1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእቅስቃሴ ገደብ በኦሮሚያ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2016

በትውልድ ቀዬያቸው መቂ የተገደሉት የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ ክልል በህቡዕ ተላልፏል የተባለውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ገደብ ጥሪን ተከትሎ አንዳንድ አከባቢዎች ላይ የትራንስፖርት ፍሰት መስተረጓጎል ሲያጋጥም በሌሎች አከባቢዎች ደግሞ እንቅስቃሴው በመደበኛ ሁኔታ ስለመቀጠሉ ተገለፀ፡፡

https://p.dw.com/p/4enJJ
የእቅስቃሴ ገደብ በኦሮሚያ
የእቅስቃሴ ገደብ በኦሮሚያምስል Seyoum Getu/DW

የእቅስቃሴ ገደብ በኦሮሚያ

የእቅስቃሴ ገደብ በኦሮሚያ

ባለፈው ሳምንት በትውልድ ቀዬያቸው መቂ የተገደሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ ክልል በህቡዕ ተላልፏል የተባለውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ገደብ ጥሪን ተከትሎ አንዳንድ አከባቢዎች ላይ የትራንስፖርት ፍሰት መስተረጓጎል ሲያጋጥም በሌሎች አከባቢዎች ደግሞ እንቅስቃሴው በመደበኛ ሁኔታ ስለመቀጠሉ ተገልጿል፡፡

ከባለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 05 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በውል ከማይታወቅ አካል ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል በተባለው በዚህ ጥሪ መሰረት ከከተሞች ወደ ከተሞች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ መጠየቁን ማህበረሰቡ በስጋት ያነሳዋል፡፡ መሰል የእንቅስቃሴ ገደቦች እስካሁንም በኑሮ ውድነት፣ በግጭት እና ስራ አጥነት የተፈተነውን የማህበረሰቡን ህይወት ይብልጥ እንደምፈትንም እየተገለጸ ነው፡፡

የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ስጋቶቹ

ከሰሞኑ ወደ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ አቅንተው የነበሩና በዛሬው እለትም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ እቅድ እንደነበራቸው የገለጹልን አንድ አስተያየት ሰጪ እንደወትሮው በጠዋት ወደ መናኸሪያ ብሄዱም የምሳፈሩት ትራንስፖርት ማጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዋ ህብረተሰቡና የተሽከርካሪ ባለንብረቶችን በዚሁ ስጋት ገብቶአቸዋል፡፡ “ጠዋት አንድ መኪና ውስጥ  ገብተን ለመንቀሳቀስ ብናስብም አሽከርካሪው በስጋት አልሄድም ብሎ ስላስወረደን መሄድ አልቻልንም፡፡ ከዚያ በኋላ ግን አሁን ከረፋድ አራት ሰዓት በኋላ መኪኖች ሰው ጭነው መውጣት ጀምረዋል የሚል ነገር ሰምቻለሁ፡፡ ብታይ ስጋት አለ፤ ሰው በጊዜው ነው ወደ ቤት የሚገባው፡፡ እንደወትሮው ባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎችም በጠዋት ስወጡ አይስተዋልም” ብለዋል፡፡

አቶ በቴ ኡርጌሳ፤ በትውልድ ቀዬያቸው መቂ የተገደሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር
አቶ በቴ ኡርጌሳ፤ በትውልድ ቀዬያቸው መቂ የተገደሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር ምስል Private

መደበኛ ስጋት የሚስተዋልባቸው መስመሮች

ትናንት ማምሻውን ከአዲስ አበባ ወደ ሃዋሳ በሞጆ፣ ባቱ እና ሻሸመኔ በኩል በርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችን አቆራርጠው ወደ ሃዋሳ ለስራ ያቀኑት ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ በዚህ መስመር ከመደበኛ ጋር የተጠጋ የትራንስፖርት ፍሰት ማስተዋላቸውን አንስተዋል፡፡ “መንገድ አንግዲህ አንዳንዶቹ ክፍት ነው ይላሉ አንዳንዶቹ ግን እንደወትሮ አይደለም ይላሉ፡፡ እኔ ግን ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ ሃዋሳ ስመጣ ምንም ያስተዋልኩት ችግር የለም፡፡ በመደበኛ እንቅስቃሴ ነው የመጣሁት፡፡ አሁን ዛሬም ከሻሸመኔ ወደ አዳማ የሄዱ ጓደኞቼ ነበሩ መቂ ላይ ካለው መጠነኛ ስጋት ውጪ በሰላም ገብተዋል” ብለዋል፡፡

ሌላው በትናንትናው እለት ከሀዋሳ በዚሁ ተመሳሳይ መስመር ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ አስተያየት ሰጪም የተለመደው የትራንስፖርት ፍሰት ማስተዋላቸውን ገልጸው፤ ከትናንሽ የግል ተሽከርካሪዎች እስከ ትላልቅ የህዝብ ማመላለሻ ባሶች እና የጭነት ተሽከርካሪዎች ስጓዙ መመልከታቸውን አስረድተዋል፡፡ “እኛ በመጣንበት ከሃዋሳ ወደ ባቱ በዚያም በፍጥነት መንገድ በኩል ምንም አላየንም፡፡ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ነው አዲስ አበባ የገባነው፡፡ ትላልቅ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ጨምሮ ሁሉም ስሄድ ተመልክተናል” ነው ያሉት፡፡

ጥሪው ቀርቧል ከተባለበት ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እስከዛሬ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ወዳሉ ከተሞችም መደበኛ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ስደረግ ሰንብቷል፡፡ ከዚህም መስመር አልፎ ከአዳማ ወደ አሰላ እና ከአሰላ ወደ በቆጂ ያለውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ይዞታ የጠየቅናቸው አንድ የበቆጂ ከተማ ነዋሪ እንዳሉት፡ “ባለፈው ሳምንት አከባቢ በነዳጅ እጥረት ነው በሚል ከተስተጓጎለው መደበኛ ፍሰት ውጪ ባሁኑ ዛሬንም ጨምሮ ትራንስፖርት በመደበኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ነው” ይላሉ፡፡

መስተጓጉሉ አጋጥሟል የተባለባቸው አከባቢዎች

ከምዕራብ ኦሮሚያ ነቀምቴ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ ደግሞ “ከተማ ውስጥ የባጃጅ እንቅስቃሴ አለ መደበኛ ነው፡፡ ምንም ከተለመደ ውጪ የሆነ ነገር የለም፡፡ ግን ከከተማ ወደ ከተማ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁን ምዕራብ ወለጋ ባለሚ በምትባል ከተማ መኪና ስለመቃጠል ሰምተናል” ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ተነስተው በሲሚንቶ ግብዓቶቿ ወደ ምትታወቀው የምዕራብ ሸዋ ዞን አደዓ በርጋ የምንቀሳቀሱ ከባድ ተሽከርካሪዎች እንደወትሮ መንገድ ላይ ባይታዩና የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርትም መንገድ ላይ በዝተው እንደወትሮ ባይስተዋሉም መንገድ ግን ክፍት ነው ይላሉ፡፡ “መንገድ ክፍት ነው ዛሬ ነው ወደ እንጭኒ ከተማ የመጣሁት፡፡ ግን እንደ ወትሮ አይደለም፡፡ ይህን የትራንስፖርት ገደብ ስባል እንጂ ማን እንደሚጠራው አናውቅም፡፡ አሁን ዛሬ በተለይ ከተለመደው እንቅስቃሴው ቀንሷል” ነው ያሉት፡፡

የእቅስቃሴ ገደብ በኦሮሚያ
የእቅስቃሴ ገደብ በኦሮሚያምስል Seyoum Getu/DW

ከዚሁ አከባቢ ሌላው በሹፍርና የምተዳደሩ አስተያየት ሰጪ ሃሳባቸውን አከሉ፡ “ዝግ ነው መንገድ ክፍት ነው ማለት ያስቸግራል፡፡ ሰው መናኸሪያ ላይ ስጠራቀም በግዳጅ ነው እንጂ ጭነህ የምትወጣው እንደ ወትሮ እየዞርክ ጠርተህ ቀስቅሰህ አትወጣም፡፡ ብዙ ሰው የግዳጇን ብቻ እየጫነ ነው ገብቶ የምተኛው፡፡ ህዝብ ተጠራቅሞ መኪና ስያጣ እንድንጭን ታዘን አንጭንም ብንል መንግስት ይቀጣናል፡፡ ከዚህ ወደ አምቦም አንዳንድ ካልሆነ እደወትሮው በቂ ትራንስፖርት መንገድ ላይ አይስተዋልም፡፡ ኑሮ እየሰራንም ከብዶናል እንዲህማ እንዴት እንደምዘልቀው አላውቅም” ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተውናል፡፡

ተጠርቷል ስለተባለው የእንቅስቃሴ ገደብና አልፎ አልፎ ተስተጓጉሏል ስለተባለው የእንቅስቃሴ ሁኔታ የክልሉ መንግስት ለው ነገር የለም፡፡ ለክልሉ ኮሚውኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ደውለን አስተያየታቸው ለማከል ያደረግነው ጥረትም ለዛሬ አልሰመረም፡፡

 

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ