1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ለእስራኤል የምትሰጠው ድጋፍ ያስከተለባት ክስና ተቃውሞ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2016

በዚህ ዓመት ከጥር እስከ ሚያዚያ እስራኤል ከጀርመን የገዛችው የጦር መሣሪያ 326.5 ሚሊዮን ዩሮ የወጣበት ነው።ይህም በ2022 ለጦር መሳሪያ ከወጣችው 32 ሚሊዮን ዩሮ በአስር እጅ ይበልጣል። በግዥው ከተካተቱ ውስጥ 20.1 ሚሊዮን ብር የወጣባቸው ፀረ-ታንክ መሣሪያዎች እና የአውቶማቲክና የመለስተኛ አውቶማቲክ ጠመንጃ ጥይቶች ይገኙበታል።

https://p.dw.com/p/4f541
Israel I Bundeskanzler Scholz besucht Benjamin Netanjahu
ምስል Michael Sohn/AP/picture alliance

ጀርመን ለእስራኤል የምትሰጠው ድጋፍ ያስከተለባት ክስና ተቃውሞ

ጀርመን ለእስራኤል የምትሰጠው ድጋፍ ከሀገር ውስጥም ከውጭ ከተለያዩ ወገኖች ክስና ተቃውሞ እየቀረበባት ነው። ይህን የጀርመን መንግሥት አቋም በመቃወም ለወራት የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፎች ቢካሄዱም የጀርመን መንግሥት ፖሊሲ አውጭዎችን አስገድደው በእስራኤል ላይ የያዙትን አቋም ማስቀየር አልቻሉም ። ያም ሆኖ ተቃውሞ እና ክሱ በተለያየ መንገድ እንደቀጠለ ነው። መቀመጫቸውን በርሊን ያደረጉ ጠበቆች በቅርቡ በፍልስጤሞች ስም ለአንድ የጀርመን ፍርድ ቤት አስቸኳይ አቤቱታ አቅርበዋል። የአውሮጳ የሕግ ድጋፍ ማዕከል የተባለው ለፍልስጤማውያን ንቅናቄ ድጋፍ የሚሰጠው የጠበቆች ስብስብ በጀርመን የጦር መሣሪያዎች ጋዛ ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀልና የጦር ወንጀሎችን የመሳሰሉ ከባድ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰቶች ይፈጸማሉ ሲል ከሷል። ጠበቆቹ የጀርመን ፍርድ ቤት የነዚህን መሣሪያዎች አቅርቦት እንዲያስቆም ጠይቀዋል። ጀርመን ከዚህ ቀደም ለፍልስጤማውያን እርዳታ ለሚሰጠው የተመድ  ድርጅት ትሰጥ የነበረውን እርዳታ ማቋረጧንም በመቃወም እርዳታውን እንድትቀጥል ትዕዛዝ እንዲሰጣት ጠይቀዋል።  በፍልስጤማውያኑ ስም ባለፈው የካቲት ወር የቀረበ ሌላ ክስ ደግሞ የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክንና የኤኮኖሚ ሚኒስትር ሮበርት ሀቤክን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የጀርመን መንግሥት ባለሥልጣናትን የጦር መሣሪያዎቹን ሽያጭ ፈቃድ በማጽደቅ ወንጅሏል። ከጀርመን በተለየ ካናዳና ኔዘርላንድስ ለእስራኤል የሚሰጡትን ወታደራዊ እርዳታ ማጤን ጀምረዋል።


የእስራኤልና የጀርመን ግንኙነት በቅርቡ በወጣ የዓለም አቀፉ የሰላም ጥናት ተቋም SIPRI ዘገባ መሠረት ከጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ.ም. አንስቶ እስከ 2023 ዓ.ም. ድረስ ጀርመን ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ ለእስራኤል ብዙ የጦር መሣሪያ የምታቀርብ ሀገር ናት። በጎርጎሮሳዊው 2022 እና በ2023 እስራኤል ከውጭ ያስገባቻቸው የጦር መሣሪያዎች በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከሁለቱ ሀገራት የተገዛ ነው። የሁለቱም የመሣሪያ አቅርቦት እኩል ደረጃ የሚባል ነው።  ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ጀርመን ለእስራኤል እንዲሰጡ ከፈቀደችው የጦር መሣሪያዎች መካከል የባህር ኃይል መርከቦች ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ፈንጂዎች የታንኮችና የጦር አውሮፕላኖች አካላት ይገኙበታል ። በዚህ ዓመት ከጥር እስከ ሚያዚያ እስራኤል ከጀርመን የገዛችው የጦር መሣሪያ 326.5 ሚሊዮን ዩሮ የወጣበት ነው።ይህም በጎርጎሮሳዊው 2022 ከወጣው 32 ሚሊዮን ዩሮ በአስር እጅ ይበልጣል። በዚህ ግዥም ከተካተቱ ውስጥ 20.1 ሚሊዮን ብር የወጣባቸው 3 ሺህ ከቦታ ቦታ መዘዋወውር የሚችሉ ፀረ-ታንክ የጦር መሣሪያዎች እንዲሁም 50 ሺህ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ የአውቶማቲክና የመለስተኛ አውቶማቲክ ጠመንጃ ጥይቶች ይገኙበታል።

የዘሄጉ የተመድ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ዳኞች
የዘሄጉ የተመድ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ዳኞችምስል Patrick Post/AP Photo/picture alliance

ከነዚህም አብዛኛዎቹ የታዘዙት ከመስከረም 26 ቀን 2016 ዓመተ ምህረቱ ሀማስ በእስራኤል ላይ ከጣለው ጥቃት በኋላ ነው። ጀርመን ለእስራኤል ከሸጠቻቸው መሣሪያዎች ውስጥ የአየር መከላከያ ስርዓት እና የመገናኛ መሣሪያዎች ዋናውን ቦታ ይይዛሉ።  የእነዚህ የጦር መሣሪያዎች ሽያጭ ከመስከረም 26 ቀን 2016 ዓምቱ ያልተጠበቀ የሀማስ ጥቃት በኋላም መቀጠሉን ጀርመንን በፍልስጤሞች ስም የከሰሱት ጠበቆች ይናገራሉ።ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ደግሞ  ላቲን አሜሪካዊቷ ሀገር ኒካራጉዋ በጋዛ እየተፈጸመ ነው ላለችው «የዘር ማጥፋት» ወንጀል ድጋፍ እየሰጠች ነው በማለት ጀርመንን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ICJ ከሳለች። ኒካራጓ  በዘሄግ ኔዘርላንድስ ለተሰየመው ችሎት ጀርመን ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመተላለፍ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ በማቅረብ «ለዘር ማጥፋት» ወንጀሉ ተባባሪ እየሆነች ነው ስትል ክሷን አሰምታለች። በኔዘርላንድስ የኒካራጉዋ አምባሳደር ካርሎስ ሆዜ ፍራንሲስኮ አርጉዌሎ ጎሜዝ ለዓለም አቀፉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ ጀርመን መንግሥታት ወንጀለኞችን ከማገዝ እንዲቆጠቡ የሚደነገጉትን ዓለም አቀፍ ህጎች ጥሳለች ብለዋል። 


«የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ ከባድ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ እና ሌላ ትኩረት የሚያሻው የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ፍልስጤም ውስጥ እየደረሰ ነው። እነዚህ የሕግ ጥሰቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እያዩ በግልጽ ነው የሚፈጸሙት። በመገናኛ ብዙሀንም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ከዓለም ህዝብ አብዛኛው ሊሆን የሚችል ተመልክቶታል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በዚህ ዓይነት ደረጃ ሲከሰት ወይም የመከሰቱ አደጋ ሲኖር የመንግሥታት ግዴታዎች ግልጽ ናቸው። መንግሥታት እርዳታ ከመስጠትም ሆነ ወንጀለኞችን ከማገዝ መቆጠብ ብቻ ሳይሆን እነዚህ መሠረታዊ ደንቦች መከበራቸውን ለማረጋገጥና እዳይጣሱ ለመከላከል የተቻላቸውን ሁሉ ሊጥሩ ይገባል። እነዚህን ግዴታዎች በሚመለከት ሌላ ሦስተኛ መንግሥታት አይኖሩም መንግሥታት ሁሉ ግዴታዎቹ የማክበር ሃላፊነት አለባቸው። ጀርመን በሁሉም መንግሥታት ላይ የተጣሉትን እነዚህን ግዴታዎች ጥሳለች።»

አምባሳደር ካርሎስ ሆሴ ጎሜዝ በኔዘርላንድስ የኒካራጉዋ አምባሳደር
አምባሳደር ካርሎስ ሆሴ ጎሜዝ በኔዘርላንድስ የኒካራጉዋ አምባሳደርምስል Robin van Lonkhuijsen/ANP/IMAGO


ጀርመን እስራኤልና ኢራንአምባሳደር ጎሜዝ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት የጀርመን የጦር መሳሪያ አምራች ኢንዱስትሪዎች አሁን ከተፈጠረው ሁኔታ በተለይም ከመስከረም 26ቱ ጥቃት ወዲህ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በዚህ ረገድ ከእስራኤል ጋር የሚፈጽሟቸው የጋራ ውሎች ጨምረዋል። የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ባለፈው ህዳር ሀገራቸው ለጀርመን «አሮው ሶስት» የተባለ 3.6 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የአየር መከላከያ ስርዓት ሽያጭ ስምምነት በይፋ መፈጸሟን በኩራትና በይፋ መናገራቸውን አስታውሰው ይህም እስራኤል የፈጸመችው እጅግ ከፍተኛ የመከላከያ የጦር መሣሪያ ሽያጭ መሆኑንም ተናግረዋል። እስራኤልም የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች እየተባለ የሚቀርብባትን ክስ ራስን የመከላከል መብቴን እየተጠቀምኩ ነው በማለት ትከራከራለች።  አምባሳደር ጎሜዝ  ጀርመን ራስን መከላከልንና የዘር ማጥፋት ወንጀልን መለየት ያቃታት ይመስላል ሲሉም ነቅፈዋል።  ኒካራጓ ጀርመን ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ማቅረብ የማቆሟን ሂደት ማረጋገጥ እንደምትሻ ለችሎቱ አሳስባም ነበር። ለፍልስጤማውያን እርዳታ ለሚያቀብለው የተመድ ተቋም  ጀርመን ያቋረጠችውን እርዳታ እንድትቀጥል እንዲደረግም አሳስበዋል።

ጀርመን የቀረበባትን ክስ አጣጥላለች። ጀርመን ለእስራኤል የጦር መሳሪያ በመላክ የተመድን የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከያ ስምምነትን ጥሳለች ስትል ኒካራጉዋ የመሰረተችባትን ክስ ውድቅ እንዲያደርግ የተመድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት(ICJ)ን ባለፈው ሳምንት ጠይቃለች። በዚሁ ወቅት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕግ አማካሪ ታንያ ፎን ኡስላር ግላይሸን ለዘሄጉ ፍርድ ቤት ባቀረቡት መከራከሪያ  ክሱን መሰረተ ቢስ ሲሉ ውስድቅ አድርገዋል ። « የኒካራግዋን መሰረተ ቢሶ ክሶች እንደምንቃወም ገልጸናል። በዘር ማጥፋት ወንጀል እና በዓለም አቀፍ ሕጎች ያሉብንን  ሃላፊነቶች በሙሉ እናውቃለን።ህጎቹንም እናከብራለን። »የሕግ አማካሪዋ እንዳሉት ጀርመን ኒካራግዋ እንደምትለው ሳይሆን ግጭቱን በሚመለከት ዓለም አቀፍ ሕግን በማክበር ነው የምትንቀሳቀሰው።

በዘሄጉ ፍርድ ቤት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕግ አማካሪ ታንያ ኡስላር ግላይሸን እና የዓለም አቀፍ ሕግ ፕሮፌሰር ክርስቲያን ታም
በዘሄጉ ፍርድ ቤት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕግ አማካሪ ታንያ ኡስላር ግላይሸን እና የዓለም አቀፍ ሕግ ፕሮፌሰር ክርስቲያን ታምምስል Dursun Aydemir/Anadolu/picture alliance

 
«ዛሬ ጀርመን በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ፊት ለዓለም አቀፍ ሕግ ማዕቀፍ ተገዥ መሆንዋን፣በዚህ ፈታኝ ሁኔታም ትክክለኛውን ሚዛን ለመያዝ እንደምትሰራ አሳይታለች። ኒካራግዋ እንደምትለው ሳይሆን በግጭቱ ተሳታፊ ለሆኑት ለሁለቱ ወገኞች ፍትህ እየጣርን ነው። የምንመራው ዓለም አቀፍ ሕግን በማክበር ነው። ለእስራኤል ደኅንነት ሃላፊነትን አለብን፤ ጋዛ ውስጥ ያሉ የፍልስጤም ህዝቦች ስቃይ ይሰማናል፤ የእስራኤል ታጋቾች ነጻ እንዲለቀቁ የሚደረገውን ጥረት ከዚህ በተጨማሪም በሁለት መንግሥታት መፍትሄ መሠረት የፍልስጤም ህዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በማክበር ነው ። »እውን ሀማስን ሙሉ በሙሉ «ማጥፋት» ይቻላል?    
የጀርመን መንግሥት ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ እስራኤልን በመደገፍ ክሶች ቢቀርቡበትም አሁንም በእስራኤል ላይ ከሚከተለው አቋሙ ዝንፍ አላለም። የዚህ መሠረታዊው ምክንያት ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከእስራኤል ጋር በመሰረተችው አዲስ ግንኙነት ምክንያት የምትከተተለው ፖሊሲ መሆኑን ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አሥራት በጀርመን የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ ፣ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ  ለቼቬለ ተናግረዋል። ኒካራግዋ በጀርመን ላይ ያቀረበችውን ክስና እና የጀርመን መከላከያ መልስ ያዳመጠው የቀረበለት ፍርድ ቤቱ በሳምንታት ውስጥ ጊዜያዊ ውሳኔዎችን ይሰጣል ተብሎ ቢጠበቅም የመጨረሻው ፍርድ ግን ዓመታት ሊወስድ ይችላል ተብሏል። ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አሥራተም ሆኑ ብዙዎች ተንታኞች ይህ በጀርመን ላይ ምንም ተጽእኖ የሚያሳድር አይሆንም ነው የሚሉት።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ