1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ያለውን ግጭት ተከትሎ ይፈጸማሉ የተባሉ ግድያዎች

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 2016

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች ሰላማዊ ዜጎችን ያልለየ ግድያ በመንግስት ፀጥታ ኃይሎች ይፈጸማል ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መንግስትን ወቀሰ ። እንደ ኦነግ መግለጫ ሰላማዊ ዜጎቹ የተለያዩ ስያሜዎች በመሰጠት በጠራራ ጸሃይ ሳይቀር ይገደላሉ ።

https://p.dw.com/p/4a9tL
Äthiopien Region Oromia
ምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያው ግድያ እና የኦነግ ክስ

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች ሰላማዊ ዜጎችን ያልለየ ግድያ በመንግስት ፀጥታ ኃይሎች ይፈጸማል ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መንግስትን ወቀሰ ። እንደ ኦነግ መግለጫ ሰላማዊ ዜጎቹ የተለያዩ ስያሜዎች በመሰጠት በጠራራ ጸሃይ ሳይቀር ይገደላሉ ። የኢትዮጵያመንግስት በበኩሉ በተለያዩ አከባቢዎች «ጽንፈኛ» ያላቸው ታጣቂ ኃይሎች ላይ የሚወስደውን ወታደራዊ ርምጃ ማጠናከሩን አሳውቋል ። 

የኦሮሚያው ግድያ እና የኦነግ ክስ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ዛሬ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ እንዳመለከተው በኦሮሚያ ተደጋጋሚ ግድያ እና የጅምላ እስሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሳያቋርጥ ይፈጸማል ብሏል፡፡ ኦነግ ለጥቃቱም መንግስትን ከሷል፡፡ እንደ ኦነግ መግለጫ ሰላማዊ ዜጎቹ የተለያዩ ስያሜዎች በመሰጠት በጠራራ ጸሃይ ሳይቀር ይገደላሉ ።

ፓርቲው በመግለጫው ጭካኔ የተሞላበት ያለው ግድያ ከተፈጸመባቸው አንዱ ምዕረብ ሸዋ ዞን አቡና ግንደበረት ወረዳ ነው ብሏል፡፡ ህዳር 30 እና ታኅሣሥ 01 ቀን 2016 ዓ.ም. በአቡና ግንደበረት እርጃጆ፣ ጫፌ ኤረርና ፊኖ ቀበሌያት 8 ንጹሃን ዜጎች በጠራራ ጸሃይ ተገድለው ሁለት ሰዎች ቆስለዋል በማለት ስማቸውንም በመግለጫው ዘርዝሯል፡፡

የኦነግ መግለጫ ከዚህ በፊት በቄሌም ወለጋ ዞን ጊዳሚ  ከተማ ውስጥ በጸሎት ላይ እያሉ ህዳር 15 ሌሊት ከመካነ የሱስ ቤተክርስቲያን ዘጠኝ አማኞች ተወስደው የተገደሉትም በመንግስትን ነው ብሏል፡፡

በኦሮሚያ ግድያዎች የሚፈጸሙት በመንግስት ብቻ ነውን?

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በዚህ ላይ ለዶቼ ቬለ ተጨማሪ ማብራሪያ ሲሰጡ ከዶቼ ቬለ በኦሮሚያው ግጭት ለሁሉም ግድያ መንግስት ብቻ ነው ተጠያቂ የሚደረገው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ አቶ ለሚ በሰጡን ማብራሪያም "የብልጽግና ቡድን አሳውን ለማጥፋት ውኃውን ማድረቅ በሚል መርኅ ነው በየቦታው ዘርፈ ብዙ ጭፍጨፋ እያካሄደ ያለው፡፡ ዜጎች ከቤታቸው ተወስደው ለህግ ሳይቀርቡ የሚገደሉት ግድያ ፖለቲካዊ ነው” ሲሉ መልሰዋል፡፡ 

ኦሮሚያ ክልል፤ ኢትዮጵያ
ህዳር 14  እና 15 በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በንጹሐን ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች መገደላቸውን ያነሳው የኦነግ መግለጫ ትንንሽ ልጆች ጨምሮ ሙሉ የአንድ ቤተሰብ አባላት የግድያ ሰለባ የሆኑበትን አጋጣሚም በዚሁ መግለጫ አካቷል፡፡ ምስል Seyoum Getu/DW

ህዳር 14  እና 15 በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በንጹሐን ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች መገደላቸውን ያነሳው የኦነግ መግለጫ ትንንሽ ልጆች ጨምሮ ሙሉ የአንድ ቤተሰብ አባላት የግድያ ሰለባ የሆኑበትን አጋጣሚም በዚሁ መግለጫ አካቷል፡፡ በአከባቢው ብዙ ቤቶች መቃጠላቸውንም ጠቅሷል፡፡ ህዳር 15 በቀሌም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማም ንጹሃን ላይ ተተኩሶ የበርካቶች ህይወት ማለፉን ያነሳው ኦነግ 4 ሰዎችን በስም ዘርዝሯልም፡፡ በተመሳሳይ እለት በምዕራብ ጉጂ ገላና ወረዳም የ5 ንጹሃን ሰዎች ሕይወትን የቀጠፈ ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች ላይ አነጣጥሯል ብሏል፡፡

ፀጥታን በማስከበር የመንግስት ሚና

የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች ሕግን የማስከበር ያለውን ወታደራዊ ርምጃ እየወሰ መሆኑን በመጥቀስ ታጣቂዎች ንጹሐንን እንደሚገድሉ ይጠቁማል ።

የኦነግ ባለስልጣኑ አቶ ለሚ ገመቹ ግን ለሁሉም ግድያዎች መንግስት ኃላፊነት መውሰድ የሚኖርበት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ብቸኛው ተቋም በመሆኑም ነው ይላሉ፡፡ "የታጠቀ ኃይል እኮ መንግስት አልሆነም፡፡ የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ ኃላፊነት የመንግስት ነው” ብለዋልም፡፡

ህዳር 13 ቀን 2016 በቡኖ በደሌ ዞን ጨዋቃ ወረዳ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ተማሪዎችን ጨምሮ 52 ሰዎች ተገድለዋል ሲልም በመግለጫው ያተተው ኦነግ፤ ምዕራብ አርሲ፣ ምእራብ ሸዋ እና ሰሜን ሸዋ በተለያዩ አከባቢዎችን ጠቅሶ የመንግስት ጦር ከመስከረም ወዲህ እንኳ በርካታ ግድያዎችን ፈጽሞ ቤቶችንም አቃጥሏል ሲል በዚሁ መግለጫ ወቅሷል፡፡

በኦሮሚያ ይፈጸማሉ ስለተባሉት ግድያዎችና ወታደራዊ ርምጃው የመንግስት ምላሽ

ዶይቼ ቬለ በዚሁ የኦነግ መግለጫ እና በመንግስት ላይ የቀረቡትን ወቀሳ በማስመልከት ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ አቶ ኃይሉ በምላሻቸውም መንግስት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚወሰድው እርምጃ አይኖርም ብለዋል፡፡

"በንጹሃን ዜጎች ላይ ርምጃ የሚወስደው አሸባሪው የሸነ ቡድን ነው” ያሉት አቶ ኃይሉ ለዚህ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በቅርቡ በርካታ ንጹሐንን የቀጠፈውን አሰቃቂ ጥቃት በአብነት አቅርበዋል፡፡ አቶ ኃይሉ ሸነ ሉትና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው በኦሮሚያ ትጥቅ አንግቦ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ከግድያዎቹ በተጨማሪ በአከባቢው የነዋሪዎችን ቤት አቃጥሏልም ሲል ከሰዋል፡፡ ኃላፊው ታጣቂ ቡድኑን ባለፉት ሥስት ዓመታት ተሰማርቶበታል ባሉት የእገታ ወንጀልም ታጣቂ ቡድኑን ከሰውታል፡፡

ኃላፊው እንደሚሉት በክልሉ ንጹሃን ዜጎችን ከትቃት ለመጠበቅና የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚረዳ ወታደራዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በማረጋገጥ የሚወሰዱ እርምጃዎችም በታጣቂዎች ላይ ያነጣጠሩ ብቻ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ለአብነትም በቡኖ በደሌ ወረዳ ጨዋቃ ወረዳ የተወሰደው "ሸማቂውን ቡድን ቡትና ቁስለኛ አድርጓል” ሉት ርምጃ ታጣቂ ቡድኑ ለጥቃት ሲዘጋጅ የተወሰደ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

ኦሮሚያ ክልል፤ ኢትዮጵያ
በኦሮሚያ ክልል ይፈጸማሉ ስለተባሉት ግድያዎችና ወታደራዊ እርምጃው የመንግስት ምላሽምስል Seyoum Getu/DW

መንግስት ወታደራዊ ርምጃውን በሚወስድበት ጊዜ ለንጹሐን ዜጎች ምን ያህል ይጠነቀቃል የተባሉት የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው፤ "ለአሸባሪ ቡድን የሞራልና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ወንጀል በመሆኑ ድጋፍ የሚሆኑት ሴሎቹ ላይ እንጂ ንጹሐንን መንግስት አይገድልም” ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ኃይሉ በሺ የሚቆጠሩ ያሏቸው የታጣቂ ቡድኑ አባላት ለመንግስት እጅ ሰጥተው የታሃድሶ ስልጣና በመውሰድ ላይ ናቸውም ብለዋል፡፡

የሆሮጉዱሩ ሰሞነኛ ጥቃት

ኦነግ በዚሁ መግለጫ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ታኅሣሥ 02 ቀን የደረሰውን እህል ለመሰብሰብ በተሸከርካሪ ከወለጋ ወደ ምዕራብ ጎጃም በመሻገር ላይ የነበሩትን ወጣቶች በአባይ ማዶ ቆርቆቤ በሚባል ስፍራ 13 ወጣቶች በፋኖ ታጣቂዎች ተገድለዋል ነው ያለው፡፡ ለዚህም መንግስትን የዜጎች ደህንነት ባለመጠበቅ ከሷል፡፡

መንግስት «ሸኔ» በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) ብሎ በሚጠራውና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በቅርቡ በታንዛንያ የተደረገው የሰላም ስምምነት ጥረቱ መክሸፉን ተከትሎ በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች የፀጥታ ይዞታው መደፍረሱ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ