1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የመንገድ ኮሪዶር ልማት»፣ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚዘጋጀው ሕግ

ዓርብ፣ መጋቢት 20 2016

«የፒያሳ መፍረስና መታደስ ውሎ ይደር የማይባል ነው።ነገር ግን በቦታው ላይ የነበሩት የንግድ ሱቆችና ማምረቻዎች ሲፈርሱ በቅድሚያ ምትክ ቦታ ባለመሰጠቱ ሠራተኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ምን ያህል ችግር እንደ ወደቁ የተረዳችሁ አይመስለኝም።እናንተ በተደጋጋሚ በየሚዲያው የምታሳዩንና የምታሰሙን ለተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያደረጋችሁትን ችሮታ ነው።»

https://p.dw.com/p/4eEoO
Äthiopien | Demolition in Addis Abeba
ምስል Solomon Muchie/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ፣በአዲስ አበባ የመንገድ ኮሪደር  ልማት በሚል የቀጠለው ቤቶችን ማፍረስ ፣ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል ሕግ እያወጣ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መናገራቸው እና ከኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛው ድሀ መሆኑን ያመለከተው ጥናት ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ያስቃኘናል።

የመንገድ ኮሪደር ልማት በሚል በአዲስ አበባ ቤቶች እየፈረሱ ነው። በአዲስ አበባ የሚካሄደውን ይህን የኮሪደር ልማት የተባለው የሥራ ሂደት መገምገሙንም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በማኅበራዊ መገናኛ ገጻቸው አስታውቀዋል። ቀዳሚ ዓላማቸው አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ የተመቸች ሳቢ ከተማ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳካት መሆኑንም የገለጹት ዐቢይ«የማልማት ሥራ ሂደቱ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና በመንግሥት ብሎም አነስተኛ ገቢ ባላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እና የተለያዩ አካላት የተያዙና የተከራዩ ንብረቶችን የነካ »ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። «ይህ ለረዥም ጊዜ ፋይዳ ትልም ይዞ የተነሳ »ያሉት « ሥራ ሲጠናቀቅ ለሁሉም ባለድርሻ አካል ብሎም ለሰፊው ሕዝብ የሚሰጠው ጥቅም ትልቅ ነውም» ብለዋል። ሰሞኑን በመካሄድ ላይ ስላለው የኮሪደር ልማት ሥራ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል። ከመካከላቸውሥራውን የደገፉ ፣ የነቅፉ አማራጭ ሀሳቦችንም ያቀረቡ ይገኙበታል።  ከመካከላቸው አንዱ ሙባረክ መሐመድ በፌስቡክ የጻፉት ነው። « መንግስት ጥሩ ውሳኔ ነው እየወሰደ ያለው...ከተማው በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ውስጥ ናት...በየቀኑ የመኪናና የነዋሪዎቿ ቁጥር እየጨመረ ይገኛል መፍረስ ያለበትን ኣፍርሶ ለእግረኞችም ሆነ ለመኪናዎች መፍትሄ ካላስቀመጠ የዛሬ አምስት ዓመት ወጥቶ መግባት ላይታሰብ ነው! ።» በማለት በርሳቸው እይታ የኮሪደር ልማቱን ጠቃሚነት ለማስረዳት ሞክረዋል።  ፍቅሩ አቡም ትክክለኛ ስራ ነው፤ግፉበት ዶክተር ዐብይ ሲሉ ከይረዲን ዩሱፍ «ልማትን ማን ይጠላል በርቱ» ብለዋል።

በአዲስ አበባ የሚካሄደው የቤቶች ፈረሳ
በአዲስ አበባ የሚካሄደው የቤቶች ፈረሳምስል Solomon Muchie/DW

ጅጊሳ ዋታ ግን ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበዋል።«ለመሆኑ መንግሥት የምንገኝበትን የድህነት ደረጃ ያውቃል? በማለት የሚጀምሩት ጂግሳ ፣ በተለያዩ ክልሎች የተካሄዱ ጦርነቶች ዘረፈ ብዙ ችግሮች ማስከተላቸውንስ መንግሥት ያውቃል ወይ? በእውነት መንግሥት ጡረተኞች የመንግሥት ሠራተኞች እና ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች እጅግ ባሻቀበው የኑሮ ውድነት ምን ያህል እየተሰቃዩ እንደሆነ ያውቃልን? አሁን በምንገኝበት ሁኔታ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ቤቶችን ማፍረስ የሚገባን ጊዜ ላይ ነን? ሲሉ ጅጊሳ ጥያቄዎቻቸውን ያከታተሉበትን አስተያየት አብቅተዋል።የመንገድ ኮሪደር ልማቱ እና የተነሺዎች ጥድፊያ በአዲስ አበባ

ሰላም ይሻላል በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ደግሞ «አድዋ ሙዚየምን የመሰለ ድንቅ ሕንጻ ተገንብቶ አካባቢው ፈርሶ ባይታደስ ነበር የሚገርመው የፒያሳ መፍረስና መታደስ ውሎ ይደር የማይባል ነው።በዚህ ረገድ የምናቀርበው ምክንያት ወይም ማስተባበያ አይኖረም። ካለ በኋላ ነገር ግን በማለት ይቀጥላል «ነገር ግን በቦታው ላይ የነበሩት የንግድ ሱቆችና ማምረቻዎች ሲፈርሱ በቅድሚያ ምትክ ቦታ ባለመሰጠቱ ሠራተኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ምን ያህል ችግር እንደ ወደቁ የተረዳችሁ አይመስለኝም እናንተ በተደጋጋሚ በየሚዲያው የምታሳዩንና የምታሰሙን ለተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ያደረጋችሁትን ችሮታ ነው። ብዙሃኑ ሠራተኛ ግን በዚህ ኑሮ ውድነት የሚሠራበት ድርጅት መፍረስ ተጨምሮ ሥራ በመፍታቱ ኑሮውን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል። የዚህ አስተያየት ፀሐፊ አንደኛው የችግሩ ሰለባ በጫማ ሥራ የምተዳደር ባለሙያ ነኝ። የመጨረሻ ችግር ፈቺ ፈጣሪ መሆኑን ብንገነዘብም መቼም ሥልጣን ሰጪም እሱ ነውና መፍቴሕ ብናገኝ ብለን ወደ ከተማ አስተዳደሩም እያማተረን እንገኛለን። እናም አንድ በሉን እንላለን።» ሲል ጥሪ ያቀርባል።

በአዲስ አበባ የሚካሄደው ቤቶችን ማፍረስ
በአዲስ አበባ የሚካሄደው ቤቶችን ማፍረስምስል Solomon Muchie/DW

ሸምስ አህመድ ስራውን «የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበና ከፈረሰ በኋላም ለህዝብ ያለው ጠቀሜታ በውል የማይታወቅ አወዛጋቢ ልማት »ሲል በአጭሩ ገልጸውታል። አብድራህማን ደጉ ምርት ደግሞ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ሌላ ነው ይላሉ « ኢትዮጲያ ቅድሚያ ሰላም ነው የሚያስፈልጋት ምክንያቱም የተረጋጋ ፖለቲካ የሌለው ሃገር የቱንም ያህል ቢያድግ እድገቱ የእንቧይ ካብ ነው የሚሆነው ቢኒ ገብርሽ ሀሳብ አላቸው «ነባሮቹን ከማፍረስ ለማለት ይመስላል « ከአዲስ አበባ መውጫ 50 ኪሎሜትር ርቀት ዙሪያ  ለምን አዳዲስ ከተሞች አይገነቡም። የሚለውን ሀሳባቸውን በፌስቡክ አካፍለዋል። ሙሉ ሰው ብርሀኑ በፌስቡክ ከቢኒ ገብርሽ ጋር የሚመሳሰል ሀሳብ አቅርበዋል። የሀገሪቱ በጀት ለምን አዲስ አበባ ብቻ ይፈሳል?ሌሎች ከተሞችን የረሳ ልማት የዜጎች ፍሰት ወደ አዲስ አበባ ብቻ ይሆንና ከሰው ብዛት የተነሳ ለኑሮ ምቹ ያልሆነች ከተማ ሊያደርጋት አይችልም?ከመፍረሱ በፊት ነዋሪዎችስ ምቹ የሆነ የመኖሪያ እና የመስሪያ ቦታስ ተመቻችቶላቸዋል?ብዙ ክልሎች ደሞዝ መክፈል ባልቻሉበት:የኑሮ ውድነቱ ህዝቡን እያስመረረው በለበት ሁኔታ ጥሩ ይዞታ ላይ ያሉ ፎቆችን ጨምሮ ማፍረስ ያገራችንን ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም?ፍትሀዊነትም ይጎለዋል? ከህዝቧ አብዛኛው ገበሬ በሆነበት ሀገር ፎቅ በመደርደር ብልፅግና አይመጣም »ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።በፒያሳ እና አራት ኪሎ የመልሶ ማልማት ተነሽዎች አስተያየት

 «ሰዉ ተፈናቅሎ መኖሪያ አጥቶ ለማነው ከተማው የሚለማው ፤ሰው የሚበላው አጥቶ የሚኖርበት አጥቶ ሰላም አጥቶ ለማነው ቆይ ልማቱ »ይህ ደግሞ መስታወት ላቭ አምሀ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት ነው። «ሀገር እደዚህ አይነት የኑሮ ውድነት፣ ረሐብ ፣ድርቅ እና ጦርነት ውሰጥ እያለች ለ አንድ ከተማ ውበት መጨነቅ ቅድሚያ መሰጠት ነበረበት? ሀለተኛ ሀገሪቱ በተፈናቃይ እንደዚህ ተጨናንቃ ሌላ ተፈናቃይየሚፈጠር አይሆንምን? » የዴቭ የናቱልጅ ጥያቄና ማሳሰቢያ ነው። ባልቻው ኦላኖ የመንግስት ዉሳኔ ትክክል ነዉ ነገር ግን በስምምነት መሆን አለበት። የሚል ሀሳብ ሲያቀርቡ ፤ ማኪባ ማኪባ የሳር ቤት የሌለው ህዝብ ታቅፎ ህንጻ ማፍረስ አላዋቂነት የህዝብንም ችግር አለመረዳት ነው ።» የሚል አስተያየታቸውን አካፍለዋል።  

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድምስል Office of Prime minister of Ethiopia

የኢትዮጵያ መንግሥት “የውጭ ሀገር ሰዎች የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ” የሚፈቅድ ሕግ እያዘጋጀ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ተናግረዋል። ዐቢይ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች ቤት እንዲገዙ የሚፈቅደው ሕግ ዝግጅት “የመጨረሻው ደረጃ ላይ” እንደሚገኝ “ታማኝ” ከተባሉ ግብር ከፋዮች ጋር ባለፈው ቅዳሜ በተወያዩበት ወቅት ተናግረዋል። በዝግጅት ላይ ነው ስለተባለው ስለዚህ ሕግ ከተሰጡት አስተያየቶች አንዱ የሰሎሞን ገብረ እግዚአብሔር አስተያየት ነው። «ለሀገሪቱ ገቢ ዶላር እስከተገኘ ድረስ ምን ችግር የለውም ለኢንቨስትመንት መስፋፋት በሮችን ይከፍታል። ይላል። እንደ ሰሎሞን ሁሉ ውልጫፎ ገብሬ የሕጉ በጎ ጎን ያሉትን በፌስቡክ አካፍለዋል። «ለነገሩ ይህ በውጪ ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ትውልዶች በዘመዶቻቸው ስም የሚገዙትን ሕጋዊ ያደርግላቸዋል። ለጊዜው የንብረት ዋጋ ሊጨምር ይችላል። ሆኖም ጊዜያዊ ነው። ይህን ሕግ ተግባራዊ ማድረግ ለኢንቨስትመንት አመቺ ሁኔታ ይጨምራል።» ብለዋል።

ሄኖክ ከበደ ግን «የሀገሪቱ ዜጎች መሬት ገዝተው ቤት መስራት ባልቻሉበት ሁኔታ የውጪ ዜጎች መግዛት ከጀመሩ የመሬቱም ዋጋ መጨመሩ አይቀርም ለዜጋውም ኑሮ መታሰብ አለበት ባይ ነኝ።»ሲሉ አሳስበዋል።  የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሱልጣን አሊ ደግሞ  «ይሄ ህግ ቢዘገይ በጣም ጥሩ ነው ::ሀገር ሳተረጋጋ ህጉን ማፅደቅ ብዙ ነገሮች ያበላሻል ::በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።ጌታቸው ሰጤም ተመሳሳይ ሀሳብ አላቸው። «መጀመሪያ ሰላሙ ላይ መስራት ነው የሚቀድመው ከዛ ውጭ የትም አይደረስ ይላል። አንዱዓለም ደግነት በአጭሩ የቤት ዋጋ ይጨምራል የኑሮው ሁኔታ ይጨምራል ሲሉ ስጋታቸውን አስፍረዋል። ደጉ ኢድሪስ እስጢፋኖስ በአጭሩ አልረካሁም ሲሉ ጌትሽ ገላሽ «  መንግሥት የራሱን ህዝብ ከማክበር ይልቅ ዓለም አቀፍ ገጽታውን ለማሳመር ነው የሚጥረው» በማለት ወቅሰዋል። ዐቢይ ባለፈው ቅዳሜ ታማኝ ከተባሉ ግብር ከፋዮች ጋር ባካሄዱት ውይይት ላይ የእስካሁኑ « ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከሌላቸው በቀር የንብረት ባለቤት እንዳይሆኑ የሚከለክለው አሠራር እንደሚቀየርም ተናግረዋል።

በኦሮምያ እናትና ከልጅዋ ጋር ውሀ ከጉድጓድ እያወጣች
በኦሮምያ እናትና ከልጅዋ ጋር ውሀ ከጉድጓድ እያወጣችምስል Christian Offenberg/Imago

በዚህ ሳምንት ነበር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በድህነት ውስጥ እንደሚኖር የተገለጸው ። አፍሮ ባሮ ሜትር የተባለው የጥናት እና የምርምር ተቋም በዚህ ሳምንት ይፋ እንዳደረገው 61 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ የድህነት ኑሮ ነው የሚገፋው።መብራቱ ለገሠ ስለጥናቱ ውጤት በፌስቡክ አስተያየት ከሰጡት አንዱ ናቸው።«እና ምን ጠብቀን ነበር ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ ያስቀደሙት መብራቱ ሀገር ምድሩ በእሳት እየነደደ ሰው እየሞተ፣ንብረት እንደ ጉድ እየወደመ፣ ማምረት ቁሞ ህዝብ እብደ ህዝብ እየተፈናቀለ፣ የመንግስትም የግልም ተቆማት እየወደሙ እየተዘረፉ እንዴትና ብሎ እድገት ይመጣል? መንግስት እድገት ብልጽግና ይላል። ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።

ቸኮለ ለማ ይህ እኮ ሳይታለም የተፈታ ነዉ ሲሉ ሄኖክ ከበደ «እኔ ግን ከዚህም ይከፋል ብዬ ነው የማስበው» ብለዋል። ማን ደፍሮት እሱም እንደ ሄኖክ ከዚህም እየባሰ ይሄዳል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጽፈዋል። ልኑር እንደ ሙዴ የድሀው መጠን እንዲያዉም 80 % ይሆናል ባይ ናቸው። ካህሳይ በርሄ ደግሞ ጥናቱ ድሀ አላሳተፈም ሀብታም ተጠይቆ ከሆነ 61% ትክክል ነው ግን 80% መሆን አለበት ብለዋል። ኅደግ ለነም «በትክክል ጥናቱን አልተጠናም፤ 61% ሳይሆን 91% የምንሆነው በድህነት እየኖርን ያለነው ብለዋል ። እስጢፍ ቢ ኢሳያስ ደግሞ ድሀነቱን ተቀብለው «ይኼ በፊትም የነበረ ነው። ደሃ መሆናችን የአደባባይ ሚስጥር ነው። ግን ተስፋ ያለን በጥቂት ጊዜ ውስጥ መውጣት የምንችል ሀገር ነን« ሲሉ ተስፋቸውን አጋርተዋል። ገብረ ሥላሴ መዝገበ ደግሞ « አሁን በ 2400 ሰዎች ላይ የተደረገው ጥናት ከመቶ ሚልዮን ህዝብ በላይ ያላትን ኣገር ይወክላል! የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ በነበሩ ሦስት ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ከሞላ ጎደል ያስቃኘን የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የእስካሁኑ ነበር ።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ