1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፣ የኢትዮጵያ ሐገራዊ ምክክር፣አስፈላጊነቱና ጊዜዉ

እሑድ፣ ጥር 1 2014

የመንግሥትን ስልጣን የያዙትና መንግስትን ለማስወገድ በነፍጥ የሚዋጉ ወገኖች ጥያቄ-ማስጠንቀቂያዉን ዉድቅ እያደረጉ ወይም ድርድር ዉይይት የሚባለዉን ለስልጣናቸዉ ማጠናከሪያ እያዋሉት ምክር ማስጠንቀቂያዉ ከንቱ ቀርቷል።አሁን ግን በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንዲደረግ መታሰቡ ሰሚ ያጣዉ ጉዳይ  በጎ ፍሬ ሊያፈራ ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ።

https://p.dw.com/p/45HSI
Symbolbild Telefonieren
ምስል Fotolia/Kamiya Ichiro

የብሔራዊ ምክክር አስፈላጊነቱና መቼነቱ

የኢትዮጵያ ዉስጥ ፖለቲካዊ ዉዝግብ፣ቀዉስና አለመግባባትን ለማስወገድ ይረዳል የተባለ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ ዝግጅቱ ተጀምሯል።የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈዉ ሳምንት (ታሕሳስ 20 2014) «ሐገራዊ ምክክር» የተባለዉን ሐሳብ የሚያስተባብርና የሚመራ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ አፅድቋል።ሕዝቡ ኮሚሽኑን የሚመሩ ሰዎችን እንዲጠቁምም ጥሪ ተደርጎለታልም።ምክር ቤቱ አዋጁን ያፀደቀና ኮሚሽን እንዲሰየም የወሰነዉ በረቂቅ አዋጁ ላይ «ሕዝባዊ» ያለዉን ዉይይት ካስተናገደ በኋላ መሆኑን አስታዉቋል።

 

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ብዙ ጊዜ ደም የሚያፋስሱ ግጭቶና ዉዝግቦችን በድርድር እንዲፈቱ፣ በታሪክ በተዛቡ ጉዳዮች ላይ እንዲግባቡ፣የጋራ ሐገራዊ እሴቶችን እንዲዳብሩ፣ ኢትዮጵያዉያንና የኢትዮጵያን ጉዳዩን የሚከታተሉ ምሑራን፣የፖለቲካ ተንታኞች፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ዲፕሎማቶች፣ምናልባት ከአፄ ኃይለሥላሴ ሥርዓት መዉደቅ ጀምሮ ደጋግመዉ ሲጥይቁ፣ ሲመክሩ፣ሲያሳስቡም ነበር።

 

እስካሁን የተፈራረቁት ፖለቲከኞች በተለይም የመንግሥትን ስልጣን የያዙትና መንግስትን ለማስወገድ በነፍጥ የሚዋጉ ወገኖች ጥያቄ-ማስጠንቀቂያዉን ዉድቅ እያደረጉ ወይም ድርድር ዉይይት የሚባለዉን ለስልጣናቸዉ ማጠናከሪያ እያዋሉት ምክር ማስጠንቀቂያዉ ከንቱ ቀርቷል።አሁን ግን በመሠረታዊw ጉዳዮች ላይ ምክክር እንዲደረግ መታሰቡ ምናልባት ግማሽ ምዕተ-ዓመት ሰሚ ያጣዉ ጉዳይ  በጎ ፍሬ ሊያፈራ ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ።

 

የዚያኑ ያሕል የምክክር ዝግጅት የተጀመረዉ ሐገሪቱ በለየለት ጦርነትና በጎሳ ግጭት ሺዎች በሚገደሉባት፣ሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸዉ በተፈናቀሉበትና ኢትዮጵያ እንደ ሐገር መቀጠሏ በሚያጠያይቅበት ወቅት ነዉ።ተፋላሚ ኃይላት በግልፅ ተኩስ ሳያቆሙ፣ልዩነታቸዉን በድርድር ለመፍታት ሳይፈቅዱና በሕዝብ ላይ በደል ያደረሱ ለፍርድ ሳቀርቡ የሚደረገዉ ምክክር ምን ያሕል አካታችና ሁሉን አቀፍ ሊሆን ይችላል የሚሉ አሉ።የምክክሩ ሒደት ገለልተኛ መሆኑንና ዉጤት ማምጣቱንም  የሚጠራጠሩ አሉ።በዛሬዉ ዉይይታችን ደጋፊ-ተጠራጣሪዎቹን ሐሳቦች ባጫችጭሩ ለማንሳት እንሞክራለን።C

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና ዲፕሎማቶች በዉይይቱ እንዲካፈሉ በኢሜልም፣በዋትስአፕም መልዕክት ልከን፣ በስልክም ደጋግመን ደዉለን ነበር።ይሁንና በፅሁፍ ላቀረብነዉ ጥያቄ መልስ አልሰጡንም።በስልክ ያገኘናቸዉ አንድ ባለስልጣን ግን መንግስት ሒደቱን ከማመቻቸት ባለፍ ገለልተኛ መሆን ስላለበት ባለስልጣናቱ ለጊዜዉ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አይሰጡም ብለዉናል። ሶስት እንግዶች አሉን።

ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ በጀርመን የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ ፣ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ። አቶ ባይሳ ዋቅወያ፣ የሕግ ባለሙያና የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማት።ይልማ ኃይለ ሚካኤል፣ በበርሊን የዶቼ ቬለ ወኪል ናቸዉ

ነጋሽ መሐመድ