1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዜና | 07.02.2012 | 17:06

ኻርቱም፤ የታገቱት የቻይና ሠራተኞች ተለቀቁ

ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ታግተዉ የነበሩት ቻይናዉያን ተለቀዉ ወደኬንያ መሸጋገራቸዉን የሱዳን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አመለከተ። ቁጥራቸዉን ግን አልገለፀም። 29 ቻይናዉን ከአስር ቀናት በፊት ደቡባዊ ኮርዶፋን ዉስጥ በማፅያን መታገታቸዉን ሮይተርስ አስታዉቋል። ታጋቾቹ ካዑዳ ከተባለች ስፍራ በቀይ መስቀል አዉሮፕላን ተጭነዉ ወደናይሮቢ መወሰዳቸዉንና እዚያም ወደቻይና ኤምባሲ መተላለፋቸዉ ተገልጿል። የሱዳን ህዝብ የነፃነት ንቅናቄ ሰሜን፤ የተሰኘዉ ቡድን ቃል አቀባይ አርኑ ንጉቱሉ ሎዲ፤ ቀደም ብለዉ ታጋቾች በቅርቡ እንደሚለቀቁ ትናንት አስታዉቀዉ ነበር። በኻርቱም የቻይና ኤምባሲ ለጊዜዉ የሰጠዉ መግለጫ የለም።

ዋሽንግተን፤ IMF ለጅቡቲ ርዳታ ሊሰጥ ተስማማ

ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም IMF ጅቡቲ በመታት ድርቅ ሠበብ የገጠማትን ችግር ለማቅለል የሚረዳ ተጨማሪ 14 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ተስማማ። ገንዘቡ ከድርቅ በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ የተከሰተዉ የየሸቀጦች ዋጋ መናር ጅቡቲ ላይ ያስከተለዉን ተፅዕኖ ለማስታገስ እንደሚረዳም ተጠቅሷል። የIMF ምክትል ዳይሬክተር ኒማት ሻፊቅ የሸቀጦች ዋጋ ንረትና ድርቁ በተለይ ድሃዉን የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ እንደጎዳ ጠቁመዋል። ባለፈዉ የአዉሮጳዉያን ዓመት በአፍሪቃ ቀንድ በሶማሊያ፤ ኢትዮጵያ፤ ኬንያና ጅቡቲ የተስፋፋዉ ድርቅ ከ13 ሚሊዮን የሚልቅ ህዝብን ለርሃብ አደጋ አጋልጧል። IMF በዉሉ መሠረትም የመጀመሪያዉን 9,7 ሚሊዮን ዶላር ባስቸኳይ ለጅቡቲ መንግስት እንደሚሰጥም አመልክቷል።

ደማስቆ፤ ግጭትና የሩሲያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት

የሩሲያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ ከሶርያዉ ፕሬዝደንት ባሽር አልአሰድ ጋ ለመነጋገር ደማስቆ ገቡ። የላቭሮቭ የጉብኝት ዓላማ ፕሬዝደንቱ ስልጣን እንዲለቁ ለማግባባት ነዉ የሚል ጭምጭምታ ቢኖርም፤ አሰድ ግን በአገራቸዉ ህገመንግስት ላይ ህዝበ ዉሳኔ ሊጠሩ መዘጋጀታቸዉን አመልክተዋል። ከፕሬዝደንቱ ጋ ባደረጉት ንግግርም እያንዳንዱ የአገር መሪ ያለበትን ኃላፊነት ይገነዘባል ማለታቸዉ ተጠቅሷል። ላቭሮቭ አገራቸዉ የሶርያን አገዛዝ በሚመለከት ለያዘችዉ አቋምም በአሰድ ደጋፊዎች የሞቀ አቀባበል እንደተቸራቸዉ ተዘግቧል። እንዲያም ሆኖ ዛሬም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተቃዉሞ ባየለባት ሆምስ ከተማ ህዝብ በርከት ብሎ ይኖርባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን በተኩስ መደብደናቸዉ ተነግሯል። በጥቃቱ ቢያንስ የ50 ሰዎች ህይወት ማለፉን፤ በርካቶችም መጎዳታቸዉን፤ የህክምና ርዳታም ማግኘት አለመቻሉንም ነዉ አንድ የከተማዋ ኗሪ የሚያስረዱት፤ «በርካታ ሰዎች ጎዳና ላይ ወድቀዋል፤ ከባድ መሳሪያ ተኩሱ በየቦታዉ ቀጥሏል፤ የህክምና ርዳታዉ አዳጋች ነዉ፤ የተጎዱትን በየቤቱ ለማከምና ህይወት ለማትረፍ እየጣርን ነዉ፤ ሁኔታዉ ግን አስቸጋሪ እኛንም ጥይት እንዳይመታን እንሰጋለን። ከተማዋ ተነጥላለች ማንም መግባትም ሆነ መዉጣት አይችልም፤ ምን እንደምናደርግ አናዉቅም።» ይህ በእንዲህ እንዳለም ፈረንሳይ ዲፕሎማቷን በጥቂት ቀናት ዉስጥ ከሶርያ ለማዉጣት መወሰኗን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛሬ አመለከቱ። በርናርድ ቫሌሮ አገራቸዉ ከብሪታንያ ጋ በመነጋገርም በራሱ ህዝብ ላይ የኃይል ተግባሩን በቀጠለዉ የደማስቆ አገዛዝ ላይ ማዕቀብ ለማጥበቅ መዘጋጀቷንም ገልጸዋል። ፓሪስ ይህን ዉሳኔ ከማሳለፏ አስቀድሞ ጣሊያን፤ ብሪታንያ፤ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ ልዑካኖቻቸዉን ከሶርያ ማንሳታቸዉ ተዘግቧል።

ካኖ፤ የአጥፍቶ መጥፋት ፍንዳታዎች

ሰሜን ናይጀሪያ ዉስጥ ካዱና ከተማ የሚገኝ ወታደራዊ ሠፈር ላይ ያነጣጠሩ ሁለት የቦምብ ፍንዳታዎች መድረሳቸዉ ተነገረ። እማኞች ወደተጠቀሰዉ ስፍራ ሁለት ተሽከርካሪዎች ሲገቡና ከነአሽከርካሪዉ ሲጋዩ ማየታቸዉን ገልጸዋል። እንዲያም ሆኖ በስፍራዉ በሚገኙ ወታደሮች ላይ ያደረሰዉ ጉዳት ባለመኖሩ የከሸፈ ጥቃት ብለዉታል የመከላከያ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ሞሐመድ የሪማ። በአንፃሩ በተጠቀሰዉ ስፍራ ፍንዳታዉ እንደተከሰተ ህይወት ለማዳን የሄዱ ሠራተኞች መግባት መከልከላቸዉን ከከተማዋ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር አንድ ባለስልጣንን ጠቅሶ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። ጥቃቱን ቦኮ ሃራም የተሰኘዉ ፅንፈኛ እስላማዊ ቡድን እንደፈጸመዉ ነዉ የተገመተዉ። አንድ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገዉ ፖሊስ በከተማዋ ባካሄደዉ አሰሳና ዘመቻ ስምንት የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ተገድለዋል፤ መሣሪያምና ፈንጂዎችንም አግኝቷል። 

አቴንስ፤ የሥራ ማቆም አድማና ተቃዉሞ

ግሪክ ዉስጥ መንግስት የሚወስደዉን ከእዳ የመዉጫ እርምጃ በመቃወም የተጠራዉ አድማ የአገሪቱን እንቅስቃሴዎችን ገትቶ እንደዋለ ነዉ። በሺዎች የተገመቱ ዜጎች ቅዝቃዜዉን ሳይሰቀቁ በዝናብ በማዕከላዊ አቴንስ ሲንትጋም አደባባይ ተሰብስበዉ የአዉሮጳ ኅብረትና ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም ላይ ቁጣቸዉን ገልጸዋል። ሰልፈኞቹ ጠንካራ የበጀት ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ ያመለከተችዉ የጀርመንን ሰንደቅ ዓላማም በእሳት አጋይተዋል። የደሞዝ ቅነሳዉ ሃሳብ ብዙዎቹን ያበሳጨ እንደሆነ ነዉ እኝህ ጡረተኛ የሚገልፁት፤ «ለሰላሳ ዓመታት የተሻለ ኑሮ እንኖራለን በሚል ነበር የሠራነዉ፤ አሁን ግን እነሱ ሁሉንም ነገር እያከፉት ነዉ።» የጠቅላይ ሚኒስትር ሉካስ ፓፓዴሞስ መንግስት ከዚህ በፊት የታቀደዉን ደሞዝ የመቀነስ ርምጃ በአግባቡ ተግባራዊ አላደረገም በሚል ከአዉሮጳ ኅብረት፤ ከIMF እና ከአዉሮጳ ማዕከላዊ ባንክ ጫና ጠንክሮበታል። የሠራተኛ ማኅበራቱም እንደማይቀበሉት ነዉ አበክረዉ የሚገልፁት፤ ስታቲስ አኔስቲስ፤ «ይህንን መቀበል አንችልም። እነዚህ የቁጠባ ርምጃዎች አገሪቱን ከቀዉስ የሚያወጡ ሳይሆን ወደጥልቅ ሞት የሚያወርዱና ህዝቡንም ለድህነት የሚዳርጉ ናቸዉ።» የግሪክ መንግስት አሁንም በጉዳዩ ላይ መምከሩን ቀጥሏል። የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢቫንጌሎስ ቬኒዜሎስ የህዝባቸዉን ትብብር ለመጠየቅ ጥንታዊ የግሪኮችን አፈ ታሪክ ጠቅሰዉ ነበር የተናገሩት፤ «ይህ በእዉነቱ በቀላሉ መግቻ የሌለዉ ፈተና ነዉ፤ ይህን ችግር ለማስወገድ ደግሞ፤ ብቻዉን ከባዱን ፈተና ማለፍ የሚችለዉ ሄርኩለስ የለንም፤ በዚህ ምክንያትም በጋራ መቆም ይኖርብናል። ይህ መርሃግብራችን ከምንፈልገዉ ግብ እንደሚያደርሰን ህዝቡን ለማሳመን በጋራ መጣር አለብን።» እንዲያም የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ጆሴ ማኑዌል ባሮሶ አቴንስ ከዩሮ ቀጣና እንድትወጣ እንደማይፈልጉ አመልክተዋል። ቬኒዜሎስም ግሪክ በህብረቱ ቆይታ የጎደለዉን እንድታሟላ እንደሚመኙም ገልጸዋል።

ቴልአቪብ፤ የፋታህ፤ ሃማስ ስምምነት እና እስራኤል

በፍልስጤም ተፃራሪ ፓርቲዎች ሃማስና ፋታህ መካከል የተደረሰዉ ስምምነት የአካባቢዉን ሰላም ለማናጋት ያለመ ነዉ ስትል እስራኤል አስጠነቀቀች። ኳታር የሸመገለችዉ የሃማስ ፋታህ ድርድር በመጪዉ ግንቦት ወር ምርጫ እስኪካሄድ፤ ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ በመሪነት እንዲቆዩ አፈራርሟል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ትናንት ስምምነቱ እንደተፈረመ አባስ ወይ እስራኤልን ወይ ሃማስን ምረጡ ብለዋል፤ «ፕሬዝደንት አባስ ዶሃ ላይ ዛሬ የተፈረመዉን ተግባራዊ ለማድረግ ከተንቀሳቀሱ፤ የሰላሙን መንገድ ትተዉ የሰላም ጠላት ኃይሎች ጎን ተሰለፉ ማለት ነዉ። ሁለቱም መያዝ አይቻልም። ስምምነቱ ወይ ከሃማስ ወይ ከእስራኤል ሰላም ጋ መሆን ነዉ ያለበት።» አባስ ወደሃማስ በመቅረባቸዉ በየዓመቱ የሚገኘዉን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ርዳታና ምናልባትም የነበራቸዉን ፖለቲካዊ ድጋፍ ሊያጡ እንደሚችሉ አሶሲየትድ ፕረስ በዘገባዉ ጠቁሟል። SL/NM