንገዶችን ዘርግተናል፣ ትምህርት ቤቶችን ገንብተናል፣ ሐኪም ቤቶችን አቋቁመናል። በእዚህም መሠረት ማንኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ እንዲህ ስኬታማ ከሆነ ፓርቲ ጋር ለመፎካከር እጅግ ሲበዛ ይከብደዋል። ስለእዚህ ለሕዝቡ ስዋፖ ማለት ናሚቢያ፥ ናሚቢያ ደግሞ ስዋፖ ማለት ነው።»
ከናሚቢያ ከተሞች አንዷ ዊንድሆክ
ከናሚቢያ ከተሞች አንዷ ዊንድሆክምስል picture-alliance/dpa/T. Schulze
ለናሚቢያውያን ስዋፖ እና ናሚቢያ የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽ እንደማለት ነው። አብላጫው የናሚቢያ ነዋሪ የእዚህ ዓይነት እምነት እንዳለው ቢጠቀስም፤ በሀገሪቱ ሥራ አጥነት እና የሸቀጦች ዋጋ ከምን ጊዜውም በላይ መናሩ ይነገርለታል። ይኽ አለመረጋጋት ሊፈጥር እንደሚችልም ምሁራኑ ያስጠነቅቃሉ። የስዋፖ የወጣቶች ሊግ ቃል አቀባይ አሙፓንዳ በበኩሉ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ፍላጎቱ ጥልቅ ነው። ለእዚያም መከራከሪያውን ሲያቀርብ፦ ከግማሽ በላይ የናሚቢያ ነዋሪ ወጣቶች ነን፤ አመራራችን ጃጅቷል። ስለወጣቶች ችግር ምንም በማይገባቸው ሰዎች እየተመራን ነው ብሏል።
ናሚቢያ 1200 ቋሚ፣ እንዲሁም 2700 ተንቀሳቃሽ የምርጫ ጣቢያዎች አሏት። ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ የድምጽ መቁጠሪያ መሣሪያ በመጠቀምም ናሚቢያ በአፍሪቃ ቀዳሚ ሆናለች። ሆኖም ከህንድ የገቡት የኤሌክትሮኒክ ድምጽ መቁጠሪያ መሣሪያዎች እንከን አልታጣባቸውም፤ የድምጽ መፋለስ ሲፈጠር እንደደረሰኝ የሚያገለግል ወረቀት ማተም አይችሉም። ስለሆነም አንዳንድ ተቃዋሚዎች ይኽ ሁናቴ የድምጽ መጭበርበር ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ከወዲሁ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ