1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ድርድር እንደቀጠለ መሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

ሐሙስ፣ ኅዳር 6 2016

መንግሥት ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ የሚያደርገው ድርድር እንደቀጠለ መሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የታጣቂ ቡድኑ አዛዥ ማሮ ድሪባ እና ምክትላቸው ገመቹ አቦዬ በታንዛኒያው “የሰላም ውይይት” በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ኦነሠ አረጋግጧል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ ስለ ንግግሩ ዝርዝር ነገር ከመናገር ተቆጥበዋል

https://p.dw.com/p/4Ysd1
አምባሳደር መለስ ዓለም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በመንግሥት እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ መካከል የሚደረገው ውይይት እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል። ምስል Solomon Muchie/DW

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ

ከመንግሥት ጋር ለአመታት የትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚገኘውና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ የፈረጀው ኦነግ ሸኔ የተባለው ታጣቂ ቡድን ከ6 ወራት በፊት ከመንግሥት ጋር በታንዛኒያ አድርጎት ይነበረው የድርድር ጥረት ያለ ሁነኛ ስምምነት መጠናቀቁ ተገልጾ ቆይቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ አለም ስለ ጉዳዩ ዝርዝር ነገር ባይገልፁም የመንግሥት እና የቡድኑ ሁለተኛ ዙር ድርድር በታንዛኒያ እየቀጠለ መሆኑን ዛሬ ተናግረዋል። "የመጀመርያው ዙር ከሸኔ ጋር የተደረገ ውይይት ነበር። ሁለተኛ ዙር አሁንም ቀጥሏል። እየተካሄደ ነው የሚገኘው" ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ለሁለተኛ ጊዜ እየተደረገ የሚገኘው ውይይት ሰላም ለማውረድ ይረዳል የሚል ተስፋ አላቸው። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ታዛቢዎች በሁለተኛው ዙር ውይይት ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላቸው ተወካዮች መሳተፍ አዎንታዊ ምልክት አድርገው ቆጥረውታል።

የኢትዮጵያ እና የሱዳን መሪዎች ንግግር 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ "በቁልፍ ወቅታዊ ጉዳዮች ለመምከር" ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ያሏቸውን የሱዳን ሪፐብሊክ ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃንን ትናንት መቀበላቸውን ገልፀው ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም አልቡርሃን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር "ጠቃሚ እና ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል" 

ነሐሴ ላይ በሳውዲ የመን ድንበር ላይ ኢትዮጵያውያን ስለመገደላቸው ሂውማን ራይትስ ዎች ያወጣው መግለጫ ተጠቅሶ ጉዳዩ ምን ደረጃ ላይ ደረሰ በሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበሩት ቀል ዐቀባዩ "ከሳውዲ መንግሥት ጋር እየሠራንበት ነው" ብለዋል። 
የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን ቅርንጫፍ ስለመዝጋቱም መረጃዎች መኖራቸው ተገልጾ ተጠይቀው ነበር። "የተዘጋ ጽህፈት ቤት የለም" ብለዋል።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ