1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለነዳጅ ፍጆታ ቁጠባ ፤ የፈጠራ ሥራው ባለቤት መላ

ረቡዕ፣ ግንቦት 19 2007

ቁጥሩ ከ 96 - 100 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ ያላት ሀገር ፤ ኢትዮጵያ ፤ ለሕዝቧ የምግብ ብቻ ሳይሆን ፤ የኃይል ምንጭ (ኢነርጂ ) ዋስትናም ማግኘት ያስፈልጋታል። ለኤሌክትሪክ ማመንጫ ብቻ ሳይሆን ለተሽከርካሪዎች የነዳጅ ፍጆታም እንዲሁ!

https://p.dw.com/p/1FXCM
Porsche Symbolbild
ምስል AP

ለነዳጅ ፍጆታ ቁጠባ ፤ የፈጠራ ሥራው ባለቤት መላ

ይህን ችግር ለመቅረፍ ብሎም ለማስወገድ የኃይል ምንጫ ጠበብት በትጋት መሥራት ፤ የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ምሁራንም በየፊናቸው መላ መሻት ሳይጠበቅባቸው አይቀርም።

ኢትዮጵያ የተለያዩ አዝርእትን ማብቀል የሚያስችል ተስማሚ የአየር ጠባይና ለም አፈር ብቻ አይደለም ያላት። በተለያዩ የማዕድናት ሀብት የከበረች ሀገርም ናት። እርግጥ ለጊዜው በአካባቢአችን እንደሚገኙ ሀገራት ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ማዕድን ገና በገፍ የሚገኝበት ምልክት የታየ አይመስልም። ስለሆነም፤ ሕዝብንም ፣ መንግሥትንም ብዙ የሚያስወጣውን የነዳጅ ፍጆታ ለመቀነስ የሚያስችል መላ ሲሹ የኖሩት ተመራማሪና የፈጠራ ውጤት ባለቤት አቶ ብርሃን ተረፈ ተሰማ፣ ከአእምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት ፣ የአምሮአዊ ንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ የምሥክር ወረቀት (ሰርትፊኬት) ቢያገኙም ፤ ሞክረው የተሣካ ውጤት የተገኘበትን የነዳጅ ፍጆታ ቆጣቢ መሣሪያ ገና በይፋ በሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግ አልበቁም። በኢንዱስትሪ ፤ ደረጃውን ጠብቆ እንዲመረት ለማድረግ የበጀት እጥረት ስለገታቸው! አቶ ብርሃን ተረፈ የሠሩት የፈጠራ ሥራ፤ ከአውቶሞቢሎች የኋላ ጎማ ተሽከርካሪውን ጎማ ከሚያቅፈው የ«አልሚኒየም» ም ሆነ ብረት እሽክሊሊት ፤ የሚገጠምና ፣ ጎማውን በእጥፍ ፍጥነት እንዲሽከረከር የሚያበቃ ንዑስ መሣሪያ ነው። መሣሪያው የሚገጠመው እንዳልነው ጎማውን ከሚያቅፈው የአልሚኒየም ወይም የብረት እሽክሊሊት ላይ ነው፤ በእንግሊዝኛ Wheel Rim በሚሰኘው ላይ መሆኑ ነው። በዓለም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አውቶሞቢል በሠራችው ሀገር በጀርመን «ፌልገን» ነው የሚባለው ፤ ኢትዮጵያው ውስጥ በጣልያንኛው «ቸርኬ« በመባል የታወቀው መሆኑ ነው። አቶ ብርሃን ተረፈ ተሰማ ይህን መሣሪያ እንዴት ፈጠሩት? እንዴትስ እንዲፈተሽ አደረጉ? እስካሁን በይፋ ሥራ ላይ ለምን አልዋለም ?

የሥነ ቴክኒክ ፍቅር ያላቸው አቶ ብርሃን ተረፈ ተሰማ፣ በልጅነታቸው የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችንም ይሞክሩ እንደነበረ ገልጸዋል። ጎልማሣው የአእምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት ባለምሥክር ወረቀት ወደተጠቀሰው የፈጠራ ተግባር የገፋፋቸው ምን ይሆን? የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ወይም ኢንጂኔሪንግ ትምህርት? ዝንባሌ ? ተሰጥዖ?

Symbolbild Winterreifen Felgen
ምስል Fotolia/Shutter81

ከአልሚኒየም ወይም ብረት እሽክሊሊት Wheel Rim ወይም «ቸርኬ» ላይ የሚገጣጠመው መሣሪያ በትክክል ጎማው ላይ ምንድን ነው የሚያደርገው?

በአንድ ሊትር ቤንዚን 22 ኪሎሜትር ብቻ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ፤ በአቶ ብርሃን ተረፈ የፈጠራ ሥራ እገዛ ፤ በአንድ ሊትር ነዳጅ 80 ኪሎሜትር ያህል እንደሚጓዙ በሙከራ ቢረጋገጥም፤ ተጨባጭነት ባለው ሁኔታ ሥራ ላይ በማዋል ብዙዎች እንዲጠቀሙበት ለማድረግ ፣ የ 5 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት ነው የሚያሻቸው። የብሔራዊውን ችግር አሳሳቢነት ከልብ ተገንዝቦ መፍትሔ ያገኘው ያገር ሰው የፈጠራ ውጤት ይበል ሊያሰኝ ይገባል። ጥቅሙ በሚገባ እስከታወቀ ድረስ ፤ ለተግባራዊነቱ መተባበር የሚችሉ ሁሉ ከጎናቸው ቢሠለፉ እንደሚበጅ አያጠራጥርም። የፈጠራ ሥራውን ማድነቅ ብቻ ዋጋ የለውምና !

ለሀገርና ሕዝብ ጠቀሜታ የሚሰጡ የፈጠራ ሥራ ውጤቶች አሥፈላጊነት በውጭም በውስጥም በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታመንበት ነው። አቶ ብርሃን ተረፈ የሠሩት የነዳጅ ፍጆታ ቆጣቢ የፈጠራ ውጤት ፤ ሌሎች ታታሪዎችም በተለያዩ ዘርፎች ትኩረት በማድረግ እንዲነቃቁ አርአያነት ይኖረዋል።

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ