1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማዕከላዊ አፍሪቃና የአዉሮጳ ሕብረት ርዳታ

ረቡዕ፣ ግንቦት 19 2007

የአዉሮጳ ሕብረትን ጨምሮ «ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ» የሚባለዉ የሐብታሞቹ መንግሥታት ሥብብስብ ችግሩ ሕይወት ከሚያጠፋበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ እርዳታ ለመስጠት ያቅማማበት ምክንያት በርግጥ ማስተዛዘቡ አልቀረም።በነ ፕሬዝደንት ሳምባ-ፓንዛ አቅም ግን አይጠየቅቅም።

https://p.dw.com/p/1FXMd
ምስል Getty Images/AFP/E. Dunand

[No title]

የአዉሮጳ ሕብረት ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሕዝብ ሠብአዊ ርዳታና በጦርነት የወደመችዉን ሐገር መልሶ ለመገንባት ሰባ-ሁለት ሚሊዮን ዮሮ ተጨማሪ ርዳታ ለመስጠት ቃል ገባ።ትናንት ብራስልስ-ቤልጂግ በተደረገዉ የለጋሽ ሐገራት ጉባኤ ላይ እንደተገለጠዉ ሕብረቱ የሚሰጠዉ ተጨማሪ ርዳታ በጦርነቱ ለተፈናቀለ፤ ለተሰደደዉና ለረሐብ ለተጋለጠዉ ሕዝብ ምግብና መድሐኒት ለማዳረስና መልሶ ለማቋቋም የሚዉል ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ በሚሊዮን የሚቆጠር የደኸይቱ ሐገር ሕዝብ ለከፋ ችግር ተጋልጧል።

ጦርነት፤ ሥርዓተ አልበኝነትና ዘረፋ ላመሰቃቀላት አፍሪቃዊት ሐገር ጊዚያዊ ፕሬዝደንት ወይዘሮ ካትሪን ሳምባ-ፓንዛ ለትናንቱ ጉባኤተኞች እንደነገሩት የአዉሮጳ ሕብረት የገባዉ የርዳታ ቃል ለደሐይቱ ሐገር ጎስቋላ ሕዝብ ተስፋ ነዉ።

«ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሕዝብ ተስፋ መስጠት ጀምረናል።(ተስፋዉ እንዲፀና) ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ድጋፍ ጋር ምኞታችንን እና ቁርጠኝነታንን ማሳየት አለብን።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሕዝብ ለከፋ ችግር መጋለጡን ካስታወቀ ቆይቷል። በቅርቡ ባወጣዉ መግለጫዉ ደግሞ «የተረሳዉ እና የዘመናችን ታላቅ-ሠብአዊ ድቀት» እስከ ማለት ደርሶ ነበር።የዓለም ምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ ኮርኔሊያ ፐትሰ እንደሚሉት የማዕከላዊ አፍሪቃ ሕዝብ የመፅዋቾችን እጅን ማየት የጀመረዉ ሐቻምና ይኽኔ-የዓለም መገናኛ ዘዴዎች ርዕስ የነበረዉ ጦርነት ከመጋሙ በፊት ነበር።

Zentralafrikanische Republik Seleka Rebellen
ምስል ISSOUF SANOGO/AFP/Getty Images

«ገና ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከ1,5 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ተርቦ ነበር።አሁን ደግሞ ችግሩ እጅግ ብሷል።ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሐገሪቱ የግብርና ምርት በግማሽ ቀንሷል።ከጦርነቱ በፊት ለእርሻና ለእሕል ምርት ከሚያገለግሉ እንስሶች መሐል የተረፉት ሩብ ያሕል ብቻ ናቸዉ።ሕዝቡ በእዉነቱ በጣም ነዉ የተቸገረዉ።»

የአዉሮጳ ሕብረትን ጨምሮ «ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ» የሚባለዉ የሐብታሞቹ መንግሥታት ሥብብስብ ችግሩ ሕይወት ከሚያጠፋበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ እርዳታ ለመስጠት ያቅማማበት ምክንያት በርግጥ ማስተዛዘቡ አልቀረም።በነ ፕሬዝደንት ሳምባ-ፓንዛ አቅም ግን አይጠየቅቅም።

ፕሬዝደንቷ ለሕዝባቸዉ «እንስጥ» ያሉት ተስፋ ከርዕሰ-ከተማ ከባንጊ ዉጪ ለሠፈረው ተፈናቃይ ቀርቶ እዚያዉ ርዕሰ-ከተማይቱ ለሚገኙት ለአቦኒ ፊሳቶ እና ለብጤዎቻቸዉ መድረሱ እንኳ አጠራጣሪ ነዉ።የሐምሳ-አምስት ዓመቷ እናት ጦርነቱ እንደተጀመረ የቤተሰቦቻቸዉ አባላት በሙሉ ተገደሉ።ቤት ንብረታቸዉም ጠፋ። የደረሰላቸዉ አልነበረም።የቤተ-ሰቦቻቸዉን እስከሬ፤ የመኖሪያቸዉን ክሳይ ጥለዉ እንደ ብዙ ብጤዎቻቸዉ ባንጊ መስጊድ ገቡ።ርዳታ ይጠብቁ ያዙ።ዘንድሮ ሁለተኛ ዓመታቸዉ።

«መጀመሪያ ላይ የሚሰጠን ርዳታ በቂ ነበር።ጨዉ፤ቦለቄ፤ ሩዝ፤ አንዳዴ ደግሞ በቆሎ ይሰጠን ነበር።ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን በጣም እየቀነሰ ነዉ።በጭራሽ አልበቃንም።»

ለአንድ ግብረ-ሠናይ ድርጅት የሚሠሩት ዓሊ መሐመት የአሮጊቷን ብሶት ያረጋግጣሉ።

«ሁለት ሊትር ዘይት ያገኙ የነበሩት ተረጂዎች አሁን የሚያገኙት አንድ ነዉ።አምስት ሳሙና ያገኙት የነበሩት ደግሞ ወደ ሰዎስት ዝቅ ብሎባቸዋል።»

Zentralafrika Milizkämpfer Soldat 23.01.2014
ምስል Issouf Sanogo/AFP/Getty Images

ዓሊ እንደሚሉት ለርዳታዉ መቀነስ ምክንያቱ ሰወስት ነዉ።ድርጅታቸዉ የሚያከፋፍለዉ ርዳታ ከምንጩ መቀነሱ-አንድ፤ የተረጂዉ ቁጥር መጨመሩ-ሁለት፤ ከሚደርስዉም ርዳታ መሐል የተወሰነዉ በወርሮበሎች መዘረፉ-ሰወስት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ርዳታዉ ዘራፊዎች እጅ እንዳይገባ ለመከላከልና የማጓጓዢያ ወጪን ለመቀነስ በሚል ለተረጂዎቹ የሸቀጥ መግዢያ ወረቀት (ኩፖን) ማደል ጀምሯል።ይሁንና ተረጂዉ ሕዝብ የሚያስፈልገዉን ምግብና ቁሳቁስ በሚያስፈልግበት ወቅት እንዳያገኝ ወይም ወረቀቷን ለምግብ ከማዋል ይልቅ ሌላ ጉዳይ የሚያዉለዉ ገዘብ ፍለጋ ወረቀቷን በርካሽ እየሸጠ ይራባል የሚሉ ወገኖች አዲሱን አሠራር እየተቹት ነዉ።

4,7 ሚሊዮን ከሚገመተዉ ሕዝብ ግማሽ ያሕሉ አንድም ስደተኛ አለያም ተፈናቃይ ነዉ።ርዳታ ጠባቂ። የአዉሮጳ ሕብረትም ሆነ ሌሎች ለጋሾች በትናንቱ ጉባኤያቸዉ ተጨማሪ ርዳታ ለመስጠት ቃል ይግቡ እንጂ ርዳታዉ ለተገቢዉ ተረጂ እንዲደረስ የቀየሱት አዲስ ሥልት የለም።ፕሬዝደንት ሳምባ-ፓንዛ ግን «ተስፋ» ያሉት ተስፋ ከሆነ ተቀናቃኝ ሐይላት አዲስ ምርጫ ለማድረግ መስማማታቸዉ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ