1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኅብረተ ሰብየመካከለኛው ምሥራቅ

የረመዳን ጾም መጀመርን በማስመልከት የተላለፉ የሰላም ጥሪዎች

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2016

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ዛሬ ሰኞ የጀመረዉን የረመዳን ጾምን በማስመልከት በእስራኤል-ሀማስ መካከል ጋዛ ሰርጥ ዉስጥ የሚካሄደዉ ጦርነት ብሎም በሱዳን የሚታየዉ ግጭት እንዲቆም እና እርቅ እንዲወርድ ጥሪ አስተላለፉ። ጉቴሬዝ በሃማስ የተያዙ የእስራኤል ታጋቾች እንዲፈቱም ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4dP8H
የረመዳን ጾም መጀመር በማስመልከት የጋዛ ስደተኞች በድንኳን ሲከብሩ
የረመዳን ጾም መጀመር በማስመልከት የጋዛ ስደተኞች በድንኳን ሲከብሩ ምስል Ahmad Hasaballah/Getty Images

 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ዛሬ ሰኞ የጀመረዉን የረመዳን ጾምን በማስመልከት በእስራኤል-ሀማስ መካከል ጋዛ ሰርጥ ዉስጥ የሚካሄደዉ ጦርነት ብሎም በሱዳን የሚታየዉ ግጭት እንዲቆም እና እርቅ እንዲወርድ ጥሪ አስተላለፉ።  ጉቴሬዝ በሃማስ የተያዙ የእስራኤል ታጋቾች እንዲፈቱም ጠይቀዋል። የተመድ ዋና ፀሐፊ ለጋዛ ነዋሪዎች የነፍስ አድን እርዳታ በሚፈለገው ፍጥነት እንዲደርስ ሁሉንም መሰናክሎች ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በጋዛ አንድ አራተኛ የሚሆነዉ ህዝብ ከፍተኛ ረሃብ ማለትም ጠኔ በሚባል ደረጃ ስጋት ዉስጥ ገብቷል ሲሉም አሳስበዋል። የረመዳን ጾም የጀመረዉ በጋዛ ሰርጥ ከፍተኛ የምግብ ችግር እና ከፍተኛ ረሃብ ባንዣበበት በአሁኑ ወቅት ነዉ።

"የረመዳንን መንፈስ በማክበር ፤ የጦር መስርያ ድምፅን ዝም በማሰኘት፤ የህይወት አድን እርዳታን ለሚፈለገው ሁሉ በተፈለገዉ ፍጥነት እና በተፈለገዉ መጠን እንዲደርስ ሁሉም መሰናክሎች መወገድ አለባቸዉ ስል ጠንካራ ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።  "

ጉተረስ ዛሬ የረመዳን ጾም ቢጀምርም  በጋዛ ሰርጥ ግድያው፣ የቦምብ ናዳዉ  እና ደም መፋሰስ መቀጠሉን ተናግረዋል።  በእስራኤል ላይ የሃማስ የሽብር ጥቃት ከተፈፀመ እና እስራኤል የአፀፌታ አስከፊ ጥቃት በጋዛ ላይ ከተጀመረ በቅርቡ ስድስተኛው ወር መግባቱንም የተመድ ዋና ፀሐፊ አቶንዮ ጉተረሽ ተናግረዋል።  

በሌላ በኩል ዛሬ የጀመረዉን የረመዳን ጾም ምክንያት በማድረግ የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ህብረተሰቡ  በአንድነት እና በትብብር እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ። መራሄ መንግስት ትናንት ምሽት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልክት ጀርመን ለዓለም ሃገራት ክፍት የሆነች እና ሌሎችን አስተናጋጅ ዲሞክራሲ የሰፈነባት ሃገር መሆንዋን ገልፀዋል። በጋዛ ሰርጥ ከሚካሄደው ጦርነት አንጻር፣ ሾልዝ ረዘም ላለ ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ለተቸገሩ ሰዎች የምግብ እና አስፈላጊ ነገሮች እርዳታ ለነዋሪዉ ህዝብ እንዲቀርብ ሲሉ ጥሪም አስተላልፈዋል።  በረመዳን ወቅት በጦርነት እና ጥቃት ዉስጥ ያሉ ሰዎችን የምናስብበት ጊዜም ነው ሲል ሾልዝ አክለዋል። በጀርመን የሚኖሩ ብዙ ሙስሊሞች በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ባለበት አካባቢ ጓደኞች አልያም ቤተዘመዶች እንዳልዋቸዉ መራሄ መንግሥቱ ጠቁመዋል።

 

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር