1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አቋም

ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2016

የገንዘብ ሚንሰትር አቶ አህመድ ሺዴን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት ሰሞኑን ከዓለም ባንክ (WB) እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF) ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በዩናይትድ ስቴትስ ተወያይተዋል።

https://p.dw.com/p/4f3RI
የኢትዮጵያ ብር
አንድ የፋይናንስና የኢኮኖሚ አማካሪ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት "አሁን ባለንበት ሁኔታ የብርን የመግዛት አቅም ካዳከምን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል" ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አቋም

ባለሥልጣናቱ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታና የወደፊት ተስፋ፣ እንዲሁም ሀገሪቱ ስለጀመረችው የኢኮኖሚ ሪፎርም መወያየታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከጠየቀችው የብድር አቅርቦት ጋር በተገናኘ አሁንም ልዩነቶች መኖራቸው በተቋሙ ድረ ገጽ ላይ ተጠቅሷል።

በዚህ መሃል ሰሞኑን መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፤ መንግሥት ብድር ለማግኘት በሚል በዚህ ተቋም ግፊት የብርን የመግዛት አቅም የማዳከም ስምምነት እንዳይቀበል ጠይቋል። ኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ እፎይታዋን ለማዳን የአይኤምኤፍ ባለሙያዎችን የአዲስ አበባ ጉብኝት ውጤት ትጠባበቃለች


በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ያጋሩን አንድ የፋይናንስና የኢኮኖሚ አማካሪ በበኩላቸው የዋጋ ግሽበትን ይበልጥ እንደሚያባብስ በመግለጽ "አሁን ባለንበት ሁኔታ የብርን የመግዛት አቅም ካዳከምን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና የገንዘብ ተቋማት የውይይት አጀንዳዎች

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታና የወደፊት ተስፋ፣ መንግሥት የጀመረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፣ ምርታማነት እና ሌሎች ጉዳዮች የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከአለም ባንክ እና አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ኃላፊዎች ጋር የተወያዩባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። 

የፋይናንስና የኢኮኖሚ አማካሪና መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ታደሰ ሁለቱ አካላት ሰፋ ባሉ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ለውይይት እንደሚቀመጡ ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ብር
የኢትዮጵያ ብርምስል Eshete Bekele/DW

መንግሥት የፈለገው የብድር መጠን

የኢትዮጵያ መንግሥት ከ አይ ኤም ኤፍ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ጠይቋል። በዚህ ዙሪያ በሁለቱ አካላት መካከል ልዩነቶች መኖራቸው ተገልጿል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ኢዜማ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ "የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ከሚያስገኘው ታሳቢ ጥቅም ይልቅ በዜጎች የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያመጣ ይችላል" ብሏል። ፓርቲው መፍትሔ ያለው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱ የገበያውን ፍላጎት በሚያረካ መልኩ እንዲጨምር ማድረግን ነው።

የፋይናንስና የኢኮኖሚ አማካሪና መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ታደሰእንደሚሉት አሁን የብርን የመግዛት አቅም የማዳከሚያ ጊዜው አይደለም። የኢትዮጵያ መንግሥት ብድሩን በማግኘት እና የገንዘብን የመግዛት አቅም በማዳከም ምርጫ ውስጥ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው እዚህ ላይ ግን "በደንብ ማሰብ ይጠይቃል" ብለዋል። 

የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት የኢትዮጵያ ጉብኝት

ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የውጭ ምንዛሪ ክምችቷ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። መንግሥት አሁን እያደረገ ካለው ውይይት ጋር በተያያዘ የብርን የመግዛት አቅም የማዳከም እርምጃ የመውሰድ እቅድ ይኑረው አይኑረው በግልጽ የተባለ ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ዓመት ሕዳር መጀመርያ ላይ "በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ" ማቀዱን የተመለከቱ ዘገባዎች መውጣታቸውን በመጥቀስ መረጃዎቹ "ሀሰተኛ እና አሳሳች" ናቸው ማለቱ ይታወሳል።

ሰለሞን ሙጬ
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ