1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ለልጆች አደገኛ የሆኑ መተግበሪያዎች የትኞቹ ናቸው?

ረቡዕ፣ የካቲት 13 2016

ከተንቀሳቃሽ ስልክ እና ከበይነመረብ ግንኙነት ጋር ተዳምሮ ያለንበት የዲጅታል ዘመን ለልጆች አደገኛ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልፃሉ።ስለሆነም ወላጆች በልጆቻቸው የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ አጠቃቀም ላይ ክትትል እንዲያደርጉ ይመክራል። ለመሆኑ መተግበሪያዎች ለልጆች አደገኛ የሚባሉት ምንምን ባህሪያት ሲኖሯቸው ነው?

https://p.dw.com/p/4ccBv
Symbolbild Instagram Meta Bezahlmodell
ምስል Jaap Arriens/NurPhoto/IMAGO

በይነመረብ እና መረጃ ማጋራትን የሚፈቅዱ መተግበሪያዎች ለልጆች አደገኞች ናቸው


ያለንበት የዲጅታል እና  በይነመረብ ዘመን  መረጃ ለማግኘት፣ ለመማር ፣ ለመዝናናት፣ ለተግባቦት እንዲሁም  ለሌሎች በርካታ እድሎች በር የሚከፍት ነው። ያም ሆኖ  ከአጠቃቀም ጋር ተያይዘው  የሚመጡ በርካታ ችግሮችም አሉት። ከዚህ አንፃር በበይነመረብ እና በዲጅታል ዓለም በተለይ የልጆችን ደህንነት መጠበቅ በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል። ምክንያቱም  መተግበሪያዎች በአብዛኛው በአዋቂዎች  ይዘት የተሞሉ ሲሆኑ፤ሌሎች ደግሞ የልጆችን ንፁህ አእምሮ ለማጥቃት የሚጠብቁ አጥማጆች ያሏቸው ናቸው።
የሳይበር ምህዳሩም ቢሆን፤  የበይነመረብ ግንኙነት እስካለ ድረስ  ያለ ገደብ  መለጠጥ የሚችል በመሆኑ  ግላዊነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ይህ ሁኔታ ከተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት እና ከበይነመረብ ግንኙነት ጋር ተዳምሮ  ለልጆች አደገኛ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

ይህንን አደጋ ለመቀነስም ወላጆች  በልጆቻቸው የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ አጠቃቀም ላይ ክትትል እንዲያደርጉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ያን ሊያደርጉ የሚችሉት ግን  ወላጆች የመተግበሪያውን አደገኛነት  ለመለየት የሚያስችል በቂ እውቀት ካላቸው ብቻ ነው። ለመሆኑ መተግበሪያዎች ለልጆች አደገኛ የሚባሉት ምንምን ባህሪያት ሲኖሯቸው ነው? የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ብሩክ ወርቁ  ዋና ዋና የሚሏቸውን ባህሪያት እንደሚከተለው ዘርዝረዋል። «አንድ አፕሊኬሽን ለልጆች አደገኛ ነው የሚያስብሉት ዋና ዋና ነገሮች ምንድናቸው ከተባለ የመጀመሪያው የኢንተርኔት «ኮኔክሽን» የሚፈልግ ከሆነ እና ልጆች ወደ ሳይበር «ዶሜን» ወይም ወደ ሳይበር ዓለም በቀላሉ የሚወጡ መሆኑ አደገኛ ያስብለዋል።ሁለተኛ «አኖኒመስ» ከሆነ ወይም ማንነቱ ከማይታወቅ ሰው ጋር «ኮምኒኬት» እንዲያደርጉ የሚፈቅድ «ፕላትፎርም» ሲሆን፤ሌላው አደገኛ ባህሪ ነው።»በማለት ገልፀዋል።

አቶ ብሩክ ወርቁ የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ
አቶ ብሩክ ወርቁ የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ ምስል Privat

በእነዚህ መሰሎቹ መተግበሪያዎች ምንም እንኳ ልጆች ማንነታቸውን ሳያሳውቁ  በበይነመረብ መስተጋብር ለመፍጠር የሚያገለግሉ ቢሆንም፤ በሌላኛው ወገን ከልጆቹ ጋር መስተጋብር የሚፈጥረው ሰውም ማንነቱ ስለማይታወቅ ከማን ጋር እንደሚገናኙ ለማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ለልጆች አደገኛ  ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ተጠቃሚዎች ይዘትን ለሌላ  ወገን እንዲያጋሩ መፍቀድም አቶ ብሩክ እንደሚሉት  ሌላው የአደገኛ የመተግበሪያዎች ባህሪ ነው። «ሌላው በኢንተርኔት ዓለም «ፕራቬሲ »የሚባል ነገር የለም። አንዴ «ሼር» የተደረገ «ኮንቴንት» የጠፋ ቢመስልም «ዴሊት» ብናደርገውም ተመልሶ አይገኝም ተብሎ በ«አፕሊኬሽን» አበልጻጊዎች ቃል ቢገባም  አንዴ «ሼር» የተደረገ «ኮንቴንት ዌብ» ላይ ያለን ነገር  መልሶ ማግኛ መንገዶች አሉ።ያንን «ለማሉሸስ አክቲቪቲ»ወይም ለመጥፎ ነገር የሚያውሉ ስላሉ፤ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ለማጋራት የሚፈቅዱ ለምሳሌ የግል መረጃዎችን እንደነውር የሚቆጠሩ  ነገሮችን የሚያጋሩ ከሆነ አደገኛ ይሆናሉ።ሌላው ሶሻል ሚዲያ ነው።ሶሻል ሚዲያ ብዙ ዓላማ አለው። ለጤነኛ ዓላማ ልንጠቀመው እንችላለን። ነገር ግን  ለሳይበር ትንኮሳ የማጋለጥ አቅም ያለው ነው።» በማለት ገልፀዋል።

ከእነዚህ ከተጠቀሱት ባህሪያት በመነሳትም አደገኛ መተግበሪያዎችን በሶስት ዋናዋና ምድቦች ከፍሎ ማየት እንደሚቻል ባለሙያው ያስረዳሉ።እነሱም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች፣ የተለያዩ ይዘቶችን በቪዲዮ የሚያጋሩ ዲጅታል መድረኮች እንዲሁም በበይነመረብ አማካኝነት ከሰዎች ጋር ቨርቹዋል መስተጋብር ለመፍጠር የሚያገለግሉ  ዲጅታል መድረኮች ናቸው።
ከዚህ አኳያ ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ውስጥ  እንደ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ስናፕቻት እና ቲክ ቶክ ያሉ አቶ ብሩክ እንደሚገልጹት ለልጆች እጅግ አደገኛ የሚባሉ መተግበሪያዎች ናቸው።
ማንኛውም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ አጠቃቀሙን እስካላወቅን እና ልጆች በልክ እንዲጠቀሙ ካላደተደረገ  አደገኛ ሆኖ መመደብ ይችላል የሚሉት አቶ ብሩክ፤ ነገር ግን  ከላይ የተጠቀሱትን  አደገኛ የሚያደርጋቸው በልጆች ላይ ዘርፈ ብዙ ጥቃት እንዲፈጸም መፍቀዳቸው ነው።ይላሉ።ለዚህም «ሪልስ» የሚባሉትን  አጫጭር  ቪዲዎችን ለአብነት ይጠቅሳሉ።
«የመጀመሪያው ምንድነው ልጆች በአሁኑ ጊዜ ሪልስ የምንላቸውን ወይም ደግሞ  አጫጭር  ቪዲዎችን ርዝመታቸው ከ30 ሰከንድ ያልበለጡ ይዘቶችን እንዲያዩ የሚያመቻቹ ናቸው። ይህን ማድረጋቸው ክፋቱ ምንድነው የልጆችን በመጀመሪያ ደረጃ በቀላሉ ያላቸውን «አቴንሽን ስፓን» ወይም ያላቸውን  «ፎከስ» የሚያሳጡ ናቸው።ለምሳሌ ድሮ ልጆች ፊልም በማየት ይዝናኑ ነበር።መፅሀፍ በማንበብ ረዘም ባለ ይዘት እውቀት በመገብየት ጊዚያቸውን ያጠፋሉ።» ካሉ በኋላ በእነዚህ አጫጭር ቪዲዮዎች የሚዝናኑ ከሆነ ግን ረዘም ያለ ይዘት ለማየት  ትኩረት እንደሚያጡ ገልፀዋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት እንደ ፌስቡክ ፣ቲክቶክ እንስታግራም ያሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ መተግበሪያዎች ለልጆች አደገኞች ናቸው
ባለሙያዎች እንደሚሉት እንደ ፌስቡክ ፣ቲክቶክ እንስታግራም ያሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ መተግበሪያዎች ለልጆች አደገኞች ናቸውምስል Jonathan Raa/NurPhoto/picture alliance

በሌላ በኩል ልጆች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማንነታቸው ከማይታወቁ ሰዎች ጋር  ጥብቅ  ቁርኝት በመፍጠር  ግላዊ መረጃዎችን አሳልፈው ሊሰጡ እና ለጥቃት ሊጋለጡ ይችላሉ።
«ኮንቴንት ሸር ለማድረግ የተመቹ ናቸው።ቻት ያደርጋሉ ማንነታቸውን ቀይረው ሊወጡ ይችላሉ።ወይም ማንነታቸው ከተቀየሩ ሰዎች ጋር ኮምኒኬት ሊያደርጉ ይችላሉ።» ካሉ በኋላ በምሳሌ እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ።«ለምሳሌ አንድ ሰው ማንነቱን ደብቆ ወይም «ፌክ» ፕሮፋይል ፈጥሮ እንበል ፌስ ቡክ ላይ ያልሆነውን ሆኖ ወይም መስሎ ከእነሱ ጋር «ኮምንኬት» ሊያደርግ ይችላል።ለዓመታት በዚህ ሁኔታ ኮምኔኬት ካደረጉ በኃላ» በዚህ ሰው ላይ አመኔታ በመፍጠር መስጠት የማይጠበቅባቸውን መረጃ ሊሰጡ እንደሚችሉ አብራርተዋል። 
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ፎቶዎችን ለማጋራት የተመቹ በመሆናቸው ልጆችም ፎቶዎቻቸውን በነዚሁ ዲጅታል መድረኮች ያጋራሉ።ነገር ግን ልጆች በባህሪያቸው መመስገን የሚወዱ በመሆናቸው ፤በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሚያጋሯቸው ፎቶዎችም ጥሩ ግብረመልስ ማግኘትን ይጠብቃሉ። ያ ሳይሆን ቀርቶ አሉታዊ የሆኑ ምላሾችን በሚያገኙበት ወቅት  ያልጠና አእምሯቸው ይህንን መሸከም ስለማይችል ለስነ ልቡና ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ባለሙያው አስረድተዋል።ከዚህ በተጨማሪ  የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ልጆች ለመማር እና ሌሎች ውጤታማ ስራዎች የሚያውሉትን ጊዜ እና ጉልበት እንዲሁም ትኩረት እንዲያባክኑ ያደርጋሉ።

በልጆች ላይ ከሚያሳድሩት ይህንን መሰል አሉታዊ ተፅዕኖ አንፃር ፋሚሴፍ/famisafe / የተባለ ድረ ገፅ በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሰረት ፤እንደ ስናፕ ቻት ፣ብሌንደር፣ አስክ ኤፍኤም፣ ሚትሚ እንዲሁም ኪክ የተሰኙ መተግበሪያዎችም ለልጆች አደገኛ የሚባሉ ናቸው።
የተግበሪያዎቹን ባህሪያት አንድ በአንድ ስንመለከት ፤ስናፕ ቻት /Snapchat/  በልጆች እና ጎልማሶች የሚዘወተር  ታዋቂ መተግበሪያ ሲሆን፤ በዚህ መተግበሪያ ሰዎች የተለያዩ ማጣሪያዎችን/filters/ በመጠቀም የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በምስል እና በቪዲዮ ይለጥፋሉ። ይህ መተግበሪያ ልጆችን ሱስ የሚያስይዝ በመሆኑ ለልጆች አደገኛ በሚል ምድብ ተጠቅሷል። ምስሎቹ እና መልእክቶቹ በቅጽበት የሚሰረዙ በመሆናቸው ደግሞ ሰዎች መተግበሪያውን ሥነ ምግባር ለጎደላቸው ተግባራት ሊጠቀሙት ይችላሉ። ይህም የልጆችን አእምሮ ስለሚጎዳ  እንዳይጠቀሙ በባለሙያዎች ይመከራል።

ስናፕ ቻት ሰዎች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በምስል እና በቪዲዮ የሚያጋሩበት መተግበሪያ ሲሆን፤ ሥነ ምግባር ለጎደላቸው ተግባራት ሊጠቀሙት ስለሚችሉ ልጆች እንዳይጠቀሙ በባለሙያዎች ይመከራል።
ስናፕ ቻት ሰዎች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በምስል እና በቪዲዮ የሚያጋሩበት መተግበሪያ ሲሆን፤ ሥነ ምግባር ለጎደላቸው ተግባራት ሊጠቀሙት ስለሚችሉ ልጆች እንዳይጠቀሙ በባለሙያዎች ይመከራል።ምስል Jens Kalaene/dpa/picture alliance

ሌላው ለልጆች በጣም አደገኛ ከሆኑ መተግበሪያዎች ውስጥ አንዱ ብሌንደር /Blendr/ የተባለው መተግበሪያ ነው። ይህ መተግበሪያ  ተጠቃሚዎች ለማያውቋቸው ግለሰቦች መልዕክት እንዲልኩ እንዲሁም ፎቶዎችን እና ቪዲዮዎችን እንዲያጋሩ ያስችላል።ስለ ፎቶዎቹ ተወዳጅነትም ደረጃ መስጠት ይችላል። ልጅች ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ከፍ ለማድረግ ስለሚፈልጉ እንደዚህ ባሉ አደገኛ መተግበሪያዎች ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ። መተግበሪያው ከተጠቃሚው አካባቢ ወይም አቅጣጫ/location/ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን የሚጠቀም በመሆኑም ለልጆች አደገኛ ያደርገዋል።
አቶ ብሩክ  እነዚህን መተግበሪያዎች ልጆችን  የሚጠመዝዙ  አደገኛ መተግበሪያዎች ይሏቸዋል።
«ብሌንደር ፣ ግራይንደር፣ ስናፕ ቻት የሚባሉ አፕሊኬሽኖች ልጆችን እንዲጫኗቸው ወይም እንዲጠመዝዟቸው የሚያደርጉ «ማኑፕሌተርስ» ወይም ጠምዛዦች እንበላቸው እና  ሆን ብለው ለፆታዊ ፍላጎት በልጆች ስሜት የሚጫወቱ ፣ሆን ብለው እድሚያቸው ለማይፈቅድላቸው ነገሮች የሚያመቻቹ ናቸው።እነኝህ ሰዎች ምናልባት ሩቅ ተደርገው በ«ዌብ» ወይም በ«ቨርቿል» ዓለም ስንመለከታቸው የራቁ ሰወዎች ሊመስሉ ይችላሉ።ነገር ግን የልጆቹን ድክመት የሚያውቁ በቅርብ ያሉ ሰዎችም እንዲህ አይነት ጥቃት ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ።»በማለት አስጠንቅቀዋል። 

ከዚህ ባሻገር አስክ ኤፍኤም /Ask.FM /የሚባለው መተግበሪያም ሌላው ለልጆች አደገኛ የሚባል መተግበሪያ ነው። መተግበሪያው ልጆች ስማቸውን ሳይጠቅሱ ጥያቄዎቻቸውን በመለጠፍ መጠየቅ የሚያስችል ሲሆን፤ይህንን ጥያቄ ደግሞ ማንነታቸውን ሳይገልጹ ሌሎች እንዲመልሱ የሚያደርግ ነው። ነገር ግን ግልጽ ይዘት ስላለው ወላጆች ልጆቻቸው እንደዚህ ያሉ አደገኛ መተግበሪያዎችን  እንዳይጠቀሙ መጠቆም እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ።ምክንያቱም እንደዚህ ያሉ ጥያቄዎች  ለወጣቶች እና ለታዳጊዎች ተገቢ ያልሆነ ይዘት ሊኖራቸው ይችላል እና ።
ሚት ሚ /MeetMe/ የተሰኘው መተግበሪያም እንደሌሎች የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ መተግበሪያዎች ተጠቃሚዎች መልዕክት እንዲላላኩ እና  ከሰዎችን በግል እንዲያገኟቸው የሚረዳ ነው ሲሆን፤በአቅራቢያ ያሉ ተጠቃሚዎችን እንዲገናኙ ለመርዳት አቅጣጫ መጠቆሚያ «ጂፒኤስ»ን ይጠቀማል። ከዚህ አንፃር መተግበሪያው የበይነመረብ አጥማጆች በቀላሉ ሊገኙት እና ልጆችን ሊከታተሉ ስለሚችሉ  አደገኛ ነው።በተጨማሪም መተግበሪያው የልጆችን የግል መረጃ ደህንነት በሚመለከት ምንም አይነት የደህንነት ማስጠበቂያ መንገድ የለውም። 

በይነመረብ ግንኙነት የሚፈልጉ እና መረጃ ማጋራት የሚፈቅዱ መተግበሪያዎች ለልጆች አደገኞች ናቸው
በይነመረብ ግንኙነት የሚፈልጉ እና መረጃ ማጋራት የሚፈቅዱ መተግበሪያዎች ለልጆች አደገኞች ናቸውምስል Post Staff/Zuma/IMAGO


ኪክ/Kik/ መተግበሪያም በአሁኑ ጊዜ  በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝ ፤ነገር ግን ለልጆች አደገኛ ከሆኑ መተግበሪያዎች አንዱ ነው። መተግበሪያው መልዕክት ለመላክ እና ለመቀበል የሚያስችል መድረክ ሲሆን፤ ከተጠቃሚዎች ጋር የተያያዙ  መረጃዎችን ማንኛውም ሰው በቀላሉ አላግባብ ሊጠቀምበት የሚችል በመሆኑ፤ ከግላዊነት  አንፃር በጣም አደገኛ መተግበሪያ ነው። ልጆችም ከማንኛውም እንግዳ ሰው ጽሑፎችን ሊቀበሉ ይችላሉ፣ ይህም ለልጆች የሥነ-ልቡና ጤንነት ጎጂ ሊሆን ይችላል። 

ከፅሁፍ መልክት ባሻገር በቪዲዮ መልዕት መለዋወጥን የሚፈቅዱ መተግበሪያዎችም ለልጆች አይመከርም።ከእነዚህም መካከል ቫይን አፕ/Vine App/የሚባለው መተግበሪያ አንዱ ነው።. ይህ መተግበሪያ ቪዲዮ ለማጋራት የሚያገለግል  መተግበሪያ ነው።ምንም እንኳ መተግበሪያው አነቃቂ ወይም አስቂኝ ቪዲዮዎችን ለማጋራት ታስቦ የተሰራ ቢሆንም፤ ስለሚጋራው ይዘት ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል  መተግበሪያው ለልጆች አደገኛ ከሆኑት  ውስጥ አንዱ ነው።

በሌላ በኩል  የቀጥታ ውይይት ለማድረግ  የሚረዱ አንዳንድ መተግበሪያዎችም ብርቱ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ናቸው። ለምሳሌ ሃውስፓርቲ/ Houseparty/ የሚባለው መተግበሪያ  እስከ 10 ሰዎች ድረስ በቪዲዮ ውይይት ለማድረግ  የሚያስችል መተግበሪያ ነው። መተግበሪያው ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው በ2016 ዓ/ም ሲሆን፤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ይበልጥ  ታዋቂነትን አገኝቷል። ምንም እንኳን ለአጠቃቀም  ቀላል እና ብዙ ሰዎችን ለውይይት የሚጋብዝ ቢሆንም  ለልጆች ግን አደገኛ መተግበሪያ ተብሎ ሊጠራ ይችላል።ምክንያቱም  ይህ መተግበሪያ የስልክ፣ የፌስቡክ እና  የስናፕቻት አድራሻ እንዲሁም ጎደኞች ዝርዝር ሊመዘግብ ይችላል።ከላይ በተጠቀሱት ዝርዝሮች ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ከልጆች ጋር ያለ ቅድመ ማሳወቂያ  ውይይት ሊጀምር ይችላል። ይህም ልጆችን በቀላሉ ላልተገባ ይዘት ሊጋልጥ ይችላል።

ስለሆነም ከነዚህ አደገኛ መተግበሪያዎች ልጆችን ለመታደግ፤ ወላጆች ከልጆች ጋር ግልፅ ውይይት ማድረግ እና  የልጆችን የበይነመረብ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችል ዕውቀት ለማግኘት ራስን ማስተማር እንደሚያስፈልግ ባለሙያው አስረድተዋል።
 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተችነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ