1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ የመመለስ ጥረት፤ የበቴ ኡርጌሳ ግድያ፤ የሙሉቀን መለሰ ስንብት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 4 2016

ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከሳዑዲ አረቢያ ለመመለስ የጀመረችው ጥረት ድጋፍም ነቀፌታም ተቸሮታል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የፖለቲካ ኦፊሰር የነበሩት የአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ሐዘን እና ቁጣ ቀስቅሷል። ድምጸ መረዋ ከሚባሉ ሙዚቀኞች አንዱ የነበረው ሙሉቀን መለሰ ማረፉ ሲሰማ አድናቂዎቹ በሥራዎቹ የታጀቡ ትዝታዎቻቸውን መለስ ብለው እያስታወሱ ተሰናብተውታል።

https://p.dw.com/p/4egUM
ከሦስት ልጆቿ ጋር ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሰች እናት በአዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ትታያለች
የኢትዮጵያ መንግሥት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ 70 ሺሕ ዜጎቹን ለመመለስ ጥረት መጀመሩን አስታውቋል። ምስል Michael Tewelde/Xinhua/IMAGO

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የሚያዝያ 4 ቀን 2016 መሰናዶ

የኢትዮጵያ መንግሥት “በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግረው በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የሚገኙ” የተባሉ ዜጎችን ለመመለስ የጀመረው ጥረት ፌስቡክን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረ-ገጾች ድጋፍም ትችትም አስተናግዷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ የሚመሩት የባለሥልጣናት ልዑክ ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቅንቶ “በማቆያ ጣቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን” ጎብኝቷል። ልዑካን ቡድኑ ከሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዳደረገ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫዎች ይጠቁማሉ።

በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተጀመረው ጥረት ለሙከርም ሙኸዲን “ጥሩ ጅምር ነው።” ሙከርም “አላህ ለሀገራቸው ያብቃቸው” ሲሉ ጽፈዋል። ደጀን ማሞ “ፓስፖርት ያላቸው ዜጎቻችን ሕጋዊ የሚሆኑበት መፍትሔ ላይ ይሠራ” የሚል ጥቆማ ሰጥተዋል።

ራቢኦ ይማም “እስረኞቹን አስገቡልን፤ የባሕር መንገዱን ዝጉልን፤ በሀገራችን ለወጣቱ የሥራ ዕድል አመቻቹልን” የሚል አስተያየት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ ጉዳዩ ባቀረበው መረጃ ሥር በፌስቡክ ጽፈዋል። “ስደት በእኛ ይብቃን። ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ሀገራችንን ሰላም፣ አድርጉልን” የሚሉት ራቢኦ ያነሱት ሐሳብ የጉዳዩን ውስብስብነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

ከኢትዮጵያ ሳዑዲ አረቢያን ወደ መሳሰሉ የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት የሚሰደዱ አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። የተሻለ የሥራ ዕድል ፈልገው መንገድ የሚገቡት ወጣቶች በሕጋዊ መንገድ ካልተሳካላቸው ጅቡቲ፣ የኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በጦርነት የምትታመሰው የመንን በማቋረጥ ተስፋ ወደሰነቁበት መካከለኛው ምሥራቅ ለመድረስ መሞከራቸው አይቀርም።

በተያዘው ሣምንት ከጅቡቲ የባሕር ዳር በደረሰ የጀልባ አደጋ ሕጻናትን ጨምሮ 38 ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል። ስድስት ደግሞ የገቡበት አልታወቀም። ኢትዮጵያውያኑን ለስደት የሚገፋው ድሕነት ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ጭምር እንደሆነ ይታመናል። ራቢኦ ይማም ግን “ድህነት ዐይኑ ይጥፋ። ስደት የእግር እሳት ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

ቤካ በቀለ “መንግሥት ዜጎችን መመለስ መጀመሩ በጎ ነው። ነገር ግን ሊቢያ ታግተው እዚሕ ማስለቀቂያ የሚጠየቅላቸው ዜጎች ሕይወት አሳሳቢ ነው። በተለይ የተጠየቀው የብር መጠን እና የአከፋፈሉ ሁኔታ ሲታሰብ ጭካኔው ለከት ያጣ በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ቢሰጥበት” የሚል አስተያየት አስፍረዋል።

“በመጡ በማግስቱ ለሚመለሱ ለምን ተጨማሪ ወጪ ይወጣል?” የሚሉት አንዳርጌ ታዬ ደግሞ “ለተፈናቀሉት ዕርዳታ ቢሰጥ ይሻላል” የሚል አቋም አላቸው። እንድሪስ ስዩም “ቢዘገይም ደስ የሚል ዜና፤ ወገን የወገኑን ሕይወት ለማዳን ሲንቀሳቀስ ማየት” የሚል ተስፋ ያዘለ አስተያየት ጽፈዋል።

“አደራ ቶሎ ይጀመር” ያሉት ሙኒር ሳኒ “ሕፃናት ለሆኑት ቅድሚያ ቢሰጥ” የሚል አስተያየት አላቸው። “ወሬ አታብዙ” የሚሉት አቶ አሕመድ ይማም “በእስር ቤት የሚሰቃዩትን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መልሱ” የሚል ጠንከር ያለ ጥሪ አቅርበዋል።

ያሲን ይመር “ምን በሰው ትቀልዳላችሁ? ሙፈሪያት በጎን ትልካለች፤ ይቺ በጎን ትመልሳለች። ሀገሩን ሁሉ የሰው ደላላ አደረጋችሁት” ሲሉ ብርቱ ነቀፋ ሰንዝረዋል። ያሲን የጠቀሱት በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሥር በሚገኘው የውጭ ሀገር የሥራ ዕድሎች በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት በኩል መንግሥት ዜጎችን ወደ ውጭ ሀገራት የሚልክበትን አሰራር ይመስላል። በተያዘው 2016 ብቻ መንግሥት እስከ 500 ሺሕ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት የመላክ ዕቅድ አለው።

ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ ወጣቶች
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ አረቢያ እና ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች መርጃ ድርጅት በመተባበር ባለፉት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በዘመቻ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ሲመልስ ቆይቷል። ምስል Michele Spatari/AFP

“ለምን ይመለሳሉ? እየተጎበኙ የሚያሳይ ምስል ለምን አይታይም? ይህ ምን ያህል ሰቆቃ ላይ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው” ያሉት ሲሳይ በሻሕ ናቸው። ሲሳይ “ከሔዱ በኋላ ከማምጣት በሀገራቸው በነፃነት ሰርተው መኖር እንዲችሉ ማድረግ ብቸኛው መፍትሔ ነው። ያኔ ማንም ከሀገሩ መውጣት አይመኝም። ሰው ከቤቱ በሰላም ወጥቶ መመለስ በማይችልበት ሀገር ምን እንዲሆኑ ነው የምትመልሷቸው?” ሲሉ ተቃውሟቸውን አቅርበዋል።

የአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ የቀሰቀሰው ሐዘን እና ቁጣ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የነበሩት አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ የፈጠረው ሐዘን እና ቁጣ በማኅበራዊ ድረ ገጾች በሰፊው ታይቷል። አቶ በቴ የተወለዱት፣ የተገደሉት እና የተቀበሩት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በምትገኘው መቂ ከተማ ነው። የአቶ በቴ ሥርዓተ ቀብር ትናንት ሐሙስ ተፈጽሟል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር “ጭካኔ የተሞላበት” ያለውን የአቶ በቴ ግድያ በጽኑ ኮንኗል። “በኦሮሞ ታዋቂ ፖለቲከኞች እና የባሕል ሰዎች ላይ የሚፈጸም ምክንያታዊ ያልሆነ እና ከሕግ ውጪ ግድያ ለበርካታ አስርት ዓመታት የዘለቀ ሥልታዊ እና ኃላፊነት የጎደለው ኦሮሞን የማፈን ተግባር” እንደሆነ የገለጸው ኦነግ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች “በአፋጣኝ ገለልተኛ ምርመራ” እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የኦሮሚያ ክልል እና የፌድራል መንግሥት ባለሥልጣናት “አፋጣኝ፣ ገለልተኛ እና ሙሉ ምርመራ በማድረግ ገዳዮችን ተጠያቂ እንዲያደርጉ” ጠይቀዋል። የአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ላይ ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረበችው አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ የኤክስ ገጽ በኩል “የግጭት አዙሪትን ለመስበር ፍትኅ እና ተጠያቂነት ወሳኝ ናቸው” የሚል መልዕክት አስተላልፋለች። 

የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ “በርካቶች ጦርነትን ወደ ማነሳሳት እና ጽንፈኝነት ባዘነበሉበት ወቅት” በቴ “እጅግ ከተረጋጉ እና ለኹከት አልባ ትግል ቁርጠኛ ከነበሩ ጥቂት ፖለቲከኞች አንዱ” እንደነበሩ ጽፈዋል። ለተደጋጋሚ እስር እና ስቅየት ቢዳረጉም አቶ በቴ ኡርጌሳ “የበቀል ፖለቲካን” አለመቀበላቸውን አቶ ጃዋር ገልጸዋል።

በግል የፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር ሐተታ “እውነቱን ለማወቅ፣ ለበቴ እና ለትንንሽ ልጆቹ ፍትኅ ለመስጠት ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሔድ መጠየቅ ተገቢ በሆነ ነበር” ያሉት ጃዋር “ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ዕልባት ሳያገኙ እንደቀሩት በርካታ ግድያዎች ሁሉ ይህ ሊሆን እንደማይችል ሁላችንም እናውቃለን” ሲሉ ጽፈዋል።

አስቻለው ደረጄ “ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሒቃን እንደ ጃል በቴ ኡርጌሳ የተረጋጋ ስብእና ያለው፣ ባለ ጣፋጭ አንደበት፣ በሳል እና ጨዋ ሰው እስከ ዛሬ ድረስ አላየሁም። በቴለቪዥን መስኮት እርሱን ካየሁበት ጊዜ ጀምሮ በአፋን ኦሮሞ እና በአማርኛ ያደረጋቸውን ቃለ-መጠይቆች እና ንግግሮችን ተከታትያለሁ። ያመነበትን የፖለቲካ መስመር በጥልቀት እና በሰከነ አኳሃን (ሌሎችን ሳያስከፋ) ሲገልጽ ወደር የለውም” ሲሉ በፌስቡክ ጽፈዋል።

ውብሸት ታዬ “በሕይወቴ ከማውቃቸው የሰከኑ፣ አስበው የሚናገሩ፣ የሌሎችን ሃሳብ ከሚያከብሩ፣ በሐሳባችሁ ባይስማሙ እንኳ ከማይጋፏችሁ በጣም ጥቂት ሰዎች አንዱ ነው። ለጥቂት ደቂቃዎች ለሚያውቀው ሰው እንኳ እርጋታው እና ትህትናው አእምሮ ላይ ታትሞ የሚቀር ሰው ነው” በማለት ጽፈዋል።

አወል ቃሲም “ለሕዝባቸው እውነት እና ነጻነት ዕድሜ ልካቸውን ኖረው የሞቱ” ሲሉ በቴ ኡርጌሳን ገልጸዋቸዋል። ታሪቅ ዲን ናምሩድ “ምንም በሐሳብ የተራራቅን ቢሆንም ሀሳብ በሀሳብ መሞገት እንጂ በመሣሪያ አፈሙዝ ሊሆን አይገባም ነበር” ሲሉ ግድያውን ኮንነዋል።

ታዬ ቱለማ “ጃል በቴ የፓለቲካ ሊቅ ብቻ ሳይሆን በተግባር የተፈተሸ የነፃነት ታጋይም ነበረ። የብሔረሰቦች መብት እና ሕብረ ብሔራዊ ፌድራሊዝም ላይ ጽኑ አቋም ነበረው” ሲሉ የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ላይ ባሰፈሩት አጭር ጽሑፍ ዘክረዋቸዋል።

የሙሉቀን መለሰ ስንብት

በኢትዮጵያ ሙዚቃ “ድምጸ መረዋ” ከሚባሉ መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀስ የነበረው ሙሉቀን መለሰ ለረዥም ዓመታት በኖረበት አሜሪካን ሀገር ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ሲሰማ አድናቂዎቹ በማኅበራዊ ገጾች ሐዘናቸውን ገልጸዋል። በ69 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የሙሉቀን ሥርዓተ-ቀብር ዛሬ ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2016 በአሜሪካ ሀገር ይፈጸማል።

ሙሉቀን በአማርኛ የሙዚቃ ሥራዎቹ ከፍ ያለ ተቀባይነት ካገኙ የኢትዮጵያ ድምጻውያን አንዱ ነበር። በ1980ዎቹ ከዓለማዊ ሙዚቃ ወደ መንፈሳዊ መዝሙር ፊቱን ቢያዞርም እርሱ እና ሥራዎቹ የነበራቸው ተወዳጅነት ግን ፈጽሞ አልቀዘቀዘም።

ዳንኤል በቀለ ፌስቡክ ላይ ያሰፈሯት ጽሑፍ የሙሉቀን መለሰ ሥራዎች በአድናቂዎቹ ዘንድ ያላቸውን ሥፍራ የምትጠቁም ናት። “ያላንተ ዘፈኖች ስላለፈ ሕይወታቸው እና ገጠመኞቻቸው ብዙም ትዝታ የሌላቸው ብዙ ሰዎች አውቃለሁ። ራሴንም ጨምሮ” ይላሉ ዳንኤል።

“ለብዙ ራሳቸውን እና የውስጣቸውን ጭንቀት፣ ሐዘን፥ ደሰታ እና በውስጣቸው የሚፍለቀለቀውን ስሜት መያዣ መጨበጫው ለጠፋባቸው፣ ስሜታቸውን መግለጽ ላልቻሉ፣ ላፈቀሩ እና ለተጎዱ ልቦች ትልቅ ድምጽ መሆን የቻልክ ትልቅ የጥበብ ሰው ነበርክ” ሲሉ ጽፈዋል። 

ብሩክ ተፈራ “ዘመን ተሻጋሪ ኮከብ” ብለውታል። ዳዊት ተስፋዬ “ዜማ እና ድምጽህ ከእንባ እና ሳቃችን ጋር የተሸመነ የዘመናችን ጣዕም ነበርክ” ሲል ገልጸውታል። “የእናቴ ወዳጅ፣ የልጅነቴ ሳውንድ ትራክ” ሲሉ የገለጹት ቤተልሔም ነጋሽ ናቸው።

ማዕዶት “ያልተፈጠርንባቸውን ያልኖርንባቸውን ዘመኖች የኛ ያረገ፤ የኔ የሁልጊዜ አንደኛ” ሲሉ አሞካሽተውታል። ይኑስ “የሙዚቃ ገበያው እንዲህ በኣልበም ሳይጥለቅለቅ ለሦስት ወር ኣዲስ ሙዚቃ ካልወጣ ራዲዮው በሙሉ ወደሱ ሙዚቃ ነበር የሚመለሰው» በማለት የነበረውን ተጽዕኖ አስታውሰዋል።

“በወቅቱ ተደስተንበታል፣ ቆዝመንበታል፣ ትዝታችንን አከማችተንበታል” ያሉት ሰሎሞን ወጋየሁ “መልካም እረፍት ይሁንልህ ሙሉቀን መለሰ” ሲሉ ጽፈዋል። ደረጄ መላኩ “የሙዚቃችን ደሳሳ ቤት ዛሬ ከጣራ ክዳኗ አንዱ ጥሏት ሔደ። የሙዚቃችን ጽዋ ዛሬ ተሰንጥቃ ለዘመናት ያጎመራነው ወይን ጠጃችን ፈሰሰብን” በማለት የተሰማቸውን ገልዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ