1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኔቶ የ75 ዓመት ጉዞና ፈተናዎቹ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2016

ፑቲን ቢቃወሙም ኔቶ መስፋፋቱን በመቀጠል ለቀድሞዎቹ የሶቭየት ኅብረት ግዛቶች ጆርጅያና ዩክሬን የኔቶ አባል እንዲሆኑ ቃል ገባላቸው። ያኔ ግን ፑቲን ስልታቸውን ቀየሩ። በጆርጅያ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የተወሰነውን የጆርጅያ መሬት ያዙ። በ2014 የዩክሬንዋን የክሪምያ ልሳነ ምድር ገነጠሉ።በ2022 ሩስያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ከፈተች።

https://p.dw.com/p/4erHL
የኔቶ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለኔቶን 75 ተኛ ዓመት ኬክ ሲቆርሱ
የኔቶ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለኔቶን 75 ተኛ ዓመት ኬክ ሲቆርሱምስል Kenzo Tribouillard/AFP/Getty Images

የኔቶ የ75 ዓመት ጉዞና ፈተናዎቹ

የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህጻሩ NATO በቅርቡ 75 ተኛ ዓመቱን አክብሯል። ጠላት የሚላቸውን ኮምኒስት ሀገራት የመከላከል ዓላማ ይዞ የተመሰረተው ድርጅቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ አሁን ጥቂት የማይባሉ በምሥራቁ ጎራ የነበሩ አገራትንም አቅፏል። የኔቶ የ75 ዓመት ጉዞና ፈተናዎቹ የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው። 
ከምዕራባውያን ሀገራት ወታደራዊ ኅብረት እድሜ ጠገቡ ድርጅት ብቻ ሳይሆን ከዓለም ብቸኛው ወታደራዊ ኅብረት ነው። የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት NATO በጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 4 ቀን 2024 ዓም 75 ሻማ በማብራት 75ተኛ ዓመቱን አክብሯል። በጎርጎሮሳዊው 1949 ዓ.ም. በ12 አባላት የተመሰረተው ኔቶ ዘንድሮ የፕላቲኒየም እዮቤልዮውን ሲያከብር ሀያ አባላትን ጨምሯል ።ከአባላቱ  30ው የአውሮጳ  ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ናቸው። ከሩስያ ጥቃት ለመዳን ፊንላንድና ስዊድን ኔቶን ባለፈው ዓመት የተቀላቀሉ አባላት ናቸው። ዩክሬንና ጆርጅያም በተመሳሳይ ምክንያት ወደፊት የድርጅቱ አባል ለመሆን ቃል ተገብቶላቸዋል።

የኔቶ ተገዳዳሪ የነበረው የዋርሶ ስምምነት 

ከኮምኒዝም መፈረካከስ በኋላ ነበር ኔቶ ወደ ምሥራቅ አውሮጳ  መስፋፋት የጀመረው ።ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የዋርሶ ስምምነት የተባለው የቀድሞ የምሥራቁ ዓለም ኮምኒስት ሀገራት ወታደራዊ ኅብረት ከተበተነ በኋላ ማለት ነው።የኔቶ ወደ ኖርዲክ ሃገራት መስፋፋት

በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ኔቶ በተመሰረተ በስድስት ዓመቱ ነበር በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት የበላይነት በጎርጎሮሳዊው 1955 በግንቦት ወር የዋርሶ ስምምነት የተመሰረተው ።ኔቶን በኃይል ለመገዳደር ታስቦ የተቋቋመው ድርጅቱ የማዕከላዊና የምሥራቅ አውሮጳ ሀገራትን ያካተተ ነበር።  ይሁንና ሁለቱ ጀርመኖች በጎርጎሮሳዊው 1990 ከተዋሀዱ በኋላ ምሥራቅ ጀርመን ከድርጅቱ ወጣች። ከዚያም በጎርጎሮሳዊው 1991 ሀንጋሪ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ የድርጅቱ ህልውና እንዲያበቃ ተደረገ ። በ1991 የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረትም ተፈረካከሰች። ከዚያ በኋላ ነው የዋርሶ አባል የነበሩት ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ እና ሀንጋሪ በጎርጎሮሳዊው 1999 የኔቶ አባል የሆኑት። ያኔ የኔቶ 50ኛ ዓመት ሲከበር አዎንታዊ ነበር መንፈሱ ።

የኔቶ ወደ ምስራቅ አውሮጳ መስፋፋት 

በወቅቱ ቀዝቃዛ ጦርነት ያበቃለት ነበር የሚመስለው። ሩስያም ያኔ እንደ አጋር ነበር የምትቆጠረው።  በ1997 በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ሞስኮ በውል ደረጃ ኔቶ ወደ ምስራቅ በመስፋፋቱ ተስማማታ ነበር ይላል የዶቼቬለው የቤርንት ሬግይርት ዘገባ ። በዚሁ መሠረትም የቦልቲክ ሀገራቱ ስሎቫክያ፣ ስሎቬንያ ቡልጋርያ እና ሮማንያ በ2004 የኔቶ አባል ሆኑ። በ2009 ደግሞ አልባንያና ክሮኤሽያ ኔቶን ተቀላቀሉ። በዚህ ሳያበቃ በ2017 እና በ2020 ኔቶ በመስፋፋቱ ሂደት ቀጥሎ ከቀድሞዋ የዩጎዝላቪያ ግዛቶች መጀመሪያ ሞንቴኔግሮን ከዚያም ሰሜን መቄዶንያን ኔቶ አባል አደረጋቸው። 

በጎርጎሮሳዊው 1949 ኔቶ ሲመሰረት ያያኔው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሀሪ ትሩማን ፊርማቸውን ሲያኖሩ
በጎርጎሮሳዊው 1949 ኔቶ ሲመሰረት ያያኔው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሀሪ ትሩማን ፊርማቸውን ሲያኖሩ ምስል Everett Collection/picture alliance


በጎርጎሮሳዊው 2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የኔቶን ወደ ምሥራቅ ሀገራት ይበልጥ እየተስፋፋ መሄዱን መተቸት ጀመሩ። ፑቲን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለሁለት ተከፍላ የነበረችው ጀርመን እንደገና በ1990 ስትዋሀድ ኔቶ ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ግዛቶች እንደማይስፋፋ ቃል ተገብቶ ነበር ሲሉ ኔቶን ይተቻሉ። ጀርመን የተማሩትና የሚሰሩት የሕግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ይህ ለሩስያ ና ኔቶ ግንኙነት መሻከር ዐብዩ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ። ይህን የሚመለከት በጽሁፍ የሰፈረ ነገር የለም። ሞስኮ በ1997 የፈረመችው የኔቶና የሩስያ ምስረታ ሕግ ግን እነደዚህ ዓይነት ዋስትና የሚሰጥ አልነበረም። ዶክተር ለማ እንደሚሉት ግን ጽሁፍ ባይኖርም የኔቶ መስፋፋት በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ከሰፈሩት አንዳንድ አንቀጾች ጋር የምጣጣም አልሆነም። 

የፑቲን ተቃውሞና የሩስያ ዩክሬን ጦርነት 

ፑቲን ቢቃወሙም ኔቶ መስፋፋቱን በመቀጠል በ2008 ዓም ለቀድሞዎቹ የሶቭየት ኅብረት ግዛቶች ጆርጅያና ዩክሬን በመርኅ ደረጃ ኔቶን መቀላቀል እንደሚችሉ ቃል ገባላቸው። ያኔ ግን ፑቲን ስልታቸውን ቀየሩ። በጆርጅያ ላይ ጥቃት በመሰንዘር  የተወሰነውን የጆርጅያ መሬት በሩስያ ቁጥጥር ስር አደረጉ። በ2014 ደግሞ የዩክሬንዋን የክሪምያ ልሳነ ምድር ገንጥለው ያዙ።

ዩየኔቶ ምስረታ 75 ተኛ ዓመት
ዩየኔቶ ምስረታ 75 ተኛ ዓመት ምስል Geert Vanden Wijngaert/AP Photo/picture alliance

ከዚያም ምሥራቅ ዩክሬን ለሚንቀሳቀሱ ተገንጣዮች እውቅና ሰጡ። ከ6 ዓመት በኋላ በ2022 በዩክሬን ላይ ጦርነት ከፈተች። ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ሩስያ ይህን ያደረገችበት ምክንያት አላት ይላሉ ። ሩስያ ይህን በማድረጓ ምክንያት ይመስላል ኔቶ ተጨማሪ ሀገራት ወደ ድርጅቱ እንዲገቡ በሩን ክፍት አድርጓል። ኔቶ አሁን የሚገኝበት ሁኔታ የዛሬ 75 ዓመት ዋሽንግተን ውስጥ ሲመሰርት ነፃ የሚባለው ምዕራቡ ዓለም ከምሥራቁ ዓለም የሚመጣ ጥቃትን ለመከላከል በአሜሪካን የኒዩክልየር ጥላ ከለላ ስር ሲገባ ከነበረው ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ላይ ይገኛል ይላሉ ፍራንክፈርት በሚገኘው የሰላም ጥናት ተቋም ተመራማሪ ማትያስ ዴምቢኒስኪ ።« አሁን ያለውን የስጋት ሁኔታና የኔቶን ምላሽ ከግምት ውስጥ ስናስገባ  ሁሉም ነገራ ያኔ እንደነበረው ዓይነት ነው የሚመስለው። የጋራ መከላከያ እንደገና ዋነኛው ተልዕኮ ሆኗል። ይህ ምንም የሚያጠራጥር የሚያከራክር አይደለም።  ሌላው ተግባር ለምሳሌ በደቡብ ሀገራት መረጋጋትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረትም ኔቶ እንደቀድሞው  ከበስተጀርባ እየሰራ ነው። ደቡባዊ ሀገራትም አጋርነታቸውን ከምር ነው የሚወስዱት ። ይሁንና አሁን ወደ ኃላ እየተንሸራተተ ነው።  » ኔቶ ለዩክሬን ተጨማሪ ጦር መሣሪያ ለማቀበል ወሰነ

ትራምፕ ዳግም ቢመረጡ በኔቶ ላይ ያሳደረው ስጋት 


ይሁንና ዴምቢኒስኪ እንደሚሉት ከዛሬ 75 ዓመት ጋር ሲነጻጸር ኔቶን በእጅጉ በምትደግፈው በዩናይትድ ስቴትስ ላይ መተማመን ቀንሷል። በተለይ የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጪው ዓመት እንደገና ከተመረጡ እስካሁን ይሰራበት የነበረው የጋራ ድጋፍ ተግባራዊ ላይሆን ይችላል።ይህ ደግሞ የአውሮፓ ሀጋራትን ሃላፊነት ሊያከብድ ይችላል።
«መጥፎ በሚባለው መላምት ሃላፊነቱ በእጥፍ በአውሮጳ ሀገራት ጫንቃ ላይ ይወድቃል። ይኽውም እጅግ ግዙፍ የሆነውን ዩናይትድ ስቴትስ እስካሁን በድርጅቱ ትጫወተው የነበረው የፖለቲካ መሪነት ሚናና ወታደራዊ ድጋፍዋን መተካት መቻል አለመቻላቸው አሻሚ ነው። » የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን «አንድ የኔቶ አባል ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በሁሉም አባላት ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት ይቆጠራል» የሚለውን የኔቶ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ አምስት አባላት ጥቃት ሲፈጸም የሚደረግ «የተቀደሰ ቁርጠኝነት» ነው ሲሉ ገልጸውታል። ባለፈው ዓመት በሐምሌ ወር ሊትዌንያ ዋና ከተማ ቪሊንዩስ በተካሄደው የኔቶ ስብሰባ ላይ ባይደን ባደረጉት ንግግር ኔቶ ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሯል ብለዋል።  
«ኅብረታችን እንዳለፉት 70 ዓመታት ሁሉ ዛሬም የዓለም ፀጥታና መረጋጋት ምሽግ ሆኖ ቀጥሏል። ኔቶ ተጠናክሯል ፤ይበልጥ ጉልበት አግኝቷል። አዎ በታሪኩ ከምን ጊዜውም በላይ አንድ ሆኗል። »ፊንላንድ 31ኛዋ የኔቶ አባል ሀገር

የኔቶ ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶትንበርግ
የኔቶ ዋና ፀሐፊ የንስ ስቶትንበርግ ምስል Dursun Aydemir/Anadolu/picture alliance

ማትያስ ዴምቤስኪ እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ የኔቶ አባል ሀገራትን ይበልጥ ያቀራረበው ዩክሬንን የመደገፍ ተልዕኮአቸው ነው።  ዩክሬንን የሚደግፉት የኔቶ አባል ሀገራት ዩክሬን ሩስያን ማሸነፍ አለባት የሚል አቋም ይዘዋል ይሁንና ዩክሬን ሩስያን ማሸነፍ ብትችል እንኳ ሩስያ ይበልጥ ቂመኛና ተበቃይ ነው የምትሆነው፤ሩስያ ኔቶን ልታፈቅር አትችልም፤እንዳለመታደል ሆኖ በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ሩስያ ቀንደኛዋ የኔቶ ስጋት መሆንዋ ይቀጥላል ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ ። ዶክተር ለማ ግን ለኔቶም ይሁን ለሩስያ የሚበጀው ሰላማዊ መፍትሄ ብቻ ነው ብለዋል። 

ኂሩት መለሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ