1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች ማስተማር ሊጀምሩ ነዉ

ሐሙስ፣ ጥር 2 2016

ዩኒቨርስቱዎቹ ተማሪዎችን እንደሚቀበሉ ያስታወቁት የፌደራሉ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን እንዲቀበሉ ከወሰነ በኋላ ነዉ።ወላጆች የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ትምህርት ለመጀመር አያስችልም የሚል ስጋት ያደረባቸው ሲሆን አንዳንድ ተማሪዎች ደግሞ ወደየዩኒቨርቲያቸው ለመሄድ ግራ እንደተጋቡ አስታዉቀዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4b8Cd
ትምሕርት ሚንስቴር የአማራ ዩኒቨርስቲዎች ትምሕርት እንዲጀምሩ ወስኗል
የኢትዮጵያ ፈደራላዊ መንግስት የትምሕርት ሚንስቴር ሕንፃ-አዲስ አበባምስል Alemnew Mekonnen/DW

የአማራ ዩኒቨርስቲዎች ትምሕርት እንደሚጀምሩ አስታወቁ

በአማራ ክልል በሚደረገዉ ዉጊያ ምክንያት ለተከታታይ ወራት ትምሕርት አቋርጠዉ የነበሩ የክልሉ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸዉ ወደየትምሕርት ገበታቸዉ እንዲመለሱ ጥሪ አድርገዋል።ዩኒቨርስቱዎቹ ተማሪዎችን እንደሚቀበሉ ያስታወቁት የፌደራሉ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን እንዲቀበሉ ከወሰነ በኋላ ነዉ።ወላጆች የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ትምህርት ለመጀመር አያስችልም የሚል ስጋት ያደረባቸው ሲሆን አንዳንድ ተማሪዎች ደግሞ ወደየዩኒቨርቲያቸው ለመሄድ ግራ እንደተጋቡ አስታዉቀዋል፡፡

በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንት በክልሉ የሚገኙ 10ሩም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪወቻቸውን በወቅቱ ሳይጠሩ ቆይተዋል፡ታህሳስ 18/2016 ዓ ም የትምህርት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ከተወያየ በኋላ ባወጣው መግለጫ

“ ... አሁን በክልሉ አንፃራዊ ሰላም የተፈጠረ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ከጥር 1 ጀምሮ ባሉ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ተማሪዎችን መጥራትና ማስተማር እንዲችሉ ውሳኔ ላይ ተደርሷል” ብሏል፡፡

ይህን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎቻቸው ጥሪ እያደረጉ ነው፡፡ ጥሪ ካስተላለፉ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የኢንጅባራ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ይርጋ ታደሰ ይህን አረጋግጠውልናል፡፡

ለተከታታይ ወራት ትምሕርት ያቋረጡት የአማራ ዩኒቨርስቲዎች ትምሕርት ለመጀመር ለተማሪዎቻቸዉ ጥሪ እያደረጉ ነዉ
የወሎ ዩኒቨርስቲ ዋና ግቢ-ደሴምስል Gonder & Wello University

 

“ያለው  አገርአቀፍ ወቅታዊ ሁኔታ የሚታወቅ ነው፣ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ከመጡ በኋላ ችግር እንዳደርስባቸው ከሚመለከተው የፀጥታ አካል ጋር በቅንጅት በመስራት ደህንነታቸው ተጠብቆ አስፈላጊውን ትምህርት እንዲያገኙ ጥረት ይደረጋል፣ የፌደራል መንግስቱ ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር ሰላም እንዲሆን፣ ያንንም ለማስጠበቅ እንደሚሰራ እርግጠኛ ሆኖ ነው ያሳወቀን፣ አሁንም ቢሆን ኃላፊነት ወስዶ ተማሪዎችን በተመለከተ ችግር እንዳይፈጠር ጠንክሮ ይሰራል ብለን እናምናለን” ነው ያሉት፡፡

የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ለተማሪዎች ጥሪ ማድረጉን ቢገልፅም ዝርዝር ጉዳዩን ለመናገር አልፈለገም፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮሙዩኬሽን ኃላፊ ወ/ሮ ይዳኙ ማንደፍሮ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጠዋል፡፡

የተማሪ ወላጆች በበኩላቸው አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ከወላጆች አንዱ፣ “አማራ ክልል ላይ አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ጥሪ ማስተላለፉ እንደኔ ጤናማ ነው ብየ አላስብም፣ አሁን ያለው ሁኔታ ከስጋት የፀዳ አይደለም፣ ሁኔታው በጭራሽ መልካም ሆኖ አይታየኝም፣ ቢጀምሩስ አሁን ትምህርት ሊማሩ ይችላሉ ወይ? ... በሰላምስ ይማራሉ ወይ? የሚል ጥያቄ ነው የሚያስነሳብኝ”

ሌላው ወላጅ ደግሞ የሚከተለውን ብለዋል፣ “መንገድ እየተዘጋ፣ ሰው እየታገተ፣ ግድያ በበዛበት፣(ጥሪው) ትክክል አይደለም፣ ልጄን እኔ ከኔ ጀምሮ እንዴት ነው የምልከው? የትኛው ሰላም ነው ዝርፊያ አይደለ የሚካሄደው፡፡”

ጅማ ከተማ የምትገኘውና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ  ዓመት ተማሪ የሆነችው ተማሪ ማሪያማዊት ማናየ ሁኔታው ብዙ ተማሪዎችን ግራ ያጋባ እንደሆነ አመልክታለች፡፡

የጎንደር ዩኒቨርስቲ የህዝብ ግንኙነት ባለስልጣን ዩኒቨርስቲዉ ትምሕርት |ሥለመጀመር አለመጀመሩ አስተያየት መስጠት አልፈለጉም
ለተከታታይ ወራት ትምሕርት ያቋረጡት የአማራ ዩኒቨርስቲዎች ትምሕርት ለመጀመር ለተማሪዎቻቸዉ ጥሪ እያደረጉ ነዉምስል Gonder & Wello University

“ ... የሚሰማው ነገር ደስ አይልም፣ ግራ ተጋብተን ነው ለነው፣ ደውለን ስናጣራ ምንም ነገር እንደሌለ ይነገረናል፣ በማህበራዊ ሚዲያው የሚሰራጩ ነገሮች ደስ የማይሉ ናቸው፣ በተለይ ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ከባድ ነው፣ እኛ ተመራቂ ስለሆንን አማራጭ የለንም እንሄዳለን” ብላለች፡፡

ሌላ አስተያየት የሰጠን ተማሪ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ቢሆኑም ሲማርበት ወደነበረው ዩኒቨርሲቲ በስጋትም ቢሆን ለመሄድ ተዘጋጅቷል፡፡ማስፈራሪያዎችን በማህበራዊ ሚዲያ እንደሚመለከት የሚገልፀው ይህ ተማሪ ቤተሰቦቹ ፈቃደኛ ባይሆኑም ተመራቂ በመሆኑ አደራውን ሁሉ ለፈጣሪ ሰጥቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደሚመለስ አመልክቷል፡፡

አማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡኝ በተደጋጋሚ ብደውልም ስልካቸው ሊነሳ አልቻለም፣ ሆኑም ታህሳስ መጨረሻ ሳምንት የክልሉን ሰላም በተመለከተ ለመንግስት ብዙሐን መገናኛ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሁን ሁኔታዎች እየተሸሻሉ መሆናቸውን አመልክተዋል፣ መንገዶች እየተከፈቱና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንውስቃሴዎች እየተመለሱ ነውም ብለዋል፡፡

ለተከታታይ ወራት ትምሕርት ያቋረጡት የአማራ ዩኒቨርስቲዎች ትምሕርት ለመጀመር ለተማሪዎቻቸዉ ጥሪ እያደረጉ ነዉ
በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች አንዱ፣ የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ህንፃምስል Alemnew Mekonnen/DW

መንግስት በተደጋጋሚ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ሰላም መስፈኑን ቢያረጋግጥም አሁንም በብዙ ቦታዎች ግጭቶችና የጦርነት ስጋቶች እንዳሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ