1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድብርት፤ በሽታው እና መፍትሄው

ዓርብ፣ የካቲት 29 2011

ድብርት ምንድን ነው? እንደ የዓለም የጤና ድርጅት WHO ከሆነ በአለም ዙሪያ ከ 300 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የበሽታው ተጠቂ ናቸው።ለምን በሽተኞች ለሚቀርቧቸው ሰዎች እንኳን ለመንገር አይደፍሩም? መፍትሄውስ? ከበሽተኞች እና ከስነ አዕምሮ ባለሙያዎች እንሰማለን።

https://p.dw.com/p/3EdPE
Symbolbild Angst
ምስል picture-alliance/chromorange

ድብርት፤ በሽታው እና መፍትሄው

ውይ ዛሬስ ድብር ብሎኛል ብለን እናውቃለን። ግን ይህ ድብርት ሲደጋገም ራስን እስከማጥፋት የሚያደርስ  በሽታ መሆኑን እናውቃለን? 
ድብርት በእንግሊዘኛው (Depression) የአዕምሮ በሽታ ነው። እንደ የዓለም የጤና ድርጅት WHO ከሆነ በአለም ዙሪያ ከ 300 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የበሽታው ተጠቂ ናቸው። ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የበሽታው ተጠቂ ናቸው። ሰዎች ሳይጠነቀቁ ቀርተው የሚይዝ በሽታም አይደለም። ይሁንና ታታሚዎች የበሽታቸውን ስሜት በሚስጥር ይይዛሉ። በተለይ አፍሪቃ ውስጥ። የ DW ዘጋቢ ኬቲ ሾርት ከዛምቢያ እንደዘገበችው ከሆነ ዛምቢያ ውስጥ እድሜያቸው ከ 14 እስከ 25 የሆኑ ወጣቶች ዘንድ የታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ከባድ የሚያደርገው ደግሞ በቂ የህክምና ባለሙያ አለመኖሩ እና ማህበረሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ ማነስ ነው። 

ሉሳካ ውስጥ የሚገኝ አንድ የአዕምሮ ሆስፒታል እንደሚያመላክተው በድንገተኛ ወደ ሆስፒታል ከሚመጡት ሰዎች መካከል ከ 34 በመቶ በላይ ራሳቸውን የጎዱ ወይም ህይወታቸውን የማጥፋት ሙከራ ያደረጉ ናቸው። አብዛኞቹም ከድብርት በሽታ ጋር በተያያዘ ነው። በዛ ላይ ለአዕምሮ ህሙማን የተገነባው ብቸኛ ሆስፒታል የበሽተኛውን ቁጥር መቋቋም አልቻለም ትላለች ካቲ። የ 22 ዓመታ ናታሻ ካምፔ ከእነዚህ ህሙማን አንዷ ናት። እናቷ ሲሞቱ ነው የድብርት በሽታው የጀመራት « እሷ ካረፈች በኋላ አጠገቤ ሰው ስለሌለኝ የብቸኝነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ብቻ በገንዘብም የሚደግፈኝም ሆነ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ፣ ህይወትን እንዴት መምራት እንደምችል ድጋፍ የሚሰጥ ሰው እፈልግ ነበር። በተለይ ወላጆች በህይወት ከሌሉ ይህንን ለማግኘት መፈለግ አለ። ስለዚህ ሞትን የተሻለው አማራጭ አድርጌ አይ ነበር።ከየት እንደምጀምር ፣ወደየት መሄድ እንዳለብኝ መላውን ስላላወኩ ማለት ነው።

Infografik Depression weltweit nach Region ENG


የ 18 ዓመቷ ናታሻ ካዚኔም የበሽታው ተጠቂ ናት «የድብርቴ ምክንያት በጣም የምወዳት አክስቴን በማጣቴ ነበር። ከሞተች ሁለት ወር በኋላም ስሜቴን መቆጣጠር አልችልም ነበር። ያኔ ጠንካራ ድብርት ውስጥ ገባሁ። ተስፋ ቢስነት ተሰማኝ።  ራሴን የማጥፋት ስሜት ይሰማኝ ነበር። መብላት እና መጠጣት አልችልም ነበር። ወላጆቼ ተፋተዋል። ያም ጎድቶኛል።»

በተለይ ደግሞ በማህበረሰቡ ዘንድ ጠንካራ ሆነው መገኘት የሚጠበቅባቸው ወንዶች ድብርት ስያዙ ይበልጥ ፈታኝ ያደርገዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ድብርት በብዙዎች ዘንድ በግልፅ የሚወራ በሽታ አይደለም። ሊዛ ቶምሰን በዛምቢያ የስነ ልቦና ሀኪም ናቸው። በድብርት በሽታ ምክንያት ወደ እሳቸው የሚመጡት ወጣት በሽተኞች መንስኤ የተለያዩ ናቸው ይላሉ።
« ከቤተሰብ ጋር የሚያገናኘው ነገር ይኖራል። ወይም ከኢኮኖሚ ጋር፣ በሀገሪቱ ስራ የማግኘት ተስፋ አለን። ወይስ እኛ ወጣቶች መቼም ስራ አናገኝም። የመሳሰሉት እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ወጣቶችን ድብርት ውስጥ ሊጥሉ ይችላሉ።»
 
ይህ ዛምቢያ ውስጥ ነው? ኢትዮጵያስ? የበሽታው ተጠቂ የሆኑ እና ለ DW ለመንገር የደፈሩ ወጣቶች ተከታዮን ፅፈውልናል።

«እኔ የዚህ በሽታ ተጠቂ ነኝ። መፍትሄ ማገኘት አልቻልኩም በውስጤ ትንሽ ችግር አጋጥሞኛል መፍትሄ እንዴት ማገኘት እንዳልብኝ አላውቅም።»
«ድብርት ያለበት ወንድም አለኝ እራሱን ለማጥፋት ብዙ ጊዜ ሙከራ ሲያደርግ ይዘንዋል ምን ማድረግ አለብን?ሲሉ ይጠይቃሉ።» 

የህክምና ባለሙያዋ ሊዛ ቶምሰን ምን ይላሉ? «ድብርት መታከም የሚችል በሽታ ነው። መጀመሪያ ድብርቱን ያስነሳውን መንስኤ ማጥናት ያስፈልጋል። ከዛም በቴራፒ ወይም በመድሓኒት ህክምና መስጠት ይቻላል። »


ታድያ በሽታውን በህክምና መከታተል ከተቻለ ለምን በተለይ አፍሪቃ ውስጥ ሚስጥር ተደርጎ ይወሰዳል። የ DW ባልደረባ ዋንጂኩ ምዋራ አጠያይቃለች።« በአፍሪቃ በርካታ ማህበረሰቦች ዘንድ ችግሩ ቃል እንኳን የለውም። የምትበላው አለህ፤ ጥሩ ስራ አለህ ምን ሆነህ ነው ደበረኝ የምትለው። ምክንያቱም ይህ ችግር የሚፈጠረው ምንም ከሌለሽ ብቻ ነው ተብሎ ይወሰዳል። ነገር ግን ከምንሰማቸው እና ከምናነባቸው ዘገባዎች መረዳት የሚቻለው ችግሩ ሁሉንም ሰው እንደሚመለከት ነው።የትምህርት ደረጃ ወይም የማህበረሰባዊ ደረጃውን ሳይል። ይሁንና የማይዳሰስ ርዕስ ተደርጎ ነው የሚታየው።»

Infografik Depression weltweit nach Region ENG
ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የበሽታው ተጠቂ ናቸው።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመላክተው ሰዎችን ለሞት ከዳረጉ ምክንያቶች መካከል ራስን ማጥፋት በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። በተለይ እድሜያቸው 15 እስከ 29 ባሉ ወጣቶች ዘንድ። ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች መዘርዝርን በትክክል በድብርት በሽታ ከሚጠጉት ሰዎች ይልቅ ለማግኘት ይቀላል። ምክንያቱ ቀደም ሲል እንደተገለፀው ሰዎች ለመናገር ስለማይደፍሩ ነው። ታድያ ራሳችን ወይም ቅርብ የሆኑ ሰዎቻችን በበሽታው ይጠጉ እንደው ማወቅ እንዴት እንችላለን? ምልክቶቹ ምንድን ናቸው? ዶክተር ቺንየሉ አዳ ኢኬአኮ
«ድብርት የአይምሮ ማዕከላዊ የነርቭ መናጋት ነው። በየቀኑ የማዘን ምልክት ይታያል። ወይ በቂ እንቅልፍ ማጣት ወይም ከበቂ በላይ መተኛት፣  ኃይል ማጣት፣ አንድ ነገር ላይ አተኩሮ መስራት አለመቻል። የጥፋተኝነት ስሜት፣ ተስፋ ቢስነት፣ ዋጋ ቢስነት፣ ርዳታ ቢስነት የመሳሰሉት ናቸው።»
ወጣቶች ድብርት ሲይዛቸው ናይጄሪያ ውስጥ ምን እንደሚያደርጉ DW አጠያይቆ ነበር።  የተወሰኑ ወጣቶች የመለሱልንን እናሰማችሁ።

«ሙዚቃ አዳምጣለሁ። ከማነባቸው ልብ ወለድ መፀሀፎች እንዲያነቃቁኝ እሞክራለሁ።»

«በእግር ሽርሽር እሄዳለሁ። ጓደኞቼ ጋር እደውላለሁ»

«ክርስትያን ነኝ። መፅሀፍ ቅዱሴን አነባለሁ። ወደ እግዚያብሄር እፀልያለሁ።»

ብለውናል። አፍሪቃ ውስጥ በሽታው የበለፀጉ ሀገሮች በሽታ ወይም ከሀብት እና ዝና ጋር በተያያዘ የሚመጣ በሽታ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዛም አልፎ ሰይጣን ነው። አጋንንት ነው ሌላም ሌላም ይባላል። « መጀመሪያ የሚሉት ነገር ። እንፀልያለን። ወይም ሰዎች ከሚሏቸው ዋንኞቹ ነገሮች አንዱ ሀሳብ አብዝተሽ ነው። ማሰብሽን አቁሚ ይላሉ። ችግሩ ግን በቁጥጥር ስር ያለ አይደለም። ዛሬ ራሴን አጨናንቃለሁ አይ  ድብርት እንዳይዘኝ አላጨናንቅም የሚል ምርጫ የሚጠጥ በሽታ አይደለም። በተለይ አፍሪቃ ውስጥ በፀሎት ከጎንሽ ነን ይላሉ።ይሁንና መፍትሄው አይደለም። ከድብርት ለመላቀቅ መፍትሄን ባለሙያ ዘንድ ማፈላለግ ነው።»
ድብርት የያዛቸው እንዴት ብለው ነው ለሌሎች ስለስሜታቸው የሚናገሩት? ይህ በተለይ ለወንዶች ከባድ እንደሆነ ነው ዶክተር ኢኬአኮ የሚናገሩት። «አንዳንድ ጊዜ ድብርት ያለባቸው ወንዶች በቀላሉ ይቆጣሉ።  ትናንሽ ነገሮች ያበሳጫቸዋል። ይህም የበለሰ ያስጨንቃቸዋል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የእንቅልፍ ችግር አለባቸው። መተኛት አይችሉም። ወይ ደግሞ ብዙ ይተኛሉ»

የ DW ባልደረባ ዋንጂኩ ለምን ይህንን ርዕስ ማድረግ እንሳስፈለገ ታስረዳለች።«በድብርት ምክንያት ራሳቸውን የሚያጠፉትን ሰዎች ቁጥር ለመቀነስ ነው! ሰዎች የተሰማቸውን መግለፅ ሲችሉ ችግራቸውን መረዳት ይቻላል። በድብርት የተያዘው ሰው ከሞተ በኋላ ምን ማድረግ ነበረብኝ ብሎ መፀፀቱ ዋጋ የለውም። ታማሚውን ደግሞ እያሳለፍክ ያለኸው ጊዜ ለእኔ በደንብ ግልፅ አይደለም። ሀኪም ማየት ይሻላል ማለት ነው። ችግሩ የሚገባቸው እንደ የስነ አዕምሮ ፤ የስነ ልቦና የመሳሰሉ ሀኪሞችን። ስለሆነም ስለ ድብርት እና የሚያስከትለው ነገር ማውራቱ አስፈላጊ ነው።»

የድብርት አይነቱ ከሰው ሰው ይለያያል። ህክምናውም እንደክብደቱ። ዋናው ችላ ብሎ ከቁጥጥር ውጭ እስኪሆን አለመጠበቅ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ። 
 ልደት አበበ