1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርጫ እንዲካሄድ ጠየቀ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 8 2016

ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሕዝብ ተወካዮች፣ የክልል፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ እንዲካሔድ ጥሪ አቀረበ። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ጽህፈት ቤት የጸጥታው ሁኔታ ምርጫ ማካሔድ የሚያስችል መሆኑን ማረጋገጥ ያለበት መንግሥት እንደሆነ ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4Z8G7
ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሕዝብ ተወካዮች፣ የክልል፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደሮች ምርጫ እንዲካሔድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ ምስል Boro Democratic Party

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርጫ እንዲካሔድ ጠየቀ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፓርቲ በክልሉ በስድስት ወር ውስጥ  ምርጫ እንዲካሄድ እንዳለበት ጠየቀ።ፓርቲው በክልሉ በ2013 ዓ.ም በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ በአብዛኛው የክልሉ ስፍራዎች አለመካሄዱን ገልጾ ምንም እንኳ የክልሉ ሠላም ሁኔታ ቢሻሻልም የምርጫ  ጉዳይ መጓተቱን ገልጸዋል፡፡ 

የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ በድርጅቱ አባላት ላይ የተለያዩ ጫናዎችና እስራቶች  እየተፈጸሙ እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡ በክልሉ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ ምርጫ እንዲካድ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ሰሚ ማጣቱን ጠቁሟል፡፡ በፓርቲው የቀረበውን ቅሬታ አስመልክቶ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንና ሰላም ግንባታ መረጃ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸው አልተሳካም።

ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምርጫ ጥሪ በቦሮ ፓርቲ

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽ ኮሚሽነር ሀሩን ኡመር መረጃ እንደሚሰጡን ቃል ቢገቡም በቀጠሮው መሰረት ስልክ ቢደውልም ስልክ አያነሱም፡፡ በአካል ቢሮአቸው ድረስ በመሄድም ማግኘት አልተቻለም፡፡ 

የቦሮ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙት ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ውስጥ የተለያዩ ጫናዎች እየደረሱበት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የድርጅቱ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዩሐንስ ተሰማ የፓርቲአቸው አባላትና ደጋፊዎች በሰላማዊ መንገድ የሚደርጉአቸው እንቅስቃሴዎች በተለያዩ ጊዜያት እየተደናቀፈ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በቅርብ በመተከል ዞን ውስጥ የድርጅታቸው አባላት ታስረው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ 

Äthiopien Addis Abeba | Boro-Partei, EInweihungstreffen | Ato Yohannis
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የፖለቲካ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ የቤኒሻንጉል የጸጥታ ሁኔታ በመሻሻሉ ምርጫ ማካሔድ ይቻላል የሚል አቋም ፓርቲያቸው እንዳለው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Negassa Dessalegn/DW

በክልሉ በነበረው ጸጥታ ችግር ለረጅም ጊዜ ምርጫ ሳይካሄድ መቆየቱን የገለጹት አቶ ዮሐንስ ተሰማ ባሁኑ ወቅት የክልሉ የሰላም ሁኔታ በመሻሻሉ የክልል ምክር ቤት፣የከተማ እና ወረዳ ምክር ቤት ምርጫ በስድስት ወራት ውስጥ እንዲካሄድ ፓርቲው ሰሞኑን ባካሄደው የስራ አሰፈጻሚ ጉባኤ መስማማቱን አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም በክልሉ በጸጥታ ችግር የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመጠገን እና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም  ስራ በቶሎ መሰራት እዳለበትም አመልክተዋል። 

የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ ፓርቲ አመራሮች ውዝግብ

በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ታቅዶ እንደሆነ የጠየቅናቸው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ታደሰ ለማ መረጃ የማሰበሰብና ልዩ ልዩ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች  በቦርዱ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም   በክልሉ ምርጫ መካሄድ አለበት ወይም የለበትም ለሚለው የሰላም ጉዳይ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ጸጥታን  ማረጋገጥ ያለበት መንግስት መሆኑን አስታውቋል፡፡  

አሶሳ ከተማ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መሆኑን የክልሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ምስል Negassa Dessalgen/DW

የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ እና የፖለቲካ ፓርቲውን ቅሬታ አስመልክቶ ማብራሪያ ከጸጥታ ዘርፍ ከሚመሩ የስራ ኃላፊዎች መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሐሩን ዑመር ዛሬ ከቀኑ አራት ሰዓት እንዲንደውልላቸው ቃል ቢገቡም በተባለው ሰዓት ስልክ ብንደውልላቸውም ስልካቸው አይነሳም፡፡ በአካል በተቋማቸው  ቢንገኝም ማገኘት አልቻለም፡፡ ከዚህ ቀደም  በክልሉ ጸጥታ ጉዳይ  እንደተናገሩት ከተወሰኑ ስፍራዎች ውጪ በክልሉ አብዛኛው ስፍራዎች መደበኛ የስራ እንቅስቃሴ መጀመሩን  አብራርተዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ምርጫ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን በወቅቱ የኮድ ስህተት በመፈጠሩ ምርጫው ለጊዜ መቋረጡን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ገልጸዋል፡፡ ቦርዱ ምርጫ ለማካሄድ በ2014 ዓ.ም አውጥቶ የነበረውን ጊዜዊ መርሀ ግብር በጸጥታ ችግር መኖሩን ጠቅሶ ሰርዟል፡፡ በሰኔ/2013 ዓ.ም በአሶሳ ዞን ተካሄዶ በነበረው ምርጫ 6 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፏል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ
እሸቴ በቀለ