1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት 30ኛ ዓመት

ሰኞ፣ መጋቢት 23 2016

ኢትዮጵያም ኤርትራን ከሰሜን ከአናቷ ላይ ቆርጣ ለቀድሞዎቹ ነፃ አዉጪዎች አስረክባለች። ፣ለ17 ዓመታት ጠፍንጎ የያዛትን ወታደራዊ-ሶሻሊስታዊ ሥርዓት ሰባብራ ከጣለች 3ኛ ዐመቷን ይዛለች።በ3 ዓመቱ ዉስጥ የብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና አብዮታዊ ዴሞራሲ እያለ ግራ ቀኝ ከሚረግጥ ሥርዓት ጋር ፍቅር ወድቃ------

https://p.dw.com/p/4eJvY
ጥፍጨፋዉ በሚፈፀምበት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ኃያሉ ዓለም ዝምታን መርጦ ነበር
የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊከን በሩዋንዳዉ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የተገደሉ ሰዎችን ፎቶ ሲመለከቱምስል Andrew Harnik/AFP/Getty Images

ማሕደረ ዜና፣ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት 30ኛ ዓመት

                   

ሩዋንዶች «የማይበገረዉ» በሚል ቅፅል ስም ይጠሯቸዋል።እንደ ወታደር ደፋር የጦር ጄኔራል፣ እንደ ሐገር መሪ ብሔረተኛ፣ ፖለቲከኛም ነበሩ።ሩዋንዳን፣ በመፈንቅለ መንግስትም፣ በምርጫም ብለዉ  ከ1973 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) መርተዋል።ዩቬናል ሐብያሪማና። የዚያን ቀን ግን ተጃጃሉ ወይም በጣም ደፈሩ።ወደ ዳሬ ኤ ሰላም-ታንዛኒያ እንዳይሄዱ የዛኢሩ መሪ ሞቦቱ ሴሴሴኮ አስጠንቅቀዋቸዉ ነበር።ሔዱ።ሚያዚያ 6፣ 1994።ከዉሎ ጉባኤ በኋላ ማታዉኑ የብሩንዲ አቻቸዉንና  ሌሎች 7 ባለስጣኖቻቸዉን ይዘዉ በልዩ ጄታቸዉ ወደ ኪጋሊ በረሩ።ከምሽቱ 2:20።ጄታቸዉ ኪጋሊ አዉሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ስትሽከረከር ከምድር ወደ አየር በተተኮሰ ሚሳዬል ክንፏ ተመታ።ቀጥሎ ጭራዋ።ጋየች።ዘጠኝ መንገደኞችና ሶስት የአዉሮፕላኑ ሰራተኞች ነደዱ።በማግስቱ ሩዋንዳ ለዘር፟ ዛሯ ግብር ዜጎችዋን ታሳጭድ ገባች።የፊታችን ዕሁድ 30 ዓመቱ። 

             ዓለም በለዉጥ ሒደት

ሶቭየት ሕብረት ተፈረካክሳለች።ለዘመናት የፀናዉ፣የተዘመረ፣የተሰበከለት «ዓለም የወዛደሮች ትሆናለች» ትኮሚንስታዊ ትንቢት ምሥራቅ አዉሮጳ ላይ ለነበር ዝክር ተቀብሮ ዓለም የካፒታሊስቶች ሆናለች «ቀዝቃዛ» የሚባለዉ ጦርነትም በካፒታሊስቱ ጎራ የበላይነት አብቅቷል።
ኢትዮጵያም ኤርትራን ከሰሜን ከአናቷ ላይ ቆርጣ ለቀድሞዎቹ ነፃ አዉጪዎች አስረክባለች። ፣ለ17 ዓመታት ጠፍንጎ የያዛትን ወታደራዊ-ሶሻሊስታዊ ሥርዓት ሰባብራ ከጣለች 3ኛ ዐመቷን ይዛለች።በ3 ዓመቱ ዉስጥ  የብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና አብዮታዊ ዴሞራሲ እያለ ግራ ቀኝ ከሚረግጥ ሥርዓት ጋር ፍቅር ወድቃ ምናልባት ለወደፊት የጎሳ እልቂቷ መሠረት ለመጣል ዓለምን ረስታ አለሟን ትቀጫለች።

በቱትሲዎችና በለዘብተኛ ሁቲዎች ላይ ባነጣጠረዉ ጭፍጨፋ የተገደሉ ሰዎች አልባሳትና ቁሳቁስ
በቱትሲዎችና በለዘብተኛ ሁቲዎች ላይ ባነጣጠረዉ ጭፍጨፋ የተገደሉ ሰዎች አልባሳትና ቁሳቁስምስል Ben Curtis/AP/picture alliance

እንደ ኮሚንስታዊዉ ሥርዓት ሁሉ ከ1948 ጀምሮ ደቡብ አፍሪቃን  በጠንካራ ጥርስ ጥፍሩ ፈጥርቆ የያዘዉ የዘር መድሎ ሥርዓት ተገርስሶ፣ያቺ የአፍሪቃ ሐብታም፣ኃያል ግን የጥቁር ዜጎችዋ የሲዓል ምድር ላዲድ ምርጫ እየተጣደፈች ነዉ።እርግጥ ነዉ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ላይ የሚንተከተከዉን የዘር እልቂት እሳተ ጎሞራን  ካምፓላዎች ሲቆሰቁሱ እና ኪንሻሳዎች በተቃራኒ አቅጣጫ ሲቆሰቁሱት ዳሬሰላምና ሌሎች እያቀዘቀዙ ጊዜ «ለመግዛት» መሞከራቸዉ አልቀረም።

ከ1990 ጀምሮ ዩጋንዳ ዉስጥ የሸመቀዉ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (RPF) ኒ,ተባለዉ አማፂ ቡድንና የሩዋንዳን ማዕከላዊ መንግስትን አሩሻ-ታንዛኒያ ዉስጥ የተፈራረሙት የተኩስ አቁም ዉል በየጊዜዉ እየፈረሰ፣ከመጠገን፣ እየተጠገነ ከመፍረስ ሌላ ሁነኛ ዉጤት ያላመጣዉም ለዚሕ ነዉ። 

የተቀሩት ብዙዎቹ የአፍሪቃ  መንግስታት፣ የአፍሪቃ ጉዳይ ተንታኖችና ኮፊ አናንን የመሰሉ የአፍሪቃ ትላልቅ ዲፕሎማቶችም የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ከአንጎላ እስከ አልጄሪያ፣ ከደቡብ አፍሪቃ እስከ ሶማሊያ ያስከተለዉን በጎ መጥፎ ተፅዕኖ ከማሰላሰል ሌላሩዋንዳ ላይ የሆነዉ ይሆናል ብለዉ የገመቱ አይመስልም።

የያኔዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን እንደሚሉት የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ፍላጎት ላይ «ፍንዳታ» ያሉት ዓይነት ተፅኖ ነዉ ያሳደረዉ።

«የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ዘመቻ ላይ ተደራራቢ ሥራ ነዉ ያስከተለዉ።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በተደጋጋሚ ዉሳኔዎችን ያሳልፋል።በዉሳኔዉ መሠረት በጣም አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ሁሉ ኃላፊነት ይሰጠናል።ነገር ግን ለዘመቻዉ የሚያስፈልገዉ ሐብት ግን ሁል ጊዜ አይመደብም።»

ምዕራባዉያን መንግስታት ስለ ዘር ማጥፋቱ 

ዩናይትድ ስቴትስ 1993 ላይ መሪ ቀይራለች። በ1992 ሶማሊያ ላይ ከገጠማት ሐፍረት ግን ገና አላገገመችም።ኋላ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አናሳዎቹ ቱትሲዎች የሚበዙበት የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ሰሜናዊ ሩዋንዳን መቆጣጠሩ በ1959 የተቀጣጠለዉን ዓይነት የሁቲዎች አመፅ አስከትሎ ሕዝብ ሊያጫርስ ይችላል የሚል ትንታኔና አስታየት በየመገናኛ ዘዴዉ ሲሰራጭ ነበር።
በተለይ የዩናይትድ ስቴትሱ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት (CIA) ሚያዚያ መግቢያ 1994 ላይ ለፕሬዝደንት ቢል ክልተን ባቀረበዉ ዘገባ እልቂት ሊደርስ እንደሚችል ጠቁሞ ነበር።ከጥቆማ አላለፈም።
ብሪታንያዎችን ጨምሮ  አብዛኞቹ የአዉሮጳ ሕብረት መንግስታትየሩዋንዳን ጉዳይ ሲርቅ ለጀርመን፣ ቀርብ ሲል ለቤልጂግና ለፈረንሳዮች ትተዉ ምሥራቅ አዉሮጳ ላይ በኮሚንስቶች እግር የተተካና የሚተካዉን አዲስ ሥርዓት እንዴትነት እየተከታተሉ ነዉ።ዳግም የመዋሐዳቸዉ ፌስታ-ደስታ ገለል ቀለል ሲልላቸዉ የወደፊቱን ጉዞ በማሰላሰል የተጠመዱት ጀርመኖች ስለ ድሮዋዋ ቅኝ ተገዢያቸዉ የሚያስቡበት ጊዜ አልነበራቸዉም።ሌለዋ የሩዋንዳ የቀድሞ ቅኝ ገዢ ቤልጅግ ግን ሰላም አስከባሪ ሰራዊት አስፍራለች።ፍራንሷ ሜትሯ የሚመሩት የፈረንሳይ መንግስት ባለሥልጣናት የወሰዱት ርምጃ የኋላዉን የዘር ማጥፋት ዘመቻ አቀጣጥለዋል ይባላሉ።ይሁንና ፕሬዝደንት ዩቪናል ሐብያሪማና ከተገደሉ በኋላ የተመሠረተዉ የሩዋንዳ ሞጊዝት መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር ዤን ካምባንዳ ኋላ እንዳሉት ሐብያሪማና ወደ ዳሬ ኤ ሰላም እንዳይጓዙ የዛኢሩ ፕሬዝደንት ሞቡቲ ሴሴሴ ያሳሰቧቸዉ ከፈረንሳይ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣን ያገኙትን መረጃ ጠቅሰዉ ነበር።
የሐብያሪማና አዉሮፕላን አብራሪና ሠራተኞችም ፈረንሳዉያን ነበሩ።አዉሮፕላንዋ ከነተሳፈሪዎችዋ  በጋየች ማግስት የፕሬዝደንት ፍራንሷ ሜትሯ የፀጥታ አማካሪ ፍራንሷ ደ ግሮሶቭሬ እራሳቸዉን አጥፍተዋል።ሚዚያ 7፣ 1994።ግንኙነቱ ምን ይሆን? አዉሮፕላኑን መትቶ የጣለዉስ ማን ነዉ? 

የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ዩቪናል ሐብያሪማና ከመገደላቸዉ ከጥቂት ዓመታት በፊት
በአዉሮፕላን በመብረር ላይ እንዳሉ አዉሮፕላኑ በሚሳዬል ሲመታ የተገደሉት የቀድሞዉ የሩዋንዳ ፕሬዝደንትምስል picture-alliance/dpa

ትሲዎች አማፂ ቡድን (RPF) አክራሪ ሁቱዎች ወይስ ሌላ? ሲጠየቅ-ሲመለስ እንደ ገና ሲጠየቅ 30 ዓመት ሊደፍን ዕለታት ቀሩት።የሩዋንዳ ቱትሲዎችና ቱትሲዎችን ከጥቃት ለመከላከል የሞከሩ የሁቲ ጎሳ አባላት ግን ከዚያን ቀን ጀምሮ በጥይት፣ በገጀራ፣ በዱላ ጭምር ይጨፈጨፉ ገቡ።
«እግሬን በጥይት መቱኝ።ቤቱን መዘበሩት።የሞትኩ መስሏቸዉ ሔዱ።»
እና ዳነ።ትረፍ ያላት ነብስ።የሁቲ ፖሊሶች፣ ተራ ታጣቂዎች፣ ኢንተራሐምዌ (ባንድነት የሚዋጋ እንደማለት ነዉ) ታጣቂ ኃይላት ቱትሲና ለዘብተኛ ሁቲዎችን እያሳደዱ፣ ከየቤቱ እያስወጣ ወይም በየቤቱ እየገቡ ገደሉት።ሴት ልጅን ባሏ ወይም አባቷ ፊት ደፈሩ፣ ባልን እሚስቱ፣ አባትን እልጁ ፊት ገደሉ።ከዘር ማጥፋት ዘመቻዉ በኋላ የሩዋንዳን የመሪነት ሥልጣን በተዘዋዋሪና በቀጥታ የተቆጣጠሩት  ፖል ካጋሚ ጥሩ ሕዝብ ለመሆን የዘር ማጥፋት ዘመቻ አያስፈልግንም ነበር ይላሉ።
«የተሻለ ሕዝብ ለመሆን የዘር ማጥፋት ሊደርስብን አይገባም ነበር።ባጭሩ መሆን አልነበረበትም።አፍሪቃም ይሁን ሌላ ቦታ ያለ ማንኛዉም ሐገር እጠቅሳለሁ «ዳግማዊት ሩዋንዳ መሆን የለበትም።»

 

                            ጭፍጨፋዉ  

ካጋሚ ራሳቸዉ እንደጠንካራ አማፂ ቡድን መሪ በመሪዎቹ ግድያ ይሁን በአጠቃላይ በዘር ማጥፋቱ ጭፍጨፋ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የነበራቸዉ ሚና በግልፅ አይታወቅም።

ከፕሬዝደንት ዩቬናል ሐብያሪማና ጋር የነበሩት ሹማምታት ማንነት ሲታይ ግን ለአንድ አማፂ ቡድን ኢላማ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸዉ።ከሁለቱ ፕሬዝደንቶች በተጨማሪ ሁለት የብሩንዲ ሚንስትሮች፣ የሩዋንዳ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም፣የሩዋንዳ ፕሬዝደንት የወታደራዊ ዘመቻ አማካሪ፣የፕሬዝደንቱ የወታደራዊ ጉዳይ ምክር ቤት ኃላፊ፣ የፕሬዝደንቱ የዉጪ ግንኙነት አማካሪ ይገኙበታል።
ሚዚያ ,መጀመሪያ ላይ የዚያች ትንሽ፣ ለም፣ ደሐ ሐገር ሕዝብ እያለቀ መሆኑን የያኔዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአዉሮጳና የአሜሪካ ባለስልጣናትም ሰምተዉ ነበር።መልሳቸዉ ግን የያኔዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ዘመቻ ምክትል ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን እንደሚሉት አሳፋሪ ነዉ።
                         
«አዉሮፕላኑ ሲመታ ጥሩ የበሩ ተስፋዎች ሁሉ በነኑ። እዚያ ከነበሩት የኛ ጄኔራሎች አንዱ  ማስጠንቀቂያ ሰጠን።አንድ የሆነ ሰዉ ሊያናግረኛ ይፈልጋል ቱትሲዎችን የማጥፋት ዕቅድ እንዳለ ነገሮኛልም አለን።ጄኔራሉ  135 መሳሪዎችን መማረክ እንዳለበትም ሰዉዬዉ ነግሮታል።በዚያ ሰዓት መንግስታት ተጠማሪ ወታደሮች ለማዝመት ፈቃደኞች አልነበሩም።ጄኔራሉ የነበሩት ወታደሮች ደግሞ በጣም ትንሽ ናቸዉ።600 ቢሆኑ ነዉ።ከሰዎቹ ጋራ ግጭት ቢፈጠር መቋቋም የሚችሉበት አቅም የላቸዉም።ጄኔራሉ ጉዳዩን ለአሜሪካ፣ለፈረንሳይና ለቤልጅግ አምባሳደሮች እንዲናገር ነገርነዉ።»
ጄኔራሉ የተባሉትን አድርገዋል።ነገር ግን  ከኪጋሊ የደረሰዉን አዲስ  ማስጠንቀቂያ የኒዮርክ፣ ዋሽግተን፣ ፓሪስ፣ ብራስልስ ዲፕሎማቶች፣ የጦር አዛዦችና መሪዎች ሲያመነዥኹ ሩዋንዳ በደም አበላ ትጥለቀለቅ ያዘች።

በሩዋንዳዉ የዘር ጭፍጨፋ የሚጠረጠሩት አብዛኞቹ ሚሊሺያ ባልደረቦች ወደ ኮንጎ ሸሽተዋል
የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ አድርሰዋል ተብለዉ የጠረጠሩ የሁቲ አክራሪ ሚሊሻ አባላትምስል picture-alliance/dpa

የቤልጂጎች ሽሽት የአሜሪካኖች ርዳታ

 

በዚሕ መሐል ከ1916 እስከ 1962 ሩዋንዳን ቅኝ የገዛችዉ ቤልጂግ 10 ወታደሮች ተገደሉብኝ በሚል ሰበብ በደም የምትዋኘዉን ሐገር ህዝብ ለገዳዮች ጥላ ወታደሮችዋን አስወጣች።
«ሁከቱ ሲቀጣጠልና ሲስፋፋ 10 የቤልጂግ ወታደሮች ተገደሉ።እና የቤልጂግ ሠላም አስከባሪ ጓድ ወጣ።የሼሪላንካዎች ብቻቸዉን ራሳቸዉን እንዲከላከሉ ታዘዙ።ሌሎቹ ግምሽ ሻለቃ ወይም 250 ወታደሮች የሚሆኑ የጋና ወታደሮች ናቸዉ።ባንፃራዊነት ሲታይ ባጭር ጊዜ ዉስጥ 800 ሺሕ ሕዝብ ተገደለ።»
ይላሉ አናን። 
የዘር ትልቅ ትንሽነት ሲሰበክ፣ ሲነገረዉ፣ በራዲዮ ሲለፈፍ፣ ሲተነተንለት የሚሰማዉ የሁቲ ወጣት፣ሐብት ንብረት ለመዝረፍ ካሰፈሰፈዉ ቦዘኔ ጋር አብሮ ባጭር ጊዜ ዉስጥ የትንሺቱን ሐገር ለም ሜዳ፣ ተራራ ወደ አስከሬን መከመሪያነት ለወጠዉ።በመቶ ቀናት ዉስጥ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ መሰረት ከ800 ሺሕ በላይ፣ አንዳዶች አንደሚሉት ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ አለቀ።ሕፃናት ያላ አሳዳጊ፣ አዛዉንቶች ያለ ጧሪ፣ ሕሙማን ያለ አሳካሚ ቀሩ።ሚሊዮኖች እግራቸዉ እንዳመራቸዉ ወደ አጎራባች ሐገራት ተሰደዱ።ያኔ ዓለም ተነቃነቀ።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ቢል ክሊተን ዋናዉ ነበሩ።

የሩዋንዳዉ የዘር ጭፍጨፋ በመሸሽ ሚሊዮኖች ተሰድደዋል
ከሩዋንዳዉ የዘር ጭፍጨፋ ያመለጠዉ ስደተኛ ወደ አጎራባች ሐገራት ሲገባምስል afp/picture-alliance

«በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ያለዉን ለመከታተል የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኬሪ በዚሕ ሳምንት አካባቢዉን እንዲጎበኝና ዘገባ እንዲያቀርብልኝ ጠይቄዋለሁ።ዛኢር የሚገኙት አዉሮፕላን ማረፊያዎች በጣም ትናንሽ በመሆናቸዉ መራገፍ ያልተቻለዉ ርዳታ እንዲራገፍ ኪጋሊ ዉስጥ አዲስ የአዉሮፕላን ማረፊያ መክፈት ያስፈልግ እንደሆነ እየመከርንበት ነዉ።አንድ ነገር ላይ ግልፅ ልሁን።ሩዋንዳ የሚዘምቱት ያአሜሪካ ወታደሮች በሙሉ ላጭር ጊዜ ሰብአዊ አገልግሎት እንጂ ሠላም ለማስከበር አይደለም።»

ፖል ካጋሚ የሚመሩት የሩዋዳ አርበኞች ግንባር ኪጋሊን  ከተቆጣጠረ በኋላ የዘር ማጥፋቱ ዘመቻ ቆሟል።በጭፍጨፋዉ ዘመድ ወዳጅ፣ ወላጅ ያለቀበትም፣ አካሉ የጎደለበት፣ የተደፈረችዉ ሴት ዛሬም ከሰቀቀን መጥፎ ቅዠት ጋር ይኖራሉ።የዓለም ኃያላንም ካጋሚ እንዳሉት «ኔቨር አጌን« እያሉ የቦስኒያን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ፣ የኮንጎን፣ የአፍቃኒስታን፣ የሱዳንን የሶሪያን፣ የዩክሬንን፣ የጋዛን እልቂትን ያጅባል፣ ይቆጥራል ወይም ያስቆጥራል። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ