1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ወጣቶችና ሠላም» በትግራይ-ሥልጠና

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2016

በትግራይ፣ዕድሜአቸው ከ15 እስከ 29 የሆኑ ወጣቶች ቁጥር 2 ነጥብ 9 ሚልዮን ይገመታል።የሁለት ዓመቱ ጦርነት ዋነኛ ሰለባዎች መሆናቸው የሚገለፅላቸው እነዚህ ወጣቶች ከጦርነቱ በኃላ ባለው ግዜም በስራ እጦት፣ ተስፋ ማጣት እና ሌላ ግጭት ስጋት እግራቸው ወደመራቸው መሰደድ፣ ለተለያዩ ሱሶች እና ወንጀሎች መጋለጥ በስፋት እየታየባቸው መሆኑ ይገለፃል።

https://p.dw.com/p/4f6JO
ሁለት ዓመት ያስቆጠረዉ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ስምምነት ቢቋጭም አሁንም የሌላ ጦርነት ሥጋት አለ
የትግራይ ወጣቶችን ከጦርነት አስተሳሰብ አላቅቆ የሰላምን አስፈላጊነት እንገነዘቡ ያለመ ሥልጠና በመቀሌምስል Million Haileyessus/DW

«ወጣቶችና ሠላም» በትግራይ-ሥልጠና

                 

በትግራይ ክልል ከተደረገዉ ጦርነት  በኋላየስራ አጥነት ችግር፣ ስደት እና የወጣቶችለሱስና ሌሎች ችግሮች ተጋላጭነት እያሻቀበ መሆኑ ተገለፀ። ይህን ለመከላከል ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ጥሪ ቀርቧል። «ወጣቶች ለሰላም» የሚል የወጣቶች  ስልጠና ትግራይ ዉስጥ እየተሰጠ ሲሆን፥ ወጣቶች ጦርነት እንዲቃወሙ፣ ሰላምን እንደ ብቸኛ አማራጭ እንዲያዩ የሚያስችል አስተሳሰብ ለማስረፅ ጥረት ይደረጋል  ተብሏል።

 በትግራይ ካለው ህዝብ መካከልዕድሜአቸው ከ15 እስከ 29 የሆኑ ወጣቶች ቁጥር 2 ነጥብ 9 ሚልዮን ይገመታል። የሁለት ዓመቱ ጦርነት ዋነኛ ሰለባዎች መሆናቸው የሚገለፅላቸው እነዚህ ወጣቶች ከጦርነቱ በኃላ ባለው ግዜም በስራ እጦት፣ ተስፋ ማጣት እና ሌላ ግጭት ስጋት እግራቸው ወደመራቸው መሰደድ፣ ለተለያዩ ሱሶች እና ወንጀሎች መጋለጥ በስፋት እየታየባቸው መሆኑ ይገለፃል። በትግራይ ያሉ ወጣቶች ሁለገብ ችግር ለመቅረብ ያለመ የወጣቶች የሰላም ኮንፈረንስ በተለያዩ የፌደራል መንግስት ተቋማት እንዲሁም የክልሉ አስተዳደር እና የግል ድርጅቶች ተሳትፎ በመቐለ ከትላንት ጀምሮ እየተካሄደ ያለ ሲሆን በዚሁ መድረክ ከትግራይ የተለያዩ አካባቢ የተወጣጡ 500 ወጣቶች በመጀመርያ ዙር ስልጠና እየተሰጣቸው ይገኛሉ። የትግራይ ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሐላፊ አቶ ይሐይሽ ስባጋድስ እንደሚሉት፥ በትግራይ ያሉ ወጣቶች ከገቡበት አስከፊ ሁኔታ ለማውጣት አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋል። "በጦርነቱ ምክንያት የወጣቶች ሕገወጥ ስደት የተበራከተበት፣ የአደንዛዥ እፆች ተጠቃሚዎች የበዙበት፣ ቁማር እና የተለያዩ ወንጀሎች ያሻቀቡበት እንዲሁም ለማሕበረሰብ አደጋ የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሮ ይገኛል። በዚህ ወቅት የህዝባችን ጥያቄ ሰላምና ፍትህ ሊረጋገጥ፣ ስራ ዕድል ሊሰፋለት በሚጠይቅበት ወቅት የሚካሄድ የወጣቶች የሰላም ኮንፈረንስ በመሆኑ ወቅታዊ እና አስፈላጊ ያደርገዋል" ሲሉ አቶ ይሐይሽ ተናግረዋል።


የበርካታ ወጣቶች ሕይወት የቀጠፈው የትግራዩ ጦርነት በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ቢቋጭም የሌላ ዞር ግጭት ስጋት አሁንም በበርካቶች አለ። በትላንቱ መድረክ ለወጣቶች መልእክት ያስተላለፉት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ለማንኛውም ፖለቲካዊ ችግር የሐይል መፍትሔ አማራጭ እንዳይሆን እየተሰራ ነው ብለዋል። ጀነራል ታደሰ "የሐይል አማራጭ ሁለተኛ እንዳይመጣ፥ የሚቻል ሁሉ ጥንቃቄ መደረግ አለብን። ሐይል መጨረሻ መሆን አለበት። አስፈላጊው ሰላማዊ አማራጭ ነው። የደቡብ ይሁን የምዕራብ፥ ፀለምቲ ይሁን ሁሉ ነገር በሰላም ሊያልቅ የሚቻልበት ጥረት ይደረጋል። በሰላም ተስፋ አንቆርጥም። የተረፉን ግዛቶች ለማስመለስ እና አጠቃላይ ወደነበርንበት ሁኔታ ለመመለስ ከስሜት ወጥተን በሰላም ሁሉ ማሳካት አለብን" ብለዋል።

ትግራይ ከሚዋሰንዋት ክልልሎች እና ህዝቦች ጋር ያላት ግንኙነት ሊፈተሽ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲኖርም ሊሰራ እንደሚገባ ጀነራሉ ጨምረው ገልፀዋል። ጀነራሉ ጨምረውም "እንደ ሐይሎች የአማራ የትግራይ ሐይሎች፣ እንደ ህዝብ የትግራይ አማራ ህዝቦች ተጎራብተን የምንኖር ነን። ቦታም አንቀይርም፥ ግንብ አንገነባም፥ መዘጋጋት አንችልም፥ አብሮ መኖራችን አይቀየርም። ይህ ከሆነ ዘንድ ዘላቂ ሰላም እንዴት እንፍጠር ልናስብበት ይገባል። ከሰሜን [ኤርትራ] ያለን ችግር እናውቃለን። ምን በደል እንዳደረሱብን ይታወቃል። ከሰሜንም ጋር ተጎራብቶ እንዴት በሰላም መኖር ይቻላል ሊታሰብበት የሚገባ ነው" ሲሉ ገልፀዋል። 

«ወጣቶችና ሠላም» በሚል መርሕ መቀሌ ዉስጥ በሚሰጠዉ የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ከመላዉ ትግራይ የተዉጣጡ 500 ወጣቶች ይካፈላሉ
«ወጣቶችና ሠላም» በሚል መርሕ መቀሌ ዉስጥ የሚካሔደዉ ሥልጠና በተጀመረበት ወቅትምስል Million Haileyessus/DW

በትግራይ የወጣቶች ሕይወት በተለይም ከጦርነቱ በኃላ የከፋ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ በሀገራቸው ተስፋ ያጡ ወጣቶች በየቀኑ በሕገወጥ መንገድ ድንበር በማቋረጥ እንደሚሰደዱ የትግራይ ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ይገልፃል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ