1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአላማጣ «ከፌደራል የፀጥታ ተቋማት ጋር ያጋጠመ አንድም ነገር የለም» ሕወሓት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 8 2016

የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ጠላት የሆኑ ኃይሎች ግጭት ለመፍጠር እየጣሩ ነው ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሱ።

https://p.dw.com/p/4er9F
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፈራሚዎች ከአፍሪቃ ኅብረት አደራዳሪዎች ጋር
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ፈራሚዎች ከአፍሪቃ ኅብረት አደራዳሪዎች ጋርምስል PHILL MAGAKOE/AFP

በአላማጣ ግጭት እና የነዋሪዎች በገፍ መፈናቀል

የፕሪቶርያው «የሰላም ስምምነት ጠላት የሆኑ ኃይሎች ግጭት ለመፍጠር እየጣሩ ነው» ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሱ። አቶ ጌታቸው በይፋዊ ማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ክስተቱ ሁለቱ ወገኖች የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እያደረጉት ያለውን አወንታዊ ግንኙነት ለማደናቀፍ የሚፈልጉ «የስምምነቱ ጠላቶች» የፈጠሩት ነው ብለዋል። ሕወሓት በአላማጣ ግጭቱ ከፌደራል የፀጥታ ተቋማት ጋ ሳይሆን ከአካባቢው ሚሊሺያዎች ጋ መሆኑንም ዐስታውቋል ።  

ሰሞኑን በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ዕየታዩ ስላሉ ግጭቶች የጻፉት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በደቡብ ትግራይና በሌሎች በኃይል በተያዙ የትግራይ ግዛቶች፥ እየታየ ያለው ክስተት በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አልያም በህወሓት፥ ወይም ደግሞ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት አይደለም ሲሉ ገልፀዋል። አቶ ጌታቸው በይፋዊ ማሕበራዊ የትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሑፍ ክስተቱ ሁለቱ የስምምነቱ ፈራሚ ወገኖች የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ  እያደረጉት ያለውን አወንታዊ ግንኙነት ለማደናቀፍ የሚፈልጉ "የስምምነቱ ጠላቶች" የፈጠሩት ነው ብለዋል። አቶ ጌታቸው ጨምረውም ተግዳሮቶችን ለመፍታት እና የጋራ መግባባት ለመገንባት ሁለቱ ወገኖች አሁን ላይ በአዲስ አበባ እየመከሩ መሆኑ ጠቁመዋል።

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በትግራይ ደቡባዊ ዞን በሚገኙ እና ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች በጦር መሳርያ የታገዘ ግጭት እየታየ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ትላንት ከአላማጣ ከተማ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ነዋሪዎች በበኩላቸው ግጭቶች በመስጋት ሰላማዊ ዜጎች ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ መሆኑ ገልፀውልናል።

በሩቅና ቅርብ ያሉ የሰላም ስምምነቱ ጠላቶች ያልዋቸው ሐይሎች ያለው ብቸኛ አማራጭ ሰላም መሆኑ መገንዘብ እንዳለባቸው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ጨምረው ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሐን ማብራርያ የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው የፕሪቶርያው ውል ከተፈረመ  ዓመት ከመንፈቅ ቢያልፍም፥ ውሉ በሙሉእነት እንዳይተገበር እንቅፋት የመፍጠር ስራ፣ ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ የማድረግ ተግባር ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ዜጎች የማፈናቀል እንቅስቃሴ መኖሩ ያነሱ ሲሆን ይህ የሚደርጉ ደግሞ በሐይል በተያዙ ባሏቸው አካባቢዎች ባሉ አስተዳደሮች የተደራጁ ታጣቂዎች ናቸው ብለዋል። በቅርብ ቀናት የተፈጠረው ግጭትም የአካባቢው ሚሊሻዎች እና ሕገወጥ አስተዳደሮቹ ባደራጇቸው ታጣቂዎች መካከል መሆኑ ጀነራል ታደሰ ወረዳ ገልፀዋል።

የፕሪቶርያው ስምምነት በተፈረመበት ወቅት ። ፎቶ፦ ከማኅደር
የፕሪቶርያው ስምምነት በተፈረመበት ወቅት ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Themba Hadebe/AP/picture alliance

ጀነራል ታደሰ "ታጣቂዎቹ ከነበሩበት አካባቢ ተንቀሳቅሰው በሚልሻዎቻችን ላይ ተኩስ የሚፈጥሩበት ሁኔታዎች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ክረምቶች ያለፉት የመመለሻው ቀን በጉጉት የሚጠብቅ ተፈናቃይም አለ። በተፈናቃዮቹ በኩል የሚታይ የመግፋት ነገርም አለ። በዚህ ምክንያት ያጋጠመ ግጭት አለ። ግጭቱ በአካባቢው ባለ አስተዳደር ካደራጀው ታጣቂ ጋር የሚደረግ እንጂ ከፌደራል የፀጥታ ተቋማት ጋር ያጋጠመ አንድም ነገር የለም" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ጀነራል ታደሰ በሐይል በተያዙ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ያለ ሁኔታ መቀየር እንዳለበት አስተዳደራቸው እንደሚያምን ያነሱ ሲሆን ይህ የሚሆነው ግን በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑ ተናግረዋል። ጀነራሉ "ሁኔታው መቀየር አለበት። ይሁንና በሐይል ማስፈፀም የምንፈልገው ነገር የለም። ለምሳሌ በኮረም የተወሰነ የፌደራል ሐይል ብቻ ነው ያለው፣ በአላማጣ የፀጥታ ክፍተት ተፈጥሮ ነበር። ለዘራፊዎች የተጋለጠበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነው የቆየው። ስለሚቻል ብቻ ዝም ብሎ መግባት የለም። ከፌደራል መንግስት ጋር ይህ ችግር እንዴት እንፈታዋለን የሚል መግባባት አለ። በዛ መሰረት ነው የምንሄደው" ሲሉ ተናግረዋል።

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በትግራይ ደቡባዊ ዞን በሚገኙ እና ከአማራ ክልል ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች በጦር መሳርያ የታገዘ ግጭት እየታየ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ትላንት ከአላማጣ ከተማ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ነዋሪዎች በበኩላቸው ግጭቶች በመስጋት ሰላማዊ ዜጎች ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ መሆኑ ገልፀውልናል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስሺ

ኂሩት መለሠ