1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

የምስራቅ ሀረርጌ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያ ወቀሳ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2016

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መልዓከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ ደሣለኝ ለዶይቼ ቬለ በስልክ በሰጡት መረጃ በሀረር ከተማ የቤተ ክርስትያኒቱ ንብረት የነበረና በደርግ መንግስት ተውርሶ ለማስመለስ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ የሚገኝ ይዞታ እንዲፈርስ መደረጉን ገልፀዋል ።

https://p.dw.com/p/4f6RB
በሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር የሚካሔዱ የቤት ግንባታዎች በከፊል
በሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር የሚካሔዱ የቤት ግንባታዎች በከፊልምስል Privat

የምስራቅ ሀረርጌ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያ ወቀሳ

 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት በሐረር ከተማ የሚገኝ የቤተክርስትያኒቱ ይዞታ ከህግ ውጭ እንዲፈርስ ተደርጓል በማለት ወቀሰ።"በክልሉ የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ለመገንባት"  በሚል እንዲፈርስ የተደረገው ቤት በፍርድ ቤት ክርክር እግድ የወጣበት መሆኑንም የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል።የድሬዳዋዉ ወኪላችን መሳይ ተክሉ እንደዘገበዉ ወቀሳ የተሰነዘረበት ወረዳ ባለስልጣናት ሥለ ጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠየቁም ስብሰባ ላይ ነን በማለት መልስ አልሰጡም።

ቤተክርስትያኒቱ በደርግ ዘመን የተወረሱባት ይዞታዎች ከቅርብ ጌዜያት ወዲህ በተለያዩ ክልሎች እንዲመለሱ እየተደረገ ቢሆንም በሀረሪ ክልል ግን በተለየ መልኩ ተግባራዊ እየሆነ አለመሆኑ ተገልጧል ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከትዋና ስራ አስኪያጅ መልዓከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ ደሣለኝ ለዶይቼ ቬለ በስልክ  በሰጡት መረጃ በሀረር ከተማ የቤተ ክርስትያኒቱ ንብረት የነበረና በደርግ መንግስት ተውርሶ ለማስመለስ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ የሚገኝ ይዞታ እንዲፈርስ መደረጉን ገልፀዋል ።

ቀደም ሲል ያለውን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታና በየጊዜው ለመንግስት የተከፈሉ ሰነዶች በቤተክርስትያኒቱ መኖራቸውን የገለፁት ስራ አስኪያጁ "ለብልፅግና ቢሮ መስሪያ"  በሚል መፍረሱን አስረድተዋል ።

የፍርድ ቤት እግድ ተላልፎ ቅዳሜ እና እሁድን ተገን በማድረግ ተካሂዷል የተባለውን ይዞታ እንዲፈርስ እያደረገ የሚገኘው ማን ነው? መስተዳድሩስ እንዲያስቆም ማድረግስ አልተቻለም ወይ? ብለን የጠየቅናቸው የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ መልዓከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ ደሣለኝ ተከታዩን ምላሽ ሰተዋል።

ቤተክርስትያኒቱ በደርግ መንግስት ተወርሰውባት የቆዩ ንብረቶች በሌሎች አካባቢዎች እየተመለሱ መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስኪያጁ በሀረር በተለያየ መልክ የተወሰዱ ንብረቶች አለመመለሳቸውን ተናግረዋል።

ይዞታውን የማፍረስ ስራውን እያከናወነ ነው የተባለውን የሀረሪ ክልል ጅኔላ ወረዳዋና አስተዳዳሪ በስልክ ምላሽ ለማግኘት ደውለን "ስብሰባ ላይ ነኝ" በሚል ምላሽ ባለመስጠታቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።በሀረሪ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የብልፅግና ፅ/ቤት ለመገንባት በሚል ሌላ ይዞታ መፍረሱን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

መሳይ ተክሉ

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ