1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍኒ፤ የሲዳማ ባህላዊ የግጭት አፈታት

ሐሙስ፣ ሐምሌ 13 2015

በዚህ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴ ከቀላል ዛቻ ፣ ስድብ እና የቤተሰብ ግጭት፣ እስከ የነብስ ግድያ ያሉ ከባድ ግጭቶች ድረስ የሚስተናገዱ ሲሆን፤ ሽምግልናውም የሚከናወነውም በተናጠል ሳይሆን በሸንጎ ወይም በጉባኤ ነው።የሴት ልጅ ግርዛት፣ አስገድዶ መድፈር እና ጠለፋ ሽማግሌዎቹ ለእርቅ የማይቀመጡባቸው ጉዳዮች ናቸው።

https://p.dw.com/p/4UCJn
Äthiopien | Konfliktlösung in der Region Sidama
ምስል privat

የሲዳማ ባህላዊ እርቅ


በሰው ልጆች ማህበራዊ መስተጋብር ውስጥ ከግል እና ከቡድን ጥቅም አኳያ  እንዲሁም ከፍላጎት እና ከአስተሳሰብ ልዩነት በመነጨ የግጭቶች መከሰት የተለመደ ነው። እነዚህን ግጭቶች ከመደበኛ የፍትህ ተቋማት ባሻገር   እንደየ ማህበረሰቡ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ እና እምነት  ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችም አሉ።
የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ባህሎች ፣ ቋንቋዎች እና ሀይማኖቶች ሀገር  በሆነችው ኢትዮጵያም ግጭቶችን ለመፍታት የሚያገለግሉ የተለያዩ ባህላዊ የሽምግልና ዘዴዎች አሉ። ከነዚህም መካከል በሲዳማ ብሄር የሚከወነው አፍኒ የተባለው የግጭት መፍቻ ዘዴ አንዱ ነው። በሲዳማ ክልል ባህል ፣ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የባህል ፣ታሪክ እና ቅርስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሌዳሞ እንደሚሉት የሲዳማ ብሄር  ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን የሚፈታበት የራሱ ባህላዊ መንገድ አለው።
በዚህ  ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴ ከቀላል የቤተሰብ ግጭት፣ ዛቻ እና ስድብ እስከ የነብስ ግድያ ያሉ ከባድ ግጭቶች ድረስ የሚስተናገዱ ሲሆን፤ ሽምግልናውም የሚከነወነውም በተናጠል  ሳይሆን በሸንጎ ወይም በጉባኤ ነው።
የአፍኒ ሽምግልና አራት ደረጃዎች አሉት።የመጀመሪያው ቦሳሊ ሶንጎ በመባል የሚጠራ ሲሆን፤ የተጋጨ ቤተሰብ ጉዳያችን ደጅ አይውጣ ብሎ ተስማምቶ በምድጃ ዙሪያ የሚሸማገልበት የቤተሰብ ጉባኤ ነው። ሌላው እና ሁለተኛው ኡሉ ሶንጎ በመባል የሚጠራው ሲሆን፤ ከቤተሰብ አልፎ  በጎርብትና እና በሰፈር ደረጃ የሚፈጠሩ ግጭቶች የሚፈቱበት ነው።
በዚህ የእርቅ ስርዓት አንደኛው  ወገን ሽምግልናው አልተስማማኝም ወይም የተሰጠኝ ፍትህ ተገቢ አይደለም ብሎ ቅሬታ ካቀረበ ወደሚቀጥለው እና አያዱ ሶንጎ ወደ ሚባለው ሶስተኛ የሽምግልና ደረጃ ይቀጥላል።
የዚህ ሸንጎ ውሳኔ ቅሬታ እና ይግባኝ የለውም።ውሳኔውን የማይቀበል ሰውም በሽማግሌዎች ቅጣት ይጣልበታል።በሚኖርበት አካባቢም በማህበራዊ መስተጋብሩ ላይ ዕቀባ ይደረግበታል።    
የመጨረሻው እና አራተኛው የሽምግልና እርከን ደግሞ ሞተተ ሶንጎ ይባላል።በዚህ ሸንጎ ከበድ ያሉ ጥፋቶች እና ከጎሳው ውጭ ያሉ ግጭቶች ጭምር የሚፈቱበት ነው።
አቶ ሻምበል በላይ በአቤላ ወረዳ የጎሳ መሪ ሆነው በአራተኛው የሽምግል እና እርከን ለ14 ዓመታት ሰርተዋል።ሽምግልና የጀመሩት  አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ  በውርስ ነው። ከቀላል እስከ ከባድ ግጭቶች ድረስ ብዙዎችን አንተም ተው አንቺም ተይ ብለው አስማምተዋል።ከክልል ውጭ በተከሰቱ ግጭቶችም ለሽምግልና ተቀምጠዋል።
የሽምግልናው ሂደት የሚጀምረው የተበዳይን ስሞታ በመቀበል ነው የሚሉት አቶ ሻምበል በሽምግልናው ሴቶችን ማሳተፍ ቀደም ሲል ያልነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን ሴቶችም እየተሳተፉ መሆኑን ገልፀዋል።ከዚህ በተጨማሪ የሴት ልጅ ግርዛት፣ አስገድዶ መድፈር እና ጠለፋ ሽማግሌዎቹ ለእርቅ የማይቀመጡባቸው ጉዳዮችም ሆነዋል።  
አቶ ተፈራ እንደሚሉት ሽማግሌዎቹ ለተበደለው ፍርድ የሚሰጡት በእውነት እና በጥበብ በሲዳማኛ አጠራር ሀዮ እና ሃላሌ ላይ ተመርኩዘው ሲሆን እርቁም የቀደመ ምህበራዊ ግንኙነት እንዲቀጥል ቤተሰባዊ እንዲሆኑ ከአንገት ሳይሆን ከአንጄት ነው ። ያም ሆኖ በደለም ቅጣት ይጣልበታል ካሳም ይከፍላል።በተለይ በነብስ ግድያ  ላይ የሚደረገው ሽምግልና ጠበቅ ያለ መሆኑን ገልፀዋል። 
ሽምግልናው ከተጠናቀቀ በኌላም በመካከላቸው ያለውን ጥቁር ቂም መፈታቱን ለማሳየት   በተምሳሌትነት ጥቁር በግ ይታረዳል የሚሉት አቶ ተፈራ፤በጉን በደል ያደረሰው ወገን ያለምንም አጋዥ ብቻውን እንዲያርድ ይደረጋል። ይህም ጥፋቱን የሰራው ብቻውን መሆኑን ለማሳየት ነው ይላሉ።
ይህንን  ይዘው  ወራጅ ወንዝ ያለበት ቦታ በመሄድ በዳዩን እና ተበዳዩን ማዶ እና ማዶ በማድረግ ማር የተቀላቀለበት ውሃ ሁለቱንም ወገኖች ይረጫሉ።ይህም እርቅ መውረዱን በመካከላቸው መራራ ጠብ ሳይሆን ጣፋጭ ሰላም መኖሩን ያሳያል።በመጨረሻም በአንድ ቡልኮ ውስጥ ሆነው እንዲመገቡ ይደረጋል።
በዚህ መልኩ የሚከናወኑ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች  አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰላም እንዲሰፍን በአቅራቢያ ፍርድ ቤቶች በሌሉባቸው ቦታዎች ደግሞ ጊዜን ወጭን እና እንግልትን ያስቀራሉ።በአንፃሩ  አጥፊን የሚቀጣ ተመጣጣኝ ፍትህ አይገኝም፣ የህግ የበላይነትን አያስከበርም በማለት የሚከራከሩ አሉ።የሀገር ሽማግሌው አቶ ሻምበል በላይ ግን  ይህ መሰሉ ባህል ለሀገር ጠቃሚ ነው  ይላሉ። አቶ ተፈራ ሌዳሞም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ችግሮች ይህ መሰሉ ባህላዊ የግጭት አፈታት እየተረሳ በመምጣቱ   ነው ።ሲሉ የሀገር ሽማግሌውን   ሀሳብ ያጠናክራሉ።ከዚህ አኳያ የአቶ ተፈራ ሌዳሞ የሚሰሩበት መስሪያቤት የሲዳማ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ  ባህሉን ለማሳደግ ከሽማግሌዎች ጋር ውይይት እና ስልጠና እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

Äthiopien | Konfliktlösung in der Region Sidama
ምስል privat
Äthiopien | Konfliktlösung in der Region Sidama
ምስል privat
Äthiopien | Konfliktlösung in der Region Sidama
ምስል privat
Äthiopien | Ato Tefera Ledamo
ምስል privat

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ዮሀንስ ገብረ እግዚአብሄር