1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዒድ አልፈጥር በአዲስ አበባ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 13 2015

በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ሜዳ እና በዙሪያው በተከበረው ሃይማኖታዊ የ ኢድ አል ፈጥር ክብረ በዓል ላይ እንደሌላው ጊዜ ሁሉ የሃይማኖቱ መሪዎችም ሆኑ የመንግሥት ተወካዮች ለሃይማኖቱ ተከታዮች ንግግር አላደረጉም መልዕክትም የተላለፈበት አልነበረም።

https://p.dw.com/p/4QPQ3
Äthiopien | Eid al-Fitr
ምስል Solomon Muche

ኢድ አል ፈጥር በአዲስ አበባ

የ1444ኛው ዓመተ ሒጅራ የኢድ አል ፈጥር የረመዳን ጾም ፍቺ በዓል በብሔራዊ ደረጃ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ትንሿ ሜዳ እና ዙሪያው ተከብሯል።
በዓሉ የኢድ ሰላትን በጋራ በመስገድ ከተጠናቀቀ በኋላም ያለው ለሌለው በማካፈል፣ በአብሮነትና በመጠያየቅ ነው ተከብሮ የዋለው።

ዛሬ ከንጋቱ 12 እስከ 2: 20 ገደማ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ሜዳ እና በዙሪያው በተከበረው ሃይማኖታዊ የ ኢድ አል ፈጥር ክብረ በዓል ላይ እንደሌላው ጊዜ ሁሉ የሃይማኖቱ መሪዎችም ሆኑ የመንግሥት ተወካዮች ለሃይማኖቱ ተከታዮች ንግግር አላደረጉም መልዕክትም የተላለፈበት አልነበረም። 

እስልምና ሃይማኖት ፈጣሪ አንድ መሆኑን ፣ ሰላት መስገድ ግዴታ መሆኑን ፣ ዘካ ማውጣት ፣ የሐጂ ጉዞ ማድረግ እና የረመዳንን ጾም መጾም የሚሉ አምስት አእማዶች እንዳሉት የሚታወቅ ሆኖ የሮሞዳን ጾም ከነዚህ መሰረታዊ የኢስልምና ምሶሶዎች አንዱ እንደሆነ አስተያየታቸውን የሰጡን የእምነቱ ተከታዮች ነግረውናል።
በመላው ዓለም ለአንድ ወር ረመዳንን ሲጾሙ የቆዩ ሙስሊሞች ዛሬ ኢድ አል ፈጥርን በአደባባይ እያከበሩ አርፍደዋል። ከአደባባይ የጋራ ስግደትና የጸሎት ስነስርዓት ቦኋላም እንደተለመደው ያለው ለሌለው እያካፈ፤ በመጠያየቅ ሲከበር ውሏል።
ጥሩ የለበሱ ፣ በሽቶ መልካም ማዓዛ የታወዱ ፣ መስገጃቸውን ከልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር ይዘው በብሔራዊ ስታዲየም ዙሪያ የተሰባሰቡ ሙስሊም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ይህንኑ በዓል ከንጋቱ ጀንሮ አክብረውታል።
"ከእስልምና መሠረቶች አንዱ ነው የሮሞዳን ጾም። ይህም ማለት በዓመት አንዴ ለአንድ ወር ያህል ስትራብ የሌላቸውን ወገኖችን እንድታስባ ያደርገሃል። በኢኮኖሚ አነስተኛ ደረጃ ያለን ማሕበረሰብ የማስታዎስ ትልቅ እሳቤ ነው።"ኢትዮጵያ ሰሜን የአገሪቱ ክፍል ውድመት ካስከተለው ጦርነት ማግስት የምትገኝ ከመሆኗ ባለፈ በተለያዩ አካባቢዎች ማንነት ተኮር ጥቃቶች ያፈናቀላቸው ዜጎች የበዙበት ፣ ድርቅ የሚያስጨንቃቸው የበረከቱበት ፣ የፖለቲካ ውጥረት ያለበት ጊዜ ላይ ነች። የበዓሉ አክባሪዎች ታዲያ ከደስታቸው ጎን ይህ ተቀርፎ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ተማጽነዋል።
"እርስ በርሳችን በመወያየት፣ በመደማመጥ ፣ ታላቆቻችንን በማዳመጥ እና በመስማት፣ የተጣላውን እንደገና በማስታረቅ የተጎዳንም በመርዳት መቀጠል ይሻላል" 
ወጣት የሚባለው ትውልድ እውቀትና መከባበር ወደ ሚያስገኘው አንድነት እንዲያተኩርም አስተያየት ሰጪው አሳስበዋል።
"ዋናው ትልቁ አገራዊ ሠላም ነው። ሰላም ሲኖር ነው ሙስሊሙ ማህበረሰብ ተሰብስቦ ትልቁን ነገር የሚያደርገው። የአብሮነቱ፣ ድሮ የነበረው ነገር እንዲቀጥል እና የአገሪቱን ሰላም እንዲጠብቅ እንፈልጋለን" 

Äthiopien | Eid al-Fitr
ዒድ አልፈጥር በዓል አከባበር በአዲስ አበባምስል Solomon Muche

ብሔራዊ የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በአዲስ አበባ የተከናወነው የኢድ አል ፈጥር የሰላት ሥነ - ሥርዓት በሰላም መጠናቀቁን አስታውቋል። 


ሰለሞን ሙጬ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
እሸቴ በቀለ