በሠዓት 320 ኪሎ ሜትሮች ይምዘገዘግ፣ ይሽከረከረር የነበረ ፈጣን አውሎ ነፋስ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የኦክላሆማ ከተማ አጎራባቾችን ትናንት በከፋ ሁናቴ መምታቱ ተዘገበ። በእዚህ አደገኛ የአውሎ ንፋስ ነውጥ ከእሁድ አንስቶ እስካሁን የሞቱት ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 91 መድረሱ ሲዘገብ፤ በርካቶቹ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የነበሩ ህፃናት መሆናቸውም ታውቋል። አደገኛው አውሎ ነፋስ፣ በ1 ነጥብ 5 ኪሎሜትሮች ስፋት ውስጥ የነበሩ ቤቶችን፣ሕንፃዎችን፣ መኪናዎችንና በአጠቃላይ ከፊት ለፊቱ ያገኛቸውን ቋሚ ነገሮች በመላ እንዳልነበረ አድርጎ ነው ያለፈው። በእንዲህ አይነቱ አደገኛ አውሎ ነፋስ ይህን ያህል ሰው ሲያልቅና ከፍተኛ ጥፋት ሲከሰት ከረዥም ዓመታት ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል። በዋሽንግተን የዶቸቬለ ዘጋቢ ማክስ ሆፍማን የአደጋ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶም ቢሆን፤ እንዲህ ከፍተኛ ጥፋት ሊከሰት የቻለበትን ምክንያት በእዚህ መልኩ ይገልፃል።
"እጅግ ኃይለኛው አውሎ ነፋስ፣ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠ ብዙም ሳይቆይ ነው ገስግሶ የደረሰው። ከስምንት እስከ አስራ ሁለት ደቂቃዎች ባሉት ልዩነቶችም ነበር ያን ሁሉ ዕልቂት አድርሶ ያለፈው። በግልፅ እንደሚታየው ሰዉ መጠለያዎችን ለማግኘት እንኳን በቂ ጊዜ አልነበረውም።"
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኦክላሆማውን የብርቱ አውሎ ነፋስ ጥፋት ከባድ አደጋ ሲሉ ገልፀውታል። የበጎ ፍቃደኞችና የርዳታ ሠራተኞች በህይወት የተረፉ ነዋሪዎችን ለማግኘት በፍርስራሾች ውስጥ ፍለጋቸውን እንደቀጠሉ ነው። እጎአ በ1999 መሰል የአውሎ ነፋስ ጥፋት ተከስቶ የነበረ ቢሆንም እንደ ትናንትናው ዓይነት ግን ምድርን በከፋ ሁናቴ የመታ አውሎ ነፋስ ታይቶ አይታወቅም።
የግብፅ ጦር ኃይል፣ ሰባት የፀጥታ ክፍል ባልደረቦች፣ በእስላማዊ ሚሊሺያዎች መጠለፋቸውን ተከትሎ ዛሬ ተጨማሪ ጦር ወደ ሲና በረሃ ማጓጓዙ ታወቀ። ጦሩ አራት የድንበር ጠባቂ ጓዶቹና ሦስት የፖሊስ መኮንኖቹ ባለፈው ሐሙስ ታፍነው የተወሰዱት ከሲና በረሃ ወደ ግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ በሚያቀናውና ኧል አሪሽ በተሰኘው አውራጃ ውስጥ በሚገኘው ጎዳና ላይ ነበር። በድርጊቱ ቁጣ ያደረበት የግብፅ ጦር ታጋች ባልደረቦቹን የግብፅ መንግስት እንዲያስለቅቅለት ጫና ለመፍጠር ይረዳል በሚል ዛሬ የድንበር መተላለፊያዎችን ለመዝጋት ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉ ታውቋል። መተላለፊያዎቹ ኧል አውጃ የተሰኘችው ድንበር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ወደ ጋዛ ሠርጥና እስራኤል የሚያሻግሩ ቦታዎች ናቸው። ጦሩ በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችና የጦር ጀቶች በመታገዝ እስራኤል ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው አል ጃሚኢ በተሰኘችው መንደር ውስጥ አጋች ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ የቤት ለቤት አሠሣ ማከናወኑም ተዘገቧል። አጋቾቹ በምርኮ በያዟቸው የግብፅ ጦር አባላት ለውጥ በእስር ላይ የሚገኙ ዘመዶቻቸው እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል። የግብፅ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሞርሲ በበኩላቸው ከአጋቾቹ ጋር እንደማይደራደሩ አስታውቀል። እስላማዊ ሚሊሺያዎች እስራኤልንና ግብፅን ለመምታት የሲና በረሃን እንደመንደርደሪያ አድርገው በመጠቀም ላይ ይገኛሉ።
የናይጀሪያ ጦር ሰሜን ምሥራቃዊ ናይጀሪያ ውስጥ የመሸገውን ቦኮ ሀራም የተሰኘው አክራሪ እሥላማዊ ድርጅት ለመምታት ፕሬዚዳንቱ ያስተላለፉት የሰዓት እላፊ አዋጅ ዛሬ በምክር ቤት ፀደቀ። የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ቦርኖ፣ ዮቤና አዳማዋ በተሰኙት ሦስት የሰሜን ምስራቅ ግዛቶች ውስጥ የሠዓት እላፊ አዋጁን ያስነገሩት ባሳለፍነው ሣምንት ማክሰኞ ነበር። የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ለንድ ሣምንት ያህል ዘግይቶ ነው በምክር ቤት የፀደቀው። የናይጀሪያ ሕገ-መንግሥት በአገሪቱ የአስቸኳይ አዋጅ ለማስነገር አጠቃላይ ብሔራዊ ጉባኤው ተሰብስቦ በሁለት ሶስተኛ የአባላቱ ድምፅ መፅደቅ እንዳለበት ይደነግጋል። የናይጄሪያ 100 የምክር ቤት አባላት ዛሬ በዝግ ችሎት አዋጁ ላይ ከተከራከሩ በኋላ የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ አፅድቀዋል። የናይጀሪያ ጦር ትናንት 120 የቦኮ ሐራም ተጠርጣሪዎችን መያዙን መግለፁ ይታወቃል። ቦኮ ሐራም በናይጀሪያ መንግሥት፣ በምዕራባውያን ባህልና የኑሮ ዘዬ ላይ ጦርነት ካወጀ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል።
የሶሪያ መንግስትን ለማገዝ ከጎረቤት ሊባኖስ የመነጩ ቁጥራቸው ወደ 20 የሚጠጉ ሺኣት ሚሊሺያ የሒዝቦላህ ተዋጊዎች አል ኩሲያር በተሰኘችው ወሳኝ የድንበር ከተማ ውስጥ በተደረገ ውጊያ ተገደሉ። ተቃዋሚዎች በቁጥጥራቸው ስር የምትገኘውን ቁልፍ ከተማ ለማስለቀቅ የሶሪያ መንግስት ጦር አዳፍኔዎችንና የጦር ጀቶችን እንደተጠቀመ ገልፀዋል። የሶርያ ጉዳይን የሚከታተለውና ለተቃዋሚዎች የሚያደላው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ተቋም በውጊያው 50 አማፂያን፣ ዘጠኝ የሶሪያ ወታደሮችና አራት ሠላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል። ከእሁድ አንስቶ በተካሄደው ውጊያ የሞቱት ሠላማዊ ዜጎች ቁጥር ከ100 እንደሚበልጥ ተጠቅሷል። የሶሪያ መንግስት የመገናኛ አውታሮች እንዳስታወቁት ከሁለት ቀናት ፍልሚያ በኋላ ጦሩ የከተማዋን በርካታ ክፍሎች ከተቃዋሚ ተፋላሚዎች ለማስለቀቅ ችሏል። የሶሪያ ጦርነት ወደ ጎረቤት ሊባኖስ እንዳይዛመት ከፍተኛ ስጋት መደቀኑም እየተነገረ ነው። የዓረቡ ሊግ ሶሪያን በተመለከተ የፊታችን ወር ሊያካሂደው ካቀደው መደበኛ ጉባኤው ቀደም ያለ አስቸኳይ ስብሰባ ከወዲሁ እንደሚጠራ አስታውቋል። ዩናይትድ ስቴትስ የሶሪያ መንግስት ጥቃትን አውግዛለች። የአውሮጳ ኅብረት በበኩሉ የሊባኖሱን የሒዝቦላ ሽምቅ ተዋጊ ቡድን በሽብርተኝነት መዝገብ ላይ ለማስፈር ይገባው እንደሆን በይፋ ማጤን ይዟል። በተለይ የሒዝቦላ ደፈጣ ተዋጊዎች ከሶሪያ መንግስት ጋር አብረው ተቃዋሚዎችን መውጋታቸውን ተከትሎ የውጭ ኃይላት በሶሪያ ውጊያ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳያደርጉም አስግቷል።
በኢራቅ መዲና በባግዳድ፣ ከትናንት አንስቶ በተከታታይ በተጣሉ የቦንብ ጥቃቶች ከ100 በላይ ሰዎች ተገደሉ። በቁጥር 150 ገደማ የሚጠጉት ደግሞ ቆስለዋል። ኢራቅ ውስጥ ካለፈው ሣምንት አንስቶ በተቀሰቀሰ ሐይማኖት ነክ ሁከት ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በትናንቱ ጥቃት ወደ 240 አሻቅቧል። የትናንቱ ዕልቂት የተከሰተው በ10 የተለያዩ መኪናዎች ውስጥ የተጠመዱ ፈንጂዎች ባግዳድ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ገላጣ ገበያዎችና አጎራባች የሺዓዎች መንደሮች ውስጥ በመንጎዳቸው ነበር። ደቡባዊ ኢራቅ ውስጥ ዋነኛ የሺዓዎች መቀመጫ በሆነችው የባዝራ ከተማም ተመሳሳይ ጥቃት ቢያንስ የ13 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። በመኪና ላይ የተጠመዱ ፈንጂዎች ሰሜን ባግዳድ ሳማራ ከተማና አንባር በተሰኘችው ምዕራባዊ አውራጃ ውስጥም መንጎዳቸው ታውቋል። ዛሬም በተመሳሳይ በተከሰቱ ተደጋጋሚ የቦንብ ጥቃቶች ቢያንስ 8 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። ዩናይትድ ስቴትስ በኢራቅ እየተባባሰ የመጣውን ሐይማኖት ነክ ሁከትና የቦንብ ጥቃቶች ኮንና ፀጥታ እንዲሰፍን ጠይቃለች።
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢንላደን ከተገደለ በኋላ ያነሳቸውን ከ50 በላይ የሚሆኑ የሟቹን ምስሎች ይፋ ሳያደርግ በምስጢር ይዞ እንዲቆይ የፌዴራሉ የይግባኝ ፍርድ ቤት ዛሬ መወሰኑን ሮይተር ዘገበ። ስማቸው ባልተገለጹት ሦስት የዋሽንግተን ዲ ሲ የይግባኝ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ውድቅ የሆነውን የቢንላደን ምስል እንዲሰጠው ጠይቆ የነበረው አትራፊ ያልሆነ አንድ ሕገወጥና ኢስነምግባር ጉዳዮችን የሚከታተል ወግ አጥባቂ ተቋም እንደሆነ ተጠቅሷል።
በቱሪስት መስህብነቱ በዓለም ዕውቅ በሆነው የፓሪሱ ኖትሬ ዳም ካቴድራል ውስጥ አንድ ግለሰብ ዛሬ ከሠዓት በኋላ ራሱን ማጥፋቱ ተዘገበ። ግለሰቡ፣ ዕድሜው፣ ከ50 እስከ 60 ዓመት እንደሚሆነው የተገመተ ሲሆን፤ ከካቴድራሉ ዐውደ-ምሕረት አጠገብ ራሱን ያጠፋው በጥይት እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል። ግለሠቡ እራሱን ከማጥፋቱ ቀደም ብሎ ዐውደ-ምሕረቱ አጠገብ ደብዳቤ ያኖረ ሲሆን፤ የደብዳቤው ይዘትና ራሱን ያጠፋበት ምክንያት ግን አልታወቀም። ድርጊቱ ተከትሎ ቤተመቅደሱ ውስጥ የነበሩ ግለሰቦች በአጠቃላይ ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸውም ተጠቅሷል።
MS/AT