1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለጀሃዳዊ የበላይነት የ«IS» እና የአልቃይዳ ትግል

ዓርብ፣ ኅዳር 19 2007

በአፍሪቃ እና በእስያ የሚገኙ የአሸባሪ ቡድኖች በተደጋጋሚ እስላማዊ መንግሥት ብሎ ራሱን የሚጠራዉን አሸባሪ መንግሥት ሲቀላቀሉ ተስተዉሎአል። ፅንፈኛዉ ቡድን «እስላማዊ መንግሥት» ከፅንፈኛዉ አልቃይዳ ቡድን ይልቅ የአሸባሪነት ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉ ነዉ የተመለከተዉ።

https://p.dw.com/p/1DwkI
Propagandabild IS-Kämpfer ARCHIV
ምስል picture-alliance/abaca/Yaghobzadeh Rafael

በአሁኑ ወቅት የአሸባሪዉ ቡድን የ«IS » መለያ ሰንደቅ ዓላማ በኢራቅና በሶርያ ላይ ብቻ አይደለም የሚዉለበለበዉ። በሌሎች ሀገሮች የሚገኙ አሸባሪ ቡድኖችም ቢሆኑ እራሱን ካሊፋ ብሎ ለሰየመዉ ለ«ለእስላማዊዉ መንግሥት» መሪ ለአቡባካር አል ባግዳዲ ተዓማኒነታቸዉን እያሳዩ ነዉ። የምሥራቃ ሊቢያ ዴርና ግዛትን የሚቆጣጠሩት ቡድኖች «እስላማዊዉን መንግሥት » መቀላቀላቸዉን በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸዉ ይታወቃል። በግብፅ፤ በየመን፤ በሳዉዲ አረብያ እና አልጀርያ የሚገኙ ጀሃዲስቶችም «አል-ባግዳድ » የተባለ አንድ አዲስ ካሊፋን እንደሚደግፉ በቪዲዮ ይፋ መልክታቸዉ አስታዉቀዋል። በዚህም አልቃይዳ የተሰኘዉ የአሸባሪዎች የትስስር መረብ ከቀን ወደቀን በፅንፈኞች ዓለም የመሪነቱን ቦታ እየጣ መምጣቱም ተመልክቶአል።

Abu Bakr al-Baghdadi
አቡበከር አል ባግዳዲምስል picture-alliance/dpa


«እስላማዊ መንግሥት» ብሎ ራሱን የሚጠራዉ ፅንፈኛ ቡድን በኢራቅ ብቅ ያለዉ እንደ አንድ የአልቃይዳ አሸባሪ ቡድን ቅርንጫፍ ሆኖ ነዉ። ዮርዳኖሳዊዉ «አቡ ሙሳብ አል ዛርካዊ» በኢራቅ የሚገኘዉን ይህን ቡድን ቢመራም አስተዳደሩን አልተቆጣጠረም። ከዝያም ነዉ በተለይ በኢራቅ ሺዒት ላይ ባካሄደዉ እጅግ ጭቃኔ የተሞላበት ርምጃ ፤ ከአልቃይዳ የአሸባሪ ቡድን መረብ ተገንጥሎ የወጣዉ። አልዛርካዊ በጎርጎረሳዊዉ 2006 ዓ,ም መገደሉ ይታወቃል። ከዓመት በኋላ አል ባግዳዲ የኢራቁን አሸባሪ ቡድን በአህፅሮቱ «ISIS » ማለትም እስላማዊ መንግሥት በኢራቅና በሶርያ በሚል በመሪነት ከያዘ እና በሶርያ የሚያደርገዉን ትግል ትቶ ከወጣ በኋላ በሁለቱ ጀሃዳዊ ቡድኖች መካከል ያለዉ ልዩነት ግልፅ እየሆነ መምጣቱ ተዘግቦአል። በሶርያ ሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች ደም አፋሳሽ ጦርነት ማካሄዳቸዉም ተመልክቶአል። እነዚህ ሁለት አሸባሪ ቡድኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረገዉ የጀሃዲስቶች ንቅናቄ ላይ መሪነትን ለመያዝ ይታገላሉ።
በለንደኑ ኪንግ ኮሌጅ በአሸባሪነት ጉዳይ ላይ ጥናት ያካሄዱት ካትሪን ብራዉን፤ የአልቃይዳንና «IS» ፅንፈኛ ቡድኖች እንዲ አነጻጽረዉታል፤

« እንደኔ ሃሳብ ሁለቱም ቡድኖች አስተባባሪ ቡድኖች አይነት ናቸዉ ብል ትክክል ይመስለኛል። በአካባቢዉች ለሚገኙ ቡድኖች ወደ ዓለማቀፍ ፍልስፋና ተግባር ላይ እንዲሰባጠሩ ቀላል መንገድን ይፈጥሩላቸዋል። በአልቃይዳ እና በIS መካከል ያለዉ ልዩነት፤ አልቃይዳ አንድ መንግሥት አቋቁማለሁ ፤ አስተዳድራለሁ ሲል ራሱ አለመግለፁ ሲሆን፤ « እስላማዊዉ መንግሥት » ግን በአንፃሩ ማስተዳደር እንችላለን ፤ ይህንንም እናንተ ላይ እናደርጋለን እናንተም አብራችሁ ናችሁ ብሎ መነሳቱ ነዉ። »
እንደ ካትሪን ብራዉን ገለፃ ሁለቱ አሸባሪ ቡድኖች የሚለዩበት ሌላ ጉዳይ ደግሞ አልቃይዳ በሰሜን አፍሪቃና በመካከለኛዉ ምስራቅ ሀገራት ላይ ሳይሆን አብዛኛ ላይ ትግሉንና ጥቃቱን የሚያደርሰዉ ፤ርቀዉ በሚገኙት ጠላቶቹ ማለትም ዩኤስ አሜሪካና ተባባሪዎችዋ ላይ ነዉ። አሸባሪዉ ቡድን «እስላማዊ መንግሥት» በአንፃሩ ጥቃቱን እያደረሰ ያለዉ በአካባቢዉ በሚገኙ መንግሥታ ላይ ሲሆን እስከ አሁን በአዉሮጳ እና ዩኤስ አሜሪካ ላይ ጥቃትን አላደረሰም።

አልቃይዳ በምዕራቡ ዓለም የሚያደርሰዉ ከባድ ጥቃት እየከሸፈ ሲሄድ «እስላማዊዉ መንግሥት » እንቅስቃሴ በአንጻሩ እየጠነከረ በግላቸዉ የሚንቀሳቀሱ አነስተኛ ቡድኖችንና የአልቃይዳ ክንፍ ቡድኖችን እያካተተ መጣ። ለዚህ ሁኔታ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች አሉት ሲሉ በመካከለኛዉ ምስራቅ «ቲንክ ታንክ» በሚባል የምርምር ድርጅት ተንታኝ አይማን ጃዋድ አልታሚም ይገልፃሉ።

Al-Nusra Front Kämpfer an der Front bei Aleppo 25.11.2014
የአል-ኑስራ ተዋጊዎች በአሌፖ ግንባርምስል Reuters/H. Katan

« የአልቃይዳዉ መሪ አል ዛዋሪ የ «IS» ፈጣን እንቅስቃሴን ለማስቆም መሞከሩ እስካሁን ምንም ድልን ያላገኘ የአልቃይዳ መሪ መሆኑን በገዛ ራሱ ስራ አስመስክሮአል። አል ዛዋሪ ይፋዊ ባልሆነ ርምጃ ማለትም ከመጋረጃ ጀርባ «IS» ለማጥቃት በተደጋጋሚ ሞክሮአል ማለት እንችላለን። በሌላ በኩል «IS» በሶማልያ አሸባብን ለመቅረብ ፈልጎ፤ ተባርዋል። በስተጀርባ የተካሄደዉ ንግግር በአልሸባብ መሪና በ«IS» ማዕከላዊ መሪዎች መካል ሳይሆን አልቀረም።»
በሁለቱ ጀሃዳዊ ድርጅቶች መካከል ያለዉ ዉዝግብ ምዕራቡ ዓለም ለሚያካሂደዉ ፀረ- ሽብር ዘመቻ ቀለል ያለ ስሌትን ያስገኝ ይሆን? እንደ አልታሚሚ ይህ አስተያየት የማይሰራ ጉዳይ ነዉ ።

Eiman al-Sawahiri Terrornetzwerk El Kaida ARCHIVBILD 2001
ኤማን አል-ዛዋሪምስል picture-alliance/dpa/dpaweb


ሶርያ ዉስጥ ሁለቱም ወገኖች አቋመቸዉን አጠናክረዉ ነዉ የሚገኙት ፤ ይህን ተከትሎ ግን በጣም ጥቂት የሚባሉ የአሸባሪ ቡድኖች ናቸዉ መዳከማቸዉ የተመለከተዉ። ስለሆነም ምዕራቡ ዓለም ቅዱስ ጦርነት ማለትም ጀሃድን ለመምታት አንዳች አመቺ ስልትን ማግኘት አልቻለም።

አዜብ ታደሰ
ተክሌ የኋላ