1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሆላሎ ጭፈራ

ዓርብ፣ ጥር 12 2015

አሆላሎ በልጃገረዶች እና እነሱን ለማጨት በሚፈልጉ ወጣት ወንዶች መካከል ከጥንት ጀምሮ የሚካሄድ ባሕላዊ ጭፍራ ነው። ጭፈራው በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚከናወን ሲሆን በዚህ በጥምቀት በዓል ሰሞን በወሎ ደሴ እና አካባቢዋ ይከናወናል። የአሆላሎ ጭፈራና አከባበሩ ባህሉን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ምን እየተሰራ ነው?

https://p.dw.com/p/4MU0e
በዚህ ጭፈራ ላይ የሚሳተፉ ሁሉም ልጃገረዶች የባሕል ልብሳቸውን ለብሰው፤ ሹሩባ ተሠርተው እና ተቆነጃጅተው ይገኛሉምስል Tehuledere District Culture and Tourism Office

የአሆላሎ ጭፈራ

አሆላሎ ልጃገረዶች አንድ ላይ በመሆን ክብ ሰርተው በዜማ የሚጫወቱት ባህላዊ ጭፈራ ሲሆን ያላገቡ ወንድ ወጣቶች ደግሞ በጭፈራው ወቅት ያጅቧቸዋል፤ ስጦታም ያበረክቱላቸዋል። መስፍን ተክሌ ይህ ባህላዊ ጨዋታ ባህሉን ጠብቆ እንዲቆይ ከሚያስተባብሩት ወጣቶች አንዱ ነው። የተሁለደሬ ወረዳ የባህል እሴቶች ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ የሆነው መስፍን የአሆላሎን ጨዋትን ሲገልፅ « የሚፈላለጉ ልጃገረዶች እና ወንዶች/ጢነኖች ለመገናኘት ወይም ለመተጫጨት የሚጫወቱት ጨዋታ ነው። ለምሳሌ በክብረ በዓላት፣  በጥምቀት፣ በአረፋ፣ በአሹራና ሠርግ ላይ ይጫወቱታል።» ይላል።  ክብ ከሰሩት ውስጥ አንዷ ሴት ተሽኮርምማ መሀል ገብታ ከአንድ ወንድ ሎሚ ተቀብላ አሽታ ከመለሰችለት ትፈልገዋለች ማለት ነው።  ሎሚውን ግን ለሌላ ወንድ ከሰጠች መስፍን እንደገለፀልን እነዚህ ሁለት ወንዶች ትግል ይወርዳሉ። ይሁንና ትግል ሲወርዱ «ትግሉ ሰላማዊ ትግል ነው» ይላል መስፍን።  ያሸነፈ ልጅቷን ይወስዳል። ለትግል የሚያበቁ ሶስት ምክንያቶች እንዳሉም መስፍን ገልፆልናል።  ትግል እና ጠቡም እዛው ቦታው ላይ ይፈታል።  የአሆላሎ ጭፈራም እስከ ምሽት ድረስ የሚዘልቅ ጨዋታ ነው። 

የ 24 ዓመቷ መዓዛ አብዱ የተሁለደሬ ባህል እና ቱሪዝም ቡድን ውስጥ ቲያትር እና ውዝዋዜ ላይ ትሰራለች።  ጭፈራውን ባህል ቡድኑ ውስጥ የተማረችው ሳይሆን ያደገችበት ነው። « የምንሞጋገሰው፣የምንነቃቀፈውም በዜማ ነው። »ትላለች። መዓዛ ባለትዳር ናት። እሷም በዚሁ መልክ ነው የታጨችው « እሱን እዛው አገኘሁት ፤ ሳየው ወደድኩት። ከዛ ሎሚውን እና አሪቲውን ተቀበልኩኝ። ከዛ እጮና ሆንን፤ ሽማግሌዎች ተላኩ ፤ ከዛ ቤተሰብ ፈቀደ። ያው በባህላችን መሠረት ተጋባን» ትላለች። ይህ የሆነው ከአምስት ዓመት ገደማ በፊት ነው። የዶይቸ ቬለ ተከታታይ እና የአድማጮች ማህደር ዝግጅት ተሳታፊ የሆኑት ጥቁር  አሚን  ባለፉት ዓመታት በሚኖሩበት ደሴ አካባቢ የአሆላሎ ጭፈራ ሲካሄድ ተገኝተው ነበር። ቀደም ሲል የነበረውን የአሆላሎ ጭፈራ እና አሁን ላይ የሚከበርበት መንገድ ሲያነፃፅሩ የተወሰነ ልዩነት አለ ይላሉ። « ጭፈራው እንዳለ ሆኖ ፤  ለታጨችው ቤተሰቦች ቤት የሚወሰደው እና ለታዳሚው በሙሉ የሚሰጠው አደስ አሁን ላይ ቀርቷል  በተረፈ ግን ድባቡ አሁንም ደስ የሚል ነው» ይላሉ ጥቁር አሚን  «ወደ አሆላሎ  ቦታ ሴት ልጅ  እንዳትሔድ  መከልከል  እንደነውር ስለሚቆጠር ልጃገረዶቹ በነፃነት ወደሚጫወቱበት ቦታ ይሄዱ ነበር » የሚሉት ጥቁር አሚን ቀደም ሲል ከስምንት ዓመት ጀምሮ ያሉ ልጃገረዶች ወደ ጭፈራው ይሄዱ እንደነበር፣ አብዛኞቹ ልጃ ገረዶች ግን እድሜያቸው በ 12 እና 14 ዓመት ገደማ ይሆን እንደነበር ገልፀውልናል። 
ይህ ጭፈራ በአንዳንድ የወሎ አካባቢዎች ጨርሶ ተቋርጦ እንደነበር እና ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ባህል እና ቱሪዝም ማስተዋወቅ ሲጀምር ተመልሶ በድምቀት መከበር መጀመሩን መስፍን ነግሮናል። የ31 ዓመቱ ወጣት «የአሆላሎ ጨዋታን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እቅድ ተይዞ እየተሰራም ነው» ይላል። ለዚህም ባለፉት ዓመታት ባህሉን ከሚያውቁ ሰዎች ጋር ጨዋታውን የመከወን ስራ እንደተሰራ እና በበርካታ ምክንያት እየተሸረሸረ እና እየተበረዘ መጥቷል ያለውን ባህል መልሶ ለመገንባት እየተሰራ እንደሆነ መስፍን ያብራራል።  ዘንድሮም የአሆላሎ ጭፈራ በዞን ደረጃ ሀይቅ ላይ ከጥር 17 እስከ 21 ቀን እንዲካሄድ ቀን እንደተቆረጠ እና ለዚህ በዓል ድምቀት የሚሆኑ ልጃገረዶች ከገጠሩ አካባቢ ተጋብዘው እንደሚመጡም መስፍን ገልፆልናል።  የዘንድሮው የአሆላሎ ጭፈራ የሚካሄድበት ቀን አስቀድሞ ቀን እንደተቆረጠለት ሁሉ ቀደም ሲልም ጭፈራው የሚካሄድበት ቀን ይታወቃል። «ይህም ወላጆች ለልጆቻቸው ልብስ ገዝተው እንዲዘጋጁ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥር ነበር» ይላሉ ጥቁር አሚን ።  ከዚህም ሌላ የአሆላሎ ጭፈራ በክርስትያን እና በሙስሊሙ ዘንድ እንዴት አሁን ድረስ በጋራ እንደሚከበር ጥቁር አሚን አካባቢያቸውን ለክብረ በዓላት ምሳሌ አድርገው ይጠራሉ። ወጣቶች የአሆላሎ ጭፈራ ባህል እንዲቀጥል የሚያደርጉትንም ጥረት ያወድሳሉ።

የአሆላሎ ጭፈራ
በዚህ ጭፈራ ላይ የሚሳተፉ ሁሉም ልጃገረዶች የባሕል ልብሳቸውን ለብሰው፤ ሹሩባ ተሠርተው እና ተቆነጃጅተው ይገኛሉምስል Tehuledere District Culture and Tourism Office
የአሆላሎ ጭፈራ
የአሆላሎ ጭፈራ ላይ ወንዶቹም ሴቶችን በሚማርክ መልኩ ራሳቸውን አስውበው፣ ጎፈሬያቸውን ነቅሠውና ቅቤ ተቀብተው ይገኛሉምስል Tehuledere District Culture and Tourism Office

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ