1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአለማጣ እና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ አሻቀበ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 2016

በአማራና ትግራይ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ያለፈው ሰኞ አስታውቋል። እንደ ድርጅቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ በተለይ ሴቶችና ህጻናት የሚገኙበት ሁኔታም አሳሳቢ ነው።

https://p.dw.com/p/4f9GP
ከአለማጣ ከተማ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው
ከአለማጣ ከተማ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነውምስል Alemenew Mekonnen Bahardar/DW

ከአለማጣ እና አካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ አሻቀበ

የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው በትግራይ እና አማራ ክልል የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አዋሳኝ አካባቢዎች  በተከሰተው ግጭት ሳቢያ  የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ እንደሚበልጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል ። 
ድርጅቱ  ባለፈው ሰኞ  ማምሻ የአካባቢውን ባለሥልጣናት ጠቅሶ እንዳስታወቀው ካለፈው ሚያዝያ አምስት እና ስድስት ጀምሮ በአላማጣ ከተማ ፣ በራያ አላማጣ ዛታ እና ኦፍላ በተካሄደው ግጭት  የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ በላይ ሆኗል። ከተፈናቃዮቹ መካከል በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ህጻናት መኖራቸውን ድርጅቱ ጠቅሶ፤  በሕይወት ለመቆየት  ሰፊ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አመልክቷል።ድርጅቱ አያይዞም እነዚህ  ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው ሰብዓዊ ይዞታም አሳሳቢ ነው ብሏል። ከራያ አላማጣና ሌሎች ወረዳዎች ብዙ ህዝብ እየተፈናቀለ ነው

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ከአለማጣ ከተማ ተፈናቅለው ከአራት ሊጆቻቸው ጋር በዋጃ ጊዚያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት ወይዘሮ ገነት አበበ  ያሉበት  ሁኔታ ፈታኝ መሆኑን ይገልፃሉ። 
 ላለፉት ዘጠኝ ቀናት እሳቸውም ሆነ ሌሎች ተፈናቃዮች  እርዳታ አለማግነታቸውን የገለፁት ወይዘሮ ገነት ፤በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ሆነው  የወለዱ ሴቶች መኖራቸውንም ያስረዳሉ።
ሌላው ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በአለማጣ ከተማ በባጃጅ ሹፌርነት ይተዳደሩ የነበሩ እና በአሁኑ ጊዜ ተፈናቅለው በዋጃ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙት አቶ ሚሊዮን ኪሮስ በበኩላቸው፤ሁኔታው በተለይ ለህፃናት እና ለሴቶች ከባድ መሆኑን ያስረዳሉ።
በመሆኑም መንግስት ህዝቡን ማየት እና ከጎን መቆም አለበት ይላሉ።ወይዘሮ ገነት በበኩላቸው  ከጊያዚያዊ ከእርዳታ ይልቅ  ሰላም ወርዶ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል።

የአለማጣ ከተማ እና አካባቢው በሰሞኑ ግጭት በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
የአለማጣ ከተማ እና አካባቢው በሰሞኑ ግጭት በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል።ምስል DW

ግጭቱ እስከተከሰተበት ጊዜ ድረስ የአላማጣ ከንቲባ ሆነው የቆዩት የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ አበራ፤ ኅብረተሰቡ ከስድስት ወረዳዎች መፈናቀሉን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ለተፈናቃዩ ኅብረተሰብ እህል ማቅረብ ባለመቻሉ እራሱ የከተማው አስተዳደር ለተወሰኑ ቀናት ዳቦ እየገዛ ለመመገብ መሞከሩንም ተናግረዋል።ሆኖም  ችግሩ ከአቅም በላይ በመሆኑ እና፤ተፈናቃዮቹን በመጠለያ ጣቢያ ማስቀመጥ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እና ለከፋ ማህበራዊ ቀውስ ሊያጋልጥ ይችላል በሚል  ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የተፈናቃዮች የድረሱልን ጥሪ

በአማራና ትግራይ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት  ተከትሎ፤ በአካባቢው የሚደርሰው ጉዳት እንዳሳሰበው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  እየገለፀ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ፣የጃፓን፣ የብሪታንያ እና የፈረንሳይ ኤምባሲዎች ችግሩ በውይይት እንዲፈታና ለሰላማዊ ሰዎችም ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። 

የአማራ ክልል መንግስት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ «ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል» ሲል ከሶ አካባቢውን ለቆ ካልወጣ ህዝቡን ከጥቃት ለመከላከልና ክልሉንም ከጥፋት ለማዳን ይገደዳል ሲል አስታውቆ ነበር። 
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጀኔራል ታደሰ ወረደ  ደግሞ «በኃይል የተያዙ የትግራይ አካባቢዎች» ያሏቸውን ቦታዎች በኃይል ለማስመለስ እንደማይፈልጉ ሆኖም ችግሮቹ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመነጋገርና በመግባባት የሚፈቱ እንደሚሆን ባለፈው ሳምንት ገልፀዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ