1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕይወት ያጠፋዉ የባሌ ደን እሳት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 8 2007

የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ተፈጥሮን ለማድነቅ፤ በሌሎች አካባቢ የማይገኙ አዕዋፍና የዱር እንስሳትን ለመመልከትና ተራሮችን የመዉጣት ፍቅር ያላቸዉን ቱሪስቶች በመሳብ ይታወቃል። በበጋ ወራት በተለያዩ አካባቢዎች የእሳት ቃጠሎ እየተነሳ ጉዳት ማድረሱ ይደጋገማል። በንብረትና በተፈጥሮ ሀብት ላይም ቀላል የማይባል ችግር ሲያስከትል ይሰተዋላል።

https://p.dw.com/p/1EsGI
Äthiopien Omo Fluss Tal Landschaft
ምስል JENNY VAUGHAN/AFP/GettyImages

በበጋ ወራት በተለያዩ አካባቢዎች የእሳት ቃጠሎ እየተነሳ ጉዳት ማድረሱ ይደጋገማል። በንብረትና በተፈጥሮ ሀብት ላይም ቀላል የማይባል ችግር ሲያስከትል ይሰተዋላል። ሰሞኑን በኢትዮጵያ የባሌ ተራሮች አካባቢ የተከሰተዉ የእሳት አደጋ ግን ለአካባቢ ተፈጥሮ የምትቆረቆር ሕይወትንም አልማረም። ከሌላ አንፃር እሳቱ ያደረሰዉ የጉዳት መጠን ገና እየተጠና ነዉ ቢባልም ምንም ዋጋ ቢከፈል መልሶ የማይተካ ዉድ የሰዉ ሕይወት ግን ላይመልስ ነጥቋል።

የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ተፈጥሮን ለማድነቅ፤ በሌሎች አካባቢ የማይገኙ አዕዋፍና የዱር እንስሳትን ለመመልከትና ተራሮችን የመዉጣት ፍቅር ያላቸዉን ቱሪስቶች በመሳብ ይታወቃል። ከብዙ በጥቂቱ የምኒልክ ድኩላ፤ ኒያላ፤ የባሌ ጦጣዎችና ሌሎችም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የዱር እንስሳት የባሌ ብሔራዊ ፓርክና አካባቢዉን መኖሪያቸዉ አድርገዉ ይገኛሉ። የብዝሃሕይወት ስብጥር ያበለፀገዉ ይህ አካባቢ ሰሞኑን የእሳት አደጋ እንደገጠመዉ ተሰምቷል። ወደስፍራዉ በመሄድ ሁኔታዉን ተመልክተዉ የተመለሱት የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ዘዉዴ አሁን እሳቱን መቆጣጠር መቻሉን ይገልጻሉ።

Zhara Church Forest, Äthiopien
ምስል Matthew Jellings

ቃጠሎዉ ወደነበረበትአካባቢዉ ደዉለን ያነጋገርናቸዉ የባሌ ብሔራዊ ፓርክ ሠራተኛ መሆናቸዉን የገለፁልን አቶ አስቻለዉ ጋሻዉ፤ በተራራዉ ዙሪያ ለተነሳዉ እሳት ምክንያት ነዉ ተብሎ የሚገመተዉ ሠዉ ሠራሽ መንስኤ ሳይሆን እንዳልቀረ ያመለክታሉ። እንዲያም ሆኖ መንስኤዉን ለማጣራትና እጃቸዉ ሳይኖርበት አልቀረም የተባሉ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ የአካባቢዉ ፖሊስ የማጣራት ሥራ መጀመሩንም ጠቁመዉናል።

በዚህ ስፍራ ከየካቲት 24 ቀን ጀምሮ እንደተነሳ የተሰማዉ እሳት ጉዳቱ በአካባቢ ተፈጥሮዉ ላይ ብቻ ሳይገታ ተፈጥሮን በማድነቅና በመንከባከብ የምትታወቅ የወጣት ባለሙያን ነፍስም ማጥፋቱ የብዙዎች መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል። የማኅበረሰብ ቱሪዝም ባለሙያ ነዉ። ጊዜና ሕይወቱን ተፈጥሮን በማድነቅና የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መኖሩን በቅርብ የሚያዉቁት ይናገሩለታል። በመናገር ብቻ ሳይሆን በተግባርም የአካባቢ ተፈጥሮ ወዳጅነቱን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ባከናወናቸዉ ተግባራት ተከታዮችም አፍርቷል። የ33ዓመቱ ወጣት ብንያም አድማሱ አስታ የተባለዉ ተክል በእሳት እየነደደ እሳቱም ወደሌላ አካባቢ እንዳይስፋፋ ጥረት እያደረጉ ከነበሩ ወገኖች ጋ ሆኖ የሚመለከተዉን ለሚቀርበዉ ሰዉ ደዉሎ እንዲህ አዋይቶ ነበር። ሄኖክ ስዩም አደጋዉ ከመድረሱ ከቀናት በፊት በስልክ አግኝቶታል።

Landschaft in Äthiopien
ምስል picture alliance/imagestate/Impact Photos

በባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ የተነሳዉ የእሳት ቃጠሎ አሁን በቁጥጥር ሥር መዋሉ መልካም ዜና ቢሆንም ለእሳቱ መነሻ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ የሚጠረጠረዉ የከብቶች መኖ የሆነዉን ተክል የማቃጠል ልማድ ሌላ መፍትሄ እንዳለዉ ባለሙያዎች ቢመረምሩት መልካም ይሆናል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ