1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን»

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 2 2007

«መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን» በአጼ ዘረያቆብ ዘመነ መንግሥት ከ 1510 እስከ 1520 ባለዉ ጊዜ ከአረብኛ ወደ ግዕዝ ደብረሊባኖስ ዉስጥ እንደተረጎመ ስለ መጽሐፈ ፈላስፋ የሚያጠኑት ምሁራን ይገልፃሉ።

https://p.dw.com/p/1E2cb
Die abessinischen Handschriften
መጽሐፈ ፈላስፋምስል Zerihun Mulatu/Martin-Luther-Universität Halle-Wittenberg

ስለ «መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን » መጽሐፍ ይዘት ከጀርመናዉያን ምሑራን ጋር ለማጥናት ለሶስት ወራት በጀርመን ሃለ ከተማ በሚገኘዉ ማርቲን ሉተር ዩንቨርስቲ ቆይታ ያደረጉት ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ፤ እንደሚሉት፤ ይህ የብራና መጽሐፍ፤ የፍልስፍና መጽሐፍ ሲሆን፤ ከዓረብኛ ወደ ግዕዝ የተተረጎመና ከግብፅ ኮፕቲክ ቤተ-ክርስትያን ለኢትዮጵያ የተሰጠ መሆኑን ገልፀዉልናል። ትርጉሙ የተሰራዉም በደብረሊባኖስ ዉስጥ መሆኑን ተናግረዋል።

Zerihun Mulatu Dr. Ute Pietruschka Martin-Luther-Universität Halle-Wittenberg Die abessinischen Handschriften
ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱና ጀርመናዊትዋ ዶክተር ኡተ ፔትሩሽካ በጀርመን ማርቲን ሉተር ዩንቨርስቲ በፍልስፍና ተቋም ዉስጥምስል Zerihun Mulatu/Martin-Luther-Universität Halle-Wittenberg

የዶክትሪት ትምህርታቸዉን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በመከታተል ላይ የሚገኙት ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ጥናታቸዉን መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን ላይ ማድረጋቸዉንና፤ የተሟላ ጥናት ለማግኘት ወደ ጀርመን እንደመጡም ነግረዉናል። ረዘም ላለ ግዜ የብራና ጽሑፎች ላይ ጥናት በማድረጋቸዉ የሚታወቁት እና በተለይ በመጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን ላይ ምርምራቸዉን ያደረጉት ጀርመናዊትዋ ዶክተር ኡተ ፔትሩሽካ አስደሳች የምርምር ስራ ሲሉ አጫዉተዉናል። በዚህ መጽሐፍ ላይ ኢትዮፕያዉ ተመራማሪ በመገኘቱም ተደስተዋል። ለዚሁ ጥናትም ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ ወደ ጀርመን እንዲመጡና ጥናታቸዉን ለሶስት ወራቶች እንዲያደርጉ መንገድ አመቻችተዋል።


«መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን»ን በተመለከተ ረዘም ላለ ጊዜ ምርምር ሥራ ዉስጥ እገኛለሁ። በመካከለኛዉ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር ምን ያህል ግንኙነት እንደነበራት በዚህ መጽሐፍ ምርምር ላይ ማግኘቱና ማየቱ እጅግ በጣም ደስ ያሰኛል። በኢትዮጵያ የሚገኙ የሃይማኖች አባቶችም ይህን መፅሐፍ ደግሞ ደግሞ በመፃፍ አባዝተዉታል። እነዚህ አባቶች በዝያን ዘመን የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ-ክርስትያንን ተከትሎ ከግብፅ የጠበቀ ጋር ግንኙነት ነበራቸዉ። ኢትዮጵያና ግብፅ አሁንም ግንኙነት አላቸዉ። ሌላዉ ከሶርያ እና ሌሎች ሃገራት ጋር ኢትዮጵያ የነበራትን ግንኙነት ግልፅ አድርጎ ያሳያል። ይህ መጽሐፍ ኢትዮጵያ የነበራትን ግንኙነት የአካባቢዉን ልማድ ሁሉ ግልፅ አድርጎ ያሳያል»
ጀርመናዉኑ ይህን በግዕዝ የተፃፈ ፍልስፍናን እንዴት ይረዱት ይሆን? ጀርመናዊትዋ ዶክተር ኡተ ፔትሩሽካ ይዘቱ ለአዉሮጳዉያን ባዕድ አይደለም ሲሉ ነዉ የገለፁልን።

Die abessinischen Handschriften
መጽሐፈ ፈላስፋምስል Zerihun Mulatu/Martin-Luther-Universität Halle-Wittenberg


«ይዘቱ እጅግ ባዕድ አይደለም። መ ጽሐፈ ፈላስፋ ይዘቱ ፍልስፍና ነዉ። ከጥንታዊ ፍልስፍና፤ ከግሪክ ፍልስፍና ተወስዶ ነዉ እዚህ መጽሐፍ ዉስጥ የሰፈረዉ። ይህ ጥንታዊ ፍልስፍና ደግሞ ለኛ ለአዉሮጳዉያን ባዕድ አይደለም። ምናልባትም ለኢትዮጵያዉያን ትንሽ ለየት ያለ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ግን ይህን ጥንታዊ ፍልስፍና እጅግ በብዙ ቅጂ በእጅ ጽሑፍ ብራና ላይ ተፅፎ ኢትዮጵያ ዉስጥ መገኘቱ፤ በዘመኑ ይህ መጻሕፍ ምን ያህል ተወዳጅ እንደነበር ያሳያል። »
«መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን» መጽሐፍት ይዘታቸዉ አንድ ሆኖ በተለያየ አገላለፅ ሰላሳ ስድስ ግዜ መጻፋቸዉንና ገሚሱ አዉሮጳ ቤተ-መጽሐፍ ዉስጥ እንደሚገኙ የገለፁልን ሊቀ ጠበብት ዘሪሁን ሙላቱ መጻሕፍቱ በ19ኛዉ ክፍለዘመን መጀመርያ ወደ አዉሮጳ መምጣታቸዉን ገልጸዋል።

Älteste äthiopische Bibelhandschrift
ምስል DW/ A.T.Hahn


ጀርመናዊትዋ ተመራማሪ ዶክተር ኡተ ፒትሮሽካ በበኩላቸዉ ወደ አዉሮጳ በርካታ መጻሕፍት ቢገቡም ብዙ ጥናት ሊደረግባቸዉ የሚገባ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት አሁንም ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዳሉ ተናግረዋል።
«እነዚህ መጻሕፍት ከኢትዮጵያ በተለይ በ19ኛዉ ክፍለ ዘመን ነዉ ምዕራባዉያን ወደ አዉሮጳ ቤተ- መጻህፍት ዉስጥ ያስገቡዋቸዉ። እንድያም ሆኖ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ዉስጥ እጅግ ብዙ ጥንታዊ የፍልስፍና መጻሕፍት ይገኛሉ። ይህን ሁኔታ ጀርመናዉያን ተመራማሪዎችን ጨምሮ በርካታ የዘርፉ ሰዎች አያዉቁም ነበር። አሁን አንድ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ በማግኘታችን ተደስተናል። ጥናቱን ማድረግ ያለበት ግን ኢትዮጵያዉስጥ ባሉት ጽሑፎች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ አዉሮጳ ዉስጥ ያሉትን መጻሕፍትም በማገላበጥ ጥናቱን መቀጠል ይኖርበታል»። ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።


አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ