1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ጉዳይ የሰባት ሀገራት የጋራ ጥሪ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2016

ኢትዮጵያ ውስጥ የተወሳሰቡ የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውሶችን ለመፍታት ብሎም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ብቸኛው መንገድ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት ማድረግ መሆኑን በኢትዮጵያ የሚገኙ የ 7 ሀገራት ኤምባሲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ገለፁ።

https://p.dw.com/p/4f2dQ
Deutschland Münster | Flaggen G7
ምስል Wolfgang Rattay/AFP/Getty Images

በኢትዮጵያ ጉዳይ የሰባት ሀገራት የጋራ ጥሪ

ሀገራቱ ውዝግብ በተነሳባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች "እየደረሰ ያለው ጥቃት" እንዳሳሰባቸው በጋራ መግለጫቸው አስታውቀዋል። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባባሪያ ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው "የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ችግር ሰላማዊ፣ ሕጋዊ ፣ እና የሕዝብ ወሳኝነትን ባረጋገጠ አኳዃን መፍትሔ የሚያገኝበትን ሁኔታ ለመፍጠር ውይይቶች ተደርገዋል፣ ስምምነት ላይም ተደርሷል" በማለት ከዚያ ውጭ ያለው አማራጭ የፕሪቶሪያን ስምምነት የሚጥስ መሆኑን ሰሞኑን ገልፀዋል። 

በራያ ዜጎችን ያፈናቀለውንና ሰሞኑን ያገረሸውን ችግር አስመልክቶ አስተያየት የጠየቅናቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ "የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የግልጽነት ጉድለት ነው" በማለት የችግሩ ምንጭ ያሉትን ተናግረዋል።


ኤምባሲዎቹ ምን አሉ ?

በአዲስ አበባ የሚገኙት የካናዳ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የጃፓን፣ የእንግሊዝ እና የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲዎች "የተወሳሰቡ የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውሶችን ለመፍታት እና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉንም ባለድርሻዎች ያሳተፈ ውይይት ብቸኛው መንገድ ነው።" ብለዋል። ኤምባሲዎቹ ይህንን ያሉት ትግራይ እና አማራ ክልሎች ከሚወዛገቡባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው ራያ ሰሞኑን 29 ሺህ በላይ ሰዎችን ያፈናቀለ ሌላ ዙር ችግር መከሰቱን ተከትሎ ነው። ክስተቱን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግሥት "ሕወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ጥሶ አራተኛ ዙር ወረራ ፈጸመ" በሚል መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ ኢዜማ እና አብንም ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ አውጥተዋል።

የፖለቲካ ተንታኝ አስተያየት 

በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን የጠየቅናቸው አንድ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ "የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የግልጽነት ጉድለት ነው" በማለት የችግሩ ምንጭ ያሉትን ጠቅሰዋል።
"የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ምንድን ነው ተብሎ ቢነሳ በአጠቃላይነት የዚህ የግልጽነት ጉድለት ነው" ። የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች አሁንም የግጭት እና የጦርነት መነሻ የመሆን ሥጋት እንዳለባቸው ይነገራል። "ወደ ተኩስ የተገባበት ዋናው ጉዳይ ምንድን ነው ተብሎ መጠየቅ ነበረበት፤ በፕሪቶሪያው ስምምነት።" የሚሉት ተንታኙ ነገሩ ምናልባት ለፖለቲካ ውይይት የተተወ ጉዳይ መሆን እንዳልነበረበት ገልፀዋል።በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየተሰራ ነው ተባለ

የፌዴራል መንግሥቱ ምላሽ 

ይህ ክስተት ከተፈጠረ በኋላ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባባሪያ ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው አጭር ማብራርያ ሰጥተዋል። "በግጭት ፣በትንኮሳ፣ ሕዝቡን ማኅበራዊ እረፍት በመንሳት ሊፈታ የሚችል ችግር የለም ተብሎ ነው ውይይቶችና ምክክሮች ሲደረጉ የነበሩት" ብለዋል። 

Symbolbild I Äthiopien - Humanitäre Lage
ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ብቸኛው መንገድ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት ማድረግ እንሆነ የቡድን 7 ሀገራት ገለፁምስል Ed Ram/Getty Images

ከነገሮች ጀርባ ምን ይኖር ይሆን?

የፌዴራል መንግሥቱ ከጦርነቱ በኋላ የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸውን ቦታዎች የያዙትን አካላት በግልጽ በውይይት አለማሳተፉን እንደ አንድ ችግር የሚገልጹት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ተንታኙ ፣ በትግራይ በኩል የትግራይ ሉዓላዊነት በሚል የሚነሳው ሀሳብም "የክልል ሉዓላዊነት" የሚባል ነገር ካለመኖሩ አንፃር ትክክል አለመሆኑን ይጠቅሳሉ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በእነዚህ ቦታዎች የሚስተዋለው ግጭት "በትግራይ እና በአማራ ወይም በትግራይ እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል የተፈጠረ አይደለም" ማለታቸውና ግጭት ሲያገረሽ የመከላከያ ሠራዊት ምን አደረገ? በሚለው ዙሪያ ያስተዋሉትን ገልፀዋል።

"ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ታዛዥነት ያፈነገጠ ኃይል ይሆን ወይ? በአንድ በኩል ይህንን መገመት ተገቢ ነው ብዩ እወስዳለሁ። ከዚያ ውጭ ደግሞ 'ሳይለንት' ትብብር በፌዴራል መከላከያ ሠራዊት በኩል ታይቷል።" ብለዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት የ ሰባቱ ሀገራት ኤምባሲዎች  "ሁሉም ወገኖች ትጥቅ ማስፈታት፣ ታጣቂዎችን መበተን እና የተፈናቀሉ ዜጎችን በሰላም ወደነበሩበት የመመለስ ጉዳይ ላይ አሁንም እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ሰለሞን ሙጬ
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ