1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ግጭት፡ የሰላማዊ ሰዎች ግድያ እና የሰላም ጥሪ

ሰኞ፣ መጋቢት 30 2016

በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፉት አስር ቀናት የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች እና የታጣቂዎች እንቅስቃሴ መበርታቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። በተለይ ቶሌ እና አመያ በተባሉ ወረዳዎች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

https://p.dw.com/p/4eYM9
የኦነግ ሰንደቅ ዓላማ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባ (ኦነግ) በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቶሌ ወረዳ 20 ያህል ሰላማዊ ሰዎች በመንግስት ሰራዊት ተገድለዋል ሲል ከሷል፡፡ ምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያ ግጭት፡ የሰላማዊ ሰዎች ግድያ እና የሰላም ጥሪ

ለመዲናዋ አዲስ አበባ እጅግ ቅርብ ርቀት ላይ የምገኘው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን  በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል የሰላምና ፀጥታ ይዞታው እጅጉን ፈታኝ ከሆኑባቸው አከባቢዎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሆኗል፡፡ በዚህ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እንደሚዘወተር የሚገልጹት የአከባቢው ነዋሪዎች ተደጋጋሚ ያሉት ግድያ በሰላማዊ ዜጎች ጭምር ላይ እንደሚፈጸም ጥቆማቸውንም ይሰጣሉ፡፡

በዞኑ ከቶሌ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ለደህንነታቸው ስባል ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ ነዋሪ በቅርቡ በተለይም ከ10 ቀናት ወዲህ በዚህ ወረዳ ተባብሷል ባሉት የአማጺ ታጣቂዎች እና የመንግስት ሰራዊት እንቅስቃሴ ሰላማዊ ዜጎችም ጭምር መገደላቸውን ጠቁመዋል፡፡

 የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የ30 ዓመታት ጉዞ

ነዋሪው በአስተያየታቸው ሁለቱም የታጠቁ አካላት አንዱ ሌላውን የታጠቀ አካል ትደግፋለህ በሚል በገቢያ እና በቤታቸው ጭምር እንደምገደሉ አንስተዋል፡፡ በተመሳሳይ ዞን ውስጥ በምገኘው አመያ በተባለ ወረዳም የነዋሪዎች መኖሪያ መንደር ጭምር የወደሙበት ውጊያ እና ጥቃት መፈጸሙ ተመልክቷል፡፡ ይህ ደግሞ በአከባቢው ነዋሪዎች ላይ ከሚያደርሱ የህይወት ጥፋት እና ኢኮኖሚያዊ መስተጓጉል በላቀ ከፍተኛ ስጋትን ያጫረ ማህበራዊ ቀውስ ስለማስከተሉም አስተያየት ሰጪው አስረድተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል 30ኛ ዓመት የሚያሳይ ባነር
የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመት ባለፈው ሣምንት ያከበረው የኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች እና በታጣቂዎች መካከል ብርቱ ግጭት የሚካሔድበት ነው። ምስል Seyoum Getu/DW

ስለ ጥቃቱ የኦነግ መግለጫ

ከዚህ ባሻገር ተቃዋሚው የኦሮሞ ነጻነት ግንባ (ኦነግ) በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ባወጣው መግለጫ በዚሁ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቶሌ ወረዳ 20 ያህል ሰላማዊ ሰዎች በመንግስት ሰራዊት ተገድለዋል ሲል ከሷል፡፡ ኦነግ የ20 ሰዎች ስም ዝርዝር ባካተተበት በዚህ መግለጫው በሰላማዊ ዜጎች ላይ ይፈጸማል ያለው ወታደራዊ እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ መክፋቱን አስረድቷል፡፡ ኦነግ በቶሌ ተወስዷል ያለው “የጅምላ ግድያ” አስከፊ ነው በማለት ግድያውንም ኮንኗል፡፡

 የተገደሉ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በዚህ ላይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፡ “በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት በጦር ወንጀልም ሊያስጤቅ የሚችል” ሲሉ ተችተዋል፡፡ አቶ ለሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሷል ባሉት በመሰል የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት በርካቶች ህይወታቸውን እንደሚያጡም በመግለጽ የነዋሪዎች ሃብት ንብረትም እንደሚወድም ከማህበረሰብ እና “አደረጃጀታችን” ካሉት አካላት የሚደረሷቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩም ገልጸዋል፡፡

ኦነግ መግለጫ ካወጣበት የቶሌ ጥቃት በተጨማሪ በአመያ ወረዳም በክልሉ ታጥቀው በምንቀሳቀሱ አማጺያን ጭምር በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መኖራቸውን ነዋሪዎች ብገልጹም ኦነግ ስለዚህ ያለው ነገር የለም፡፡ አቶ ለሚን በክልሉ ለሚፈጸሙ ግድያዎች ከመንግስት ሰራዊት በተጨማሪ ስለሌሎች የታጠቁ አካላት ጥቃት የፓርቲው አቋም ምን ይሆን የሚል ጥያቄ አቅርበንላቸው፤ “በስልጣን ላይ ከለው መንግስት በተሻለ የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት አካል ባለመኖሩ በተጠያቂነት የምንጠቅሰው መንግስት ነው” ሲሉ መልሰዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከሰሞኑ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ላይ «ሰላም! ሰላም! ሰላም!» ብለው ባሰራጩት ዘለግ ያለ ጽሁፍ ላይ መንግስታቸው በክልላቸው ያለውን የጸጥታ ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት ጥረት መደረጉን ገልጸዋልምስል Seyoum Getu /DW

የመንግስት የሰላም ጥሪ

ዶይቼ ቬለ በዞኑ ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት እና አሁናዊ ይዞታውን በማስመልከት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ለዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኃይሉ ጀልዴ ስደውል፤ ኃላፊው በያከባቢው የሰላማዊ ዜጎች ጥቃቱ መኖሩን አረጋግጠው አሁን ላይ ለስራ ሌላ ቦታ በመሆናቸው ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ለምስተዋለው አለመረጋጋት ከዚህ ቀደም መንግስት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረጉን አስታውቆ ሂደቱ ግን በተደጋጋሚ መክሸፉ መገለጹ ይታወሳል፡፡

ይህንኑን መነሻ በማድረግ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከሰሞኑ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ላይ ሰላም! ሰላም! ሰላም! ብለው ባሰራጩት ዘለግ ያለ ጽሁፍ ላይ መንግስታቸው በክልላቸው ያለውን የጸጥታ ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት ጥረት መደረጉን አስታውሰው፤ “በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ ስተበተቡ ነበሩ” ባሏቸው “ሸፍጥ” መደናቀፉን ጠቁመዋል፡፡

ቄሌም ወለጋ በፀጥታ ችግር የሰዎች ሕይወት እየጠፋ ነው

አቶ ሽመልስ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው በጻፉት በዚሁ ጽሁፍ “በራችን ለሰላም ክፍት ነው” ብለው አሁንም መንግስታቸው ከህዝብ እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተማክሮ

የሰላም ጥሪን በማሳለፍ ሰፊ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በዚህም በቀረበው ጥሪ መሰረት በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን አውርደው እየተመለሱ ነው ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ “የኦሮሞ ህዝብ ከጦርነት እንደማያተፍ” ገልጸው፤ ልዩነቶች በውይይት እንዲቋጩ በማለት ጥሪ አሰምተዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ 
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ