1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማብቂያ ያጣው የቦኮ ሀራም ሽብር እና ናይጄሪያ

ሰኞ፣ ነሐሴ 19 2006

የኤቦላ ወረርሽኝ የመነጋገሪያ ርዕስ በሆነባት ናይጄሪያ ፤ ከበሽታው ሌላ ህዝቧን ያሳሰበው ሌላም ነገር አለ። ይህም በሀገሪቱ ስር የሰደደው አማፂው እስላማዊ ቡድን ቦኮ ሀራም ነው። አማፂያኑ በተቆጣጠሩት ሰሜን ናይጄሪያ እስላማዊ ካሊፋት መመሥረታቸውን በገለፁበት በአሁኑ ወቅት በሌላ በኩል ታግተው የተወሰዱትን ሴት ተማሪዎች ለማስመለስ ትግል ተይዟል።

https://p.dw.com/p/1D0x5
Wohnhaus in den Gwoza-Bergen
ምስል privat

ናይጄሪያ ውስጥ በቦኮ ሀራም ታግተው ለተወሰዱት ልጃገረዶች ተማሪዎች የሚሟገቱት ዘመቻቸውን አላቋረጡም። ተማሪዎቹ በቦኮ ሀራም ቡድን ታግተው ከተወሰዱ ዛሬ 133ኛው ቀን ተቆጠረ። የቺቦክ ነዋሪ ከሆኑት ተማሪዎች በርግጥ የተወሰኑት ለማምለጥ ቢችሉም 220 የሚደርሱት አሁንም በቦኮ ሀራም እጅ እንደወደቁ እና ከፈላጊዎቻቸው ዓይን እንደተሰወሩ ናቸው። ባለፈው ሳምንት እንዲሁ በርካታ ወንድ ልጆች ታፍሰው ተወስደዋል። ቡድኑ ምናልባትም ለውትድርና ሊያሰለጥናቸው እንደሚችል ተሰግቷል። ትናንት አንድ የናይጄሪያ የፖሊስ ቃል አቀባይ እንደገለፀው ደግሞ ሰሞኑን ሰሜን ምስራቅ ቦርኖ ግዛት ውስጥ በሁለት የጦር መለማመጃ ካምፖች ላይ ከተከፈተ ተኩስ በኋላ እንዲሁ 35 ፖሊሶች የደረሱበት አልታወቀም። ለዚህም ተጠርጣሪው ቦኮ ሀራም ነው። የቦኮ ሀራም ተጠሪ በቦርኖ ግዛት የሚገኘው «ግዋዛ» ከእንግዲህ ከናይጄሪያ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው እና በቡድኑ ቁጥጥር ስር እንደሆነ ገልጿል። ከሰብዓዊ መብት ተማጓቹ ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ማክሚድ ካማራ እንደሚሉት ግዋዛ ብቸኛዋ ከተማ አይደለችም።« በተለይ በሰሜን ናይጄሪያ ከተሞች እና መንደሮች ለሚኖሩ በርካታ ናይጄሪያውያን ያለው ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ቀጥሏል። በተለይ በቦርኖ ከተማ ለሚገኙት። በርካታ ሰዎች በቦኮ ሀራም ተፋላሚዎች ተገድለዋል።እንዲሁም በርካቶች በናይጄሪያ የፀጥታ አስከባሪ ኃይል ተገድለዋል።»

በትክክል ይህ ነው ህብረተሰቡን ጥርጣሬ ውስጥ የጣለው። የሰዉ ፍርሃት ከቦኮ ሀራም ብቻ ሳይሆን ከራሱ ከሀገሪቱ ጦር እና በምህፃሩ JTF በመባል ከሚጠራው ልዩ ሀይል ነው። አቡጃ ውስጥ ከልማት እና ዲሞክራሲ ማዕከል በመባል የሚጠራው ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ኢዳያት ሀሳን ለምን የሚለውን ጥያቄ ያብራራሉ።« የናይጄሪያ ሰላም አስከባሪ ኃይላት የከሸፉት የህዝቡን ልብ እና አመኔታ ያጡ ጊዜ ነው። ይህ እስካልተስተካከለ ድረስ ይህ የማያስተማምን ጊዜ ሊያበቃ አይችልም። መፍትሄው የወታደራዊ ርምጃ ብቻ አይደለም።»

Nordkamerun Grenzregion zu Nigeria Soldaten Anti Terror
ምስል AFP/Getty Images

በርግጥ በርካታ ወታደሮች ጦራቸውን እንደ መፍትሄ መመልከት ትተዋል። በየጊዜው እንደሚወጡት ዘገባዎች ከሆነ ወታደሮቹ ጦሩን ጥለው እየሸሹ ይገኛሉ። ትልቁ ወቀሳ ወታደሮቹ እንዲዋጉ በአግባቡ አልታጠቁም የሚል ነው። አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባደረገው ጥናትም ይህንን ወቀሳ የሚያንፀባርቅ ድርጊት እንደታዘበ ካማራ ለዶይቸ ቬለ አረጋግጠዋል።

በስፍራው ሆና የምትዘግበው ጋዜጠኛ ካትሪን እንደታዘበችው በመዲና አቡጃ በአሁኑ ሰዓት የይምረጡኝ ዘመቻው ነው በየመንገዱ የሚነበበው እና የሚሰማው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞ አባል የሆኑት እና በአሁኑ ወቅት የተቃዋሚው APC ፓርቲ አባል ዲኖ ሜላዬ ገዢውን የፕሬዚዳንት ጉድላክ መንግሥት ይተቻሉ።« « መንግሥት እና ፕሬዚዳንቱ በበቂ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ አይደለም ። የፀጥታ አስከባሪ ድርጅቶች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እየረወጡ አይደለም። ፕሬዚዳንቱ ልጃገረዶቹ ተመልሰው እንዲመጡ ከመታገል ይልቅ በሚመጣው ዓመት በሚደረገው ምርጫ ተጠምደው ይገኛሉ ለማለት እደፍራለሁ፤ ።

Nigerias Terror geht weiter
ምስል DW/K. Gänsler

ካትሪን ጌንዝለር / ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ