1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዒድ አከባበር በድሬ ደዋ ከተማ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 24 2014

ከቀናት በፊት ሁከት ተፈጥሮባት በነበረችው ድሬደዋ 1443ኛው የኢድ አል- ፊጥር በዓል በርካታ ቁጥር ያላቸው የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሯል።

https://p.dw.com/p/4AjWQ
Äthiopien Eid al-Fitr in Dire Dawa
ምስል Messay Teklu/DW

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣቶችን ጨምሮ ለዶይቼ ቬለ አስተያየት የሰጡ ነዋሪዎች በጎንደር በተከሰተው ድርጊት ማዘናቸውን ገልጠው መንግስት በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብለዋል።

በዛሬው የኢድ አል - ፊጥር በዓል አከባበር ላይ ከተገኙ ተሳታፊዎች አንዱ የሆኑት አቶ ካሚል ኢብራሂም በጎንደር የተፈጠረው ድርጊት አሳዛኝ ፤ ነገር ግን ህዝብን የማይወክል መሆኑን ገልፀው ሙስሊሙ ማህበረሰብ እንዲህ ያለ ጠብን በጥፋት መመለስ የለበትም ብለዋል።

ከቀናት በፊት በድሬደዋ ተከስቶ በነበረው ሁከት የሳተፉት" መስጊድ የማይመጡ ፣ የእምነቱ አባቶች እና መንግስት የሚለውን የማይሰሙ ጥቂት አካላት ያደረጉት ነው" ያለው  በድሬደዋ የእስልምና እምነት ተከታይ ወጣቶች አስተባባሪ አብዱልአዚዝ ሻፊ ይህንንም በሂደት መቅረፍ እንደሚያስፈልግ እና እነሱም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፃል።

Äthiopien Eid al-Fitr in Dire Dawa
የኢድ በዓል አከባበር በድሬዳዋምስል Messay Teklu/DW

"እያንዳንዱ ሰው ጥረት አድርጎ ሰላም ማስፈን አለበት ያለው ወጣት ራይት ዩሱፍ በማህበራዊ ሚዲያ የሚራገቡ ነገሮችን ማስቆም አለብን" ብሏል ።

መሀመድ ሙደሲር ለዶይቼ ቬለ" በጎንደር በተፈጠረው ድርጊት የተሳተፉ አካላትን መንግስት በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ተስፋ አለን ይህንንም ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያችንን እያቀረብን እንገኛለን" ብሏል።

በረመዳን ወር የታየው የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ተግባር በዛሬው የበዓሉ እለት የተቸገሩትን በመርዳት እና በጋራ በመሆን እንዲከበር ጥሪ ቀርቧል።

Äthiopien Eid al-Fitr in Dire Dawa
የኢድ አከባበር በድሬዳዋምስል Messay Teklu/DW

በበዓሉ የተገኙትን የመስተዳድሩ ከንቲባ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የእስልምና እምነት መሪዎች የከተማዋን የፍቅር እና የመቻቻል ለመጠበቅ  ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠበቅ ያለ የፀጥታ ጥበቃ የታየበት የዕለቱ በዓል ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን የድሬደዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገፁ አስታውቋል ።
 

መሳይ ተክሉ

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ