1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካን ምርጫ ጀርመንና የአውሮጳ ኅብረት  

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 24 2013

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን እንዲያስተዳድሩ የሚፈልጉት 13 በመቶ ጀርመናውያን ብቻ ናቸው።አብዛኛዎቹም «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው የጀርመን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው።2/3 ኛዎቹ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ይፈልጋሉ።የአውሮጳ ኅብረት ጆ ባይደን ከተመረጡ የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ግንኙነት ተስፋ ይኖረዋል የሚል እምነት አለው።

https://p.dw.com/p/3kodC
UK NATO-Treffen in London l Angela Merkel und Donald Trump
ምስል picture-alliance/empics/PA Wire/S. Parsons

የአሜሪካን ምርጫ ጀርመንና የአውሮጳ ኅብረት  

መላው ዓለም በቅርበት የሚከታተለው የዛሬው የአሜሪካን ምርጫ በጀርመን ብሎም በአውሮጳውያን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።በአራቱ ዓመት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዘመነ ሥልጣን፣ የተበላሸው የአሜሪካና የጀርመን እንዲሁም የአሜሪካንና የአውሮጳ ግንኙነት በዚህ ምርጫ መፍትሄ ያገኛል የሚል ተስፋ አለ።የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን፣ጀርመኖችና የአውሮጳ ኅብረት ከዛሬው ምርጫ ምን እንደሚፈልጉና እንደሚጠብቁ ያስቃኘናል። ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች።

አሜሪካን ለበርካታ ጀርመናውያን የተስፋይቱ ምድር  ነበረች።ከጎርጎሮሳዊው 1820 እስከ የአንድኛው የዓለም ጦርነት እስከ 1914 በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድሀ ጀርመናውያን  የተሻለ ሕይወት ፍለጋ የአትላንቲክ ውቅያኖስን  ተሻግረው ወደ አሜሪካን ተሰደዋል። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ደግሞ ናዚ ጀርመንን ድል ካደረጉት ተጓዳኝ ኃይሎች አንዷ ዩናይትድ ስቴትስ ፣የነጻነት የብልጽግና እና የእድገት ተምሳሌት ሆና የምትታይ፤ በ1990ዎቹ ደግሞ የጀርመንን ውህደት ያመቻቸች ሃገር ናት።አሁን ግን የጀርመንና የዩናይድ ስቴትስ ወዳጅነት እንደ ከዚህ ቀደሙ አይደለም። ቀዝቅዟል።በአራቱ ዓመት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት የዶናልድ ትራምፕ ዘመነ መንግሥት የሁለቱ ሃገራት ወዳጅነት ተበላሽቷል።በዚህ ምክንያት አብዛኛዎቹ ጀርመናውያን የዛሬውን የአሜሪካን ምርጫ የዴሞክራቶቹ እጩ ጆ ባይደን እንዲያሸንፉ ነው የሚመኙት።ድሉ የባይደን ከሆነ የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ አጋርነት ቀድሞ ወደነበረበት ይመለሳል የሚል ተስፋ አለ።በትራምፕ አስተዳደር ይህ ትብብር ለምን ቀዘቀዘ?ተብለው  የተጠየቁት የትብብሩ የጀርመን ወገን አስተባባሪና በጀርመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የክርስቲያን ዴሞክራቶች ሕብረት ፓርቲ ተወካይ ፔተር ባየር መልስ ለመስጠት ብዙም ማሰብ አላስፈለጋቸውም።ባየር ግንኙነቱ መበላሸት የጀመረው በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2018 መሆኑን ባየርያስታውሳሉ።
«ዶናልድ ትራምፕ አውሮጳውያንን እንደ ጠላት ሲፈረጁ በቀላሉ መስመሩን ጣሱ።እነዚህን ቃላት፣ አይደለም ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ፤ከማንም መስማት የምትፈልጋቸው አይደሉም።»
ይህ ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ ስለ አውሮጳ ጀርመንንና የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ምን እንደሚያስቡ ብዙ ጊዜ  ከተናገሩት አንዱ ነው። ባየር ባለፉት አራት የትራምፕ የሥልጣን ዓመታት የዋሽንግተንና የበርሊን ግንኙነት በብዙ መልኩ ተቀይሯል ይላሉ።
«ለውጡ በሁለቱ ወገኖች ግንኙነት አካሄድ ጭምርም ላይ ነው።እንደ ከዚህ ቀደሙ የምንወያይበት መድረክ ባለመኖሩ አዳዲስ የግንኙነት መንገዶችን መልመድ ነበረብን።ጀርመን የሚገኙ የአሜሪካን ወታደሮች ቁጥር ቅነሳን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን።ይህን ያወቅነው ዎል ስትሪት በተባለው ጋዜጣ ላይ ከወጣ ጽሁፍ ነው።ከዚያ በኋላ ለአንድ ሳምንት ዝም አልን።»                                                                                                                                                                                                                             የዶናልድ ትራምፕና የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ግንኙነትም ተሸርሽሯል። የቤት አሰሪና ሻጭ Real State ባለቤቱ ፣ዶናልድ ትራምፕ እና የፊዚክስ ምሁሯ ሜርክል ባህርይ የተለያየ ነው።ሜርክል ለስላሳ ተናጋሪ ናቸው ፤ትራምፕ ደግሞ ይጮሃሉ።በፖለቲካውም ቢሆን ልዩነታቸው የት የለሌ ነው።የተፈጥሮ ጥበቃም ይሁን የዓለም የንግድ ድርጅት ጉዳይ፣የስደተኞች መርህ ወይም ደግሞ የቅርብ ጊዜው ክስተት የኮሮና ቀውስ ላይ የሚከተሉት ፖሊሲ ፈጽሞ  አይገናኝም።የበርሊን ባለሥልጣናት አንዳንዴ በዋሽንግተን የመንግሥት ለውጥ እንዲደረግ ይመኙ ነበር።ይህ የፖለቲከኞች ምኞት ብቻ አይደለም።ሲቪዪ የተባለው በምርጫ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ አመለካከትን የሚያጠናው ተቋም ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን እንዲያስተዳድሩ የሚፈልጉት 13 በመቶ ጀርመናውያን ብቻ ናቸው።አብዛኛዎቹም «አማራጭ ለጀርመን» የተባለው የጀርመን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው። ከሁለት ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት የዚህ ፓርቲ ደጋፊዎች ፣ትራምፕ እንዲያሸንፉ ይፈልጋሉ ። ከአጠቃላዩ ህዝብ በቁጥር አናሳ ናቸው። የብዙዎቹ ጀርመናውያን ተስፋ ግን ጆን ባይደን ናቸው።ባይደን ባለፉት ጊዜያት የአውሮጳ አጋሮች ለኛ አስፈላጊ አጋሮች ናቸው በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር።ባይደን በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ትብብር ላይ እንጂ በብሔረተኛ ጉዳዮች ላይ እምብዛም አያተኩሩም ይባላል።ሆኖም ባየር እንዳሉት ባይደን ጀርመኖች ከእስከአሁኑ የበለጠ ሃላፊነት እንዲወስዱ መጠየቃቸው አይቀሬ ነው።ትራምፕ እንደሚፈልጉት ሁሉ ባይደንም ጀርመን ለመከላከያ ተጨማሪ ገንዘብ እንድታዋጣ ይጠብቃሉ።በጀርመን ምክር ቤት የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ የአውሮጳ ፖሊሲ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ፍራንሲስካ ብራንትነርም ተመሳሳይ አስተያየት ነው የሰጡት።
«በሚቀርቡን ጎረቤቶቻችን መካከል የሚካሄደው ግጭት የአውሮጳውያን ግጭት ነው።የዴሞክራቶች እጩ ቢመረጥም እንኳን ለወደፊቱ እኛ ራሳችን ሃላፊነት መውሰድ አለብን። ይህን ለመወጣትም በስተመጨረሻ የጀርመንን የውጭ መርህ ከአውሮጳ ፍላጎት ጋራ ማጣጣም አለብን። እንደ ጀርመንና እንደ አውሮጳ የመደራደር አቅም እንዲኖረን የአውሮጳን አብሮነት ማስቀደም አለብን።»
ትራምፕ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን የሚመረጡ ከሆነ ይህ ጉዳይ ችላ መባል የለበትም ይላሉ ብራንትነር። ድሉ የባይደን ከሆነ ደግሞ ፣ለብራንተር ፣ትራምፕ ሃገራቸው ለቃ እንድትወጣ ያደረጉትን የፓሪሱ የአካባቢ ጥበቃ ስምምነት ዳግም የመጠናከሩ ተስፋ አለ።በአውሮጳ ኅብረት በኩልም ጆ ባይደን ከተመረጡ የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ግንኙነት ተስፋ ይኖረዋል የሚል እምነት አለ።የአውሮጳ የፖሊሲ ማዕከል የተባለው የጥናት ተቋም ሃላፊ ያሪስ ኢማኑዊሊዲስ ባይደን ካልተሳካላቸው እና ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ከተመረጡ የዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ ግንኙነት ይበልጡን እየተበላሸ መሄዱ አይቀርም ይላሉ።
«ከመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በተለየ በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው በአውሮጳ ላይ ይበልጥ ጫና ማድረጋቸው አይቀርም።አውሮጳን ከሌሎቹ የዓለም ክፍሎች የባሰ እኩይ አድርገው ነበር የሚገልጿት። ባለፉት አራት ዓመታት በአደባባይ ከተናገሯቸው ብዙ ነገሮች መካከል ይህ አንዱ ነው።»
የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ አባልና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ባለሞያ ራይንሃርድ ቡቲኮፈር እንደሚሉት ደግሞ ትራምፕ የአውሮጳ ኅብረትን እንደ አጋር ሳይሆን እንደ ተቀናቃኝ ማየታቸው ለዋሽንግተን የሚሰጠው ጥቅም አይኖርም።በርሳቸው አባባል ትራምፕ ግንኙነቱን ቢያሰናክሉም አሁንም ቢሆን ከአውሮጳ ጋር መተባበሩ ከቻይና ከሩስያና ከሌሎች ጋር ያሉ ውዝግቦችን ለመፍታት አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑ በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥትና በኮንግረሱ ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞች ሪፐብሊካኖችንም ጭምር አሉ።ጆ ባይደን ሁሉንም ነገር በተለየ መንገድ ያካሂዳሉ ማለት አይደለም የሚሉት ቡቲኮፈር ሆኖም በነባር ወዳጆቻቸው ላይ እምነት መጣላቸው፣ እነርሱንም ማዳመጣቸውና የጋራ መግባቢያ መሠረት መፈለጋቸው እንደማይቀርም ይገምታሉ።
«ማንም ያሸንፍ ማን ውጤቱም ምንም ይሁን ምን ትብብሩ ላይ ይበልጥ መሥራት አለብን።በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ወደፊት ተራምደናል።ለምሳሌ የዓለም የንግድ ድርጅትን በሚመለከት ድርጅቱ በሚገዛባቸው ደንቦች ላይ ተሃድሶ የማድረጉ አስፈላጊነት በዚህ ረገድ ይጠቀሳል።እንደሚመስለኝ ሁላችንም አሁንም በአንድ ዓይነት መንገድ መጓዝ እንችላለን።»
የአውሮጳ ኅብረት የመሪዎች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ክፍል በአውሮጳውያኑ የበጋ ወራት ያካሄደው ጥናት እንደዳሳየው አውሮጳውያን ከዚህ ቀደም የቅርብ አጋራቸው በነበረችው በዩናይትድ ስቴትስ ላይ የነበራቸው እምነት ጠፍቷል።በተለይ ትራምፕ ለኮሮና ወረርሽኝ ቀውስ የተከተሉት የተመሰቃቀለ አመራር ይበልጡን ሸርሽሮታል።የህብረቱ ምክር ቤት ተመራማሪዎች  ባይደን ቢመረጡ ወደ አውሮጶች ይመጣሉ ብለው ነው የሚገምቱት።ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ፓሪሱን የአካባቢ ጥበቃ ስምምነት እንዲሁም ወደ ዓለም ጤና ድርጅት አባልነት ትመለሰላቸው ብለውም ተስፋ ያደርጋሉ።ዴሞክራቶችም ሆኑ ሪፐብሊካኖች የአውሮጳውያን የመከላከያ በጀት እንዲጨምር ግፊት ማድረጋቸው ባይቀርም፣የባይደን መንግሥት የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት የNATOን ማኅበር ያጠናክራል የሚል ተስፋ ጥለውበታል።የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እንደ ቀዳሚዎቹ  ሬዝዳንቶች ሁሉ አውሮጳውያን ወታደራዊው በጀት እንዲጨምር ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።የቀድሞ የትራምፕ የፀጥታ አማካሪ ጆን ቦልተን እንዳስጠነቀቁት ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ከተመረጡ በርሳቸው አባባል ኔቶ «ካፖርቱን ደርቦ መጠበቅ» ወይም ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል።አለበለዚያ ኔቶን ለቀው እስከመውጣት የዛቱት ትራምፕ ያሉትን ካደረጉ በቦልተን ግምት ይህ የኔቶ መጨረሻ መሆኑ አይቀርም። አሁን የብራሰልስ ተስፋ ጆ ባይደን ናቸው።ሆኖም የአውሮጳፖሊሲ ጥናት ተቋሙ ኢማኑዊሊዲስ እንደሚሉት፣ ብራሰልስ ከባይደን በኩልም ቢሆን ተግዳሮቶች ሊገጥሙት ይችላሉ።
«አንዱ ተግዳሮት ለምሳሌ አዲሱ የባይደን አስተዳደር በጋራ ጉዳዮች ላይ ልንተባበር እንችላለን በአየር ንብረት ለውጥ እንተባበራለን በዓለም የንግድ ድርጅት ጉዳይም እንተባበራለን ካለ በኋላ ፣እናንተ ደግሞ በፈንታችሁ ለምሳሌ በቻይና ላይ ጠንካራ አቋም እንዲኖራችሁ እንፈልጋለን ብለው ሊጠይቋቸው ይችላሉ።»
የዩናይትድ ስቴትስን ምርጫ ማንም ያሸንፍ ማንም አውሮጶች  በንግድ ግንኑነቶቻቸውን ላይ አስቸኳይ ንግግር መጀመር ይፈልጋሉ።ትራምፕ ከአውሮጳ ወደ አሜሪካ በሚላኩ መኪናዎችና ሌሎች ምርቶች ላይ  እጥላለሁ ያሉት ከፍተኛ ታክስ ጉዳይ አሁንም በእንጥልጥል እንዳለ ነው። እስካሁን ከአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት የተወሰኑት ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ጠቃሚ በሚባል ግንኙነት የቀጠሉ ቢሆንም፣ማንም ቢመረጥ ማን በስተመጨረሻ የአውሮጳ ኅብረት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ጥቅሙን ለማስጠበቅ በጋራ መቆሙ እንደማይቀር ነው የአውሮጳ የፖሊሲ ጥናት ተቋም ሃላፊው ኢማኑዊሊዲስ ያስረዱት። እንግዲህ ዛሬ ለሊት ይፋ የሚደረገው የምርጫ ውጤት ሁሉንም የሚወስን ይሆናል። 
ኂሩት መለሰ

USA Washington Jean-Claude Juncker, Präsident EU-Kommission & Donald Trump
ምስል Reuters/J. Roberts
Deutschland Berlin | Kanzleramt  | Merkel und Biden
ምስል Maurizio Gambarini/dpa/picture alliance
Weltwirtschaftsforum 2020 in Davos | Ursula von der Leyern & Donald Trump
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Vucci
Deutschland | Madame Tussauds | Angela Merkel mit roter Nelke
ምስል picture-alliance/dpa/J. Kalaene