1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃውሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መግለጫ ላይ

ሐሙስ፣ ሰኔ 8 2015

መግለጫውን በመግለጫ የተቃወሙት ፓርቲዎች 32 መሆናቸውን መግለጫውን የሰጡት ግለሰቦች ተናግረዋል።32 ቱ ፓርቲዎች እነማን እንደሆኑና አቋሙን መደገፋቸውን በፊርማና ማህተም ያረጋገጡበትን ሰነድ ብንጠይቅም አላቀረቡም።የጋራ ም/ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ግን"አይደለም 32 አሥርም አይደርሱም። የግል ፍላጎታቸውን ነው ያንፀባረቁት" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4SbGf
Äthiopien   Ethiopian political parties joint council
ምስል Solomon Muchie/DW

ተቃውሞ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መግለጫ ላይ

«መርህ ይከበር» ያሉ ጥቂት የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም "መንግሥት ሀገርን ከከፋ ቀውስ እና ብጥብጥ እንዲታደግ፣ በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸረ ነው ያለውን የፖለቲካ ምህዳር እንዲያሰፋ" የጠየቀበትን መግለጫ ተቃወሙ። የተቃውሞ መግለጫ ያቀረቡት ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ የማይጠይቅ ከሆነ ጉዳዩን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማሳወቅ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንደሚያቋቁሙ ገልፀዋል። ተቃውሞውን ያሰሙት የፖለቲካ ድርጅቶች ይህ አቋም በ32 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደገፈ መሆኑን ቢገልፁም 32 ቱ ፓርቲዎች እነማን እንደሆኑ በግልጽ እንዲያሳውቁ ቢጠየቁም ይህን ማድረግ አልቻሉም።ቅሬታው የቀረበበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በበኩሉ" ምንም የጣስኩት የአሰራር መርህ የለም" ያለ ሲሆን ይህንን መግለጫ ያወጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ "አስተዳደራዊ እርምጃ እወስዳለሁ" ሲል አስታውቋል።
ገዥው ብልጽግና ፓርቲ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ "ግጭት እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ዜጎችን ለሞት ፣ ለአካል መጉደል ፣ መፈናቀል እና የሥነ ልቦና ስብራት እየዳረጉ ነው፣ መንግሥት ሀገርን ከከፋ ቀውስ እና ብጥብጥ እንዲታደግ" በማለት ጠይቆ ነበር።ትናንት  "መርህ ይከበር" በሚል ጥቂት ክልላዊ እና ሀገር አቀፍ መሆናቸውን የጠቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች የ 32 ፓርቲዎች አቋም ነው በማለት አባል የሆኑበትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት "ሥራን በዘፈቀደ በማከናወን፣ በፓርቲዎች አመራሮች መካከል አድልዎ በመፈፀም ፣ አንዱን በአንዱ ላይ በማነሳሳት" ከሰውታል። በጋራ እንዲሰባሰቡ ያደረጋቸው የጋራ ምክር ቤቱ መርህ ተደጋግሞ ተጥሷልም ብለዋል። ይህንን አካል የሰበሰቡት የአገው ሸንጎ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አላምረው ይርዳው ናቸው።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ተቋሙ ስለቀረበበት ተቃውሞ ጠይቀናቸው ተከታዩን መልሰዋል። "በመግለጫው ኢትዮጵያ ያለችበትን አሁናዊ ሁኔታ ነው ያስቀመጥነው። ያንን በመቃወም ሦስት እና አራት ፓርቲዎች ናቸው የተቃውሞ መግለጫ ያወጡት። ይህ የጋራ ምክር ቤቱን መርህ የጣሰ ስለሆነ በእነዚህ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ የምንወስድ ነው የሚሆነው" ብለዋል። የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰኔ 2 ቀን ባወጣው መግለጫ ስለ ሃይማኖት ጉዳይ እና የፓርቲ አመራሮች እሥር እና እንግልት የተጠቀሰው ከተወያየንበት ውጪ አቋም ያልያዝንበት ነው ያሉት የህዳሴ ፓርቲ ፕሬዝደንት ሱራፌል እሸቱ በወቅቱ ባመግለጫው የተላለፈው መልእክት በጋራ ምክር ቤቱ አመራርነት ላይ ያሉ የጥቂት ፓርቲዎች ፍላጎት ነው፣ በመሆኑም የጋራ ምክር ቤቱ ይቅርታ ካልጠየቀና አሰራሩን ካላስተካከለ ወደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመሄድ ሌላ የጋራ ምክር ቤት እናቋቁማለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ሆነው ምክር ቤቱ ያወጣውን መግለጫ በመቃወም መግለጫ ያወጡት ፓርቲዎች 32 መሆናቸውን ይህንን መግለጫ የሰጡት ግለሰቦች ተናግረዋል። ይሁንና 32 ቱ ፓርቲዎች እነማን እንደሆኑና ይህንንም አቋም መደገፋቸውን በፊርማና ማህተም ያረጋገጡበትን ሰነድ ብንጠይቅም ሊያቀርቡ አልቻሉም።የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ግን"አይደለም 32 አሥርም አይደርሱም። የግል ፍላጎታቸውን ነው ያንፀባረቁት" ብለዋል።የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ወደ 61 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈ ነው። ይሁንና የጋራ ምክር ቤቱን አሠራር ያልተቀበሉ አሥር የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ በሚል ለብቻቸው ከዚህ ማዕቀፍ ውጪ ይንቀሳቀሳሉ።


ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ