1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅ ምሥቅልቅል

ሰኞ፣ ሐምሌ 1 2005

ሐይማኖተኛ በመሆናቸዉ እንዳድ የግብፅ መገናኛ ዘዴዎች በወታደራዊዉ ምክር ቤት የሙስሊም ወንድማማቾች ተወካይ በማለት እስከ መዉቀስ ደርሰዉም ነበር።ሰዉዬዉ ግን እንዲያ አልነበሩም። ብሪታንያም አሜሪካም የተማሩ በመሆናቸዉ ለግብፅ ጦር በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ ሰወስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በምታንቆረቁረዉ በአሜሪካ ዘንድ ተወዳጅ ናቸዉ

https://p.dw.com/p/193zF
epa03421199 A handout photo released by the Egyptian Presidency shows Egyptian President Mohamed Morsi (2-R) kissing the national flag next to Minister of Defence Abdel Fattah al-Sisi (R) during Morsi's visit to former Egyptian President Anwar al-Sadat's tomb in Cairo, Egypt, 04 October 2012. EPA/EGYPTIAN PRESIDENCY HANDOUT HANDOUT EDITORIAL USE ONLY/NO SALES +++(c) dpa - Bildfunk+++
አምና ወዳጅ መስለዉ ነበር አል-ሲሲና ሙርሲምስል picture-alliance/dpa


አምና ይሕን ጊዜ የሕዝባዊ አብዮት ድል አብነት፥ የሠላማዊ ትግል በጎ ዉጤት ተምሳሌት፥ የፍትሕ ዴሞክራሲ ጅምር ተስፋ ምድር ነበረች።ግብፅ።በዓመቱ ዘንድሮ የዘመናይ መፈንቅለ መንግሥት መፈተሻ፥ የዉዝግብ፥ ግጭት፥ ግድያ፥ የአለመረጋጋት ማዕከል፥ የርስ በርስ ጦርነት ሥጋት ናሙና ሆናለች።ለዘብ ባለ አገላለፅ መስላለች።ግብፅ።ፖለቲካዊ ትርምሷ መነሻ፥ ቅንጭብ ታሪኳ ማጣቀሻ፥ ሒደት፥ ሥጋቱ መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ሰኔ 24.2012 ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።ካይሮ።ምርጫ ኮሚሽን ፅሕፈት ቤት።
የምርጫ ኮሚሽን ፅሕፈት ቤት ሐላፊ ፋሩቅ ሡልጣን።

ከክርስቶሥ ልደት በፊት ከአስረኛዉ አመዓት ጀምራ-አደን አሳ ማስገር በእሕል ማብቀል፥ መትከል፥ በመፍጨት መጋገር አብዮት፥ የኒሎቲኮች ባሕል፥ በዳሪያን፥ በናቅዳዎች ባሕላዊ አብዮት የተለወጠባት፥ የሜናሶች፥ የኑቢያዎች፥ የቶባሶች አስተዳደር በፈርዖኖች አብዮት የተቀየረባት፥ የሮሞች፥ የፋርሶች፥ የቱርኮች አገዛዝ በአዉሮጶች ቅኝ አገዛዝ የተለወጠባት።የአይሁዶች፥ የክርስቲያኖች የሙስሊሞች አስተምሕሮት የተፈራረቁባት-ምድር---።

የቅምጥል፥ ዋልጌ ነገስታት አገዛዝ በብሔረተኛ የጦር ጄኔራሎች አብዮት የተደመሰሰባት፥ ወታደራዊ ሶሻሊዝም፥ በወታደራዊ ካፒታሊዝም የተተካባት ያቺ፥- የጥንታዊ ባሕል ቅርስ ጎተራ፥ ያቺ የታሪክ እምቅ መጋዘን፥ ያቺ የሥልጣኔ እምብርት ሐገር በእልፍ-አእላፍ ዘመናት ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝቧ የሚሻዉን መሪ በድምፁ መረጠባት።አምና።ተሕሪር አደባባይ።ፌስታ።

እንደገና ካይሮ፥ ግን፥ ዘንድሮ፥ ባለፈዉ ሮብ ማታ።ሐምሌ ሰወስት ሁለት ሺሕ አስራ-ሰወስት።ጄኔራል አብደል ፈታሕ አል-ሲሲ።የግብፅ ጦር ሐይል ጠቅላይ አዛዥ እና መካለከያ ሚንስትር።

«ከሕዳር ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት ጀምሮ ጦሩ፥ ሁሉም ፖለቲከኞች እና የሐገሪቱ ሐይላት የሚቀበሉት ብሔራዊ ድርድር እንዲደረግ ጠይቆ ነበር።ፕሬዝዳንቱ ግን ይሕን ጥያቄ በመጨረሻዉ ሠዓት ዉድቅ አደረጉት።»

እና ወደ አስራ-አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ወይም መምረጥ ከሚችለዉ የግብፅ ሕዝብ ሐምሳ ሁለት በመቶ ያሕሉ የመረጣቸዉ ፕሬዝዳት በአንድ ጄኔራል አጭር፥ ቀጭን ትዕዛዝ ከሥልጣን ተወገዱ።

ካይሮ አምና። ተሕሪር አደባባይ።ወጣት ናት።ፕሬዝዳት ሁስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ከተወገዱበት ጊዜ ጀምሮ የግብፅን የመሪነት ሥልጣን የያዘዉ የጦር ሐይሎች ላዕላይ ምክር ቤትን አገዛዝ በመቃወም ተሕሪሪ አደባባይ ከከተሙት ሚሊዮኖች አንዷ ናት።

እሱም ወጣት ነዉ።ሁለተኛዉ።

ብዙዎችም ድሉ በርግጥ የመላዉ ግብፃዉያን ነዉ ብለዉ ነበር።እሳቸዉ ደግሙት ያኔ። ሰኔ ሃያ-ዘጠኝ ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት።

«ምን ጊዜም ለሥልጣናችን መከበር እና ለአንድናትችን መጠበቅ እጥራለሁ።የሕዝቡን እና የተወካዮቹን ሥልጣን ለመንጠቅ የሚደረግ ሙከራን ለመከላከል እንደምጥር አረጋግጣለሁ።»

ዶክተር ኢንጂነር መሐመድ መሐመድ ሙርሲ ኢሳ አል-አያም።ካለፈዉ ሮብ ጀምሮ ሥልጣናቸዉ የቀድሞዉ ፕሬዝዳት፥ ሥፍራቸዉ እስር ቤት ነዉ።አምና አንድ የነበረችዉ ወይም አንድ እንድትሆን እጥርላታለሁ ያሏት ግብፅም፥ ካይሮ ላይ የአባይ ወይም የናይል ወንዝ ማዶ ለማዶ ተብላ እሁለት ተገምሳለች።ካባይ አንደኛዉ ማዶ፥-ተሕሪ አደባባይ አለ።ሐሙስ።

«እዚሕ አደባባይ እንዳሉት ግብፃዉያን ሁሉ በጣም ደስ ብሎኛል።እርምጃዉ (የጦሩ) ነፃነታችንን ከአክራሪዎች አስመልሷል ማለት ይቻላል።እነሱ (ሙስሊም ወንድማማቾች) ለግብፅ ሕዝብ ብዙ ችግሮች ፈጥረዉበታል።»

ከአባይ የወዲያኛዉ ማዶ፥ ካለዉ ሌላ አደባባይ ሌላ ታሪክ ይነገራል።

«ፕሬዝዳንታችን ወደ ሥልጣናቸዉ እስኪመለሱ ድረስ ከዚሕ አንነቃነቅም።አ-ሲሲ ፕሬዝዳንታችን አይደሉም።መፈንቅለ መንግሥት ነዉ-ያደረጉት።»

የሁለቱ ጠላቶች ወዳጅነት።ፊልድ ማርሻል መሐመድ ሁሴይን ታንታዊ የሚመሩት የግብፅ ጦር ሐይል ላዕላይ ምክር ቤት በአብዛኛዉ የግብፅ ሕዝብ ዘንድ እንደተጠላ፥የሚያስተናብራቸዉ ጄኔራሎች ከሆስኒ ሙባረክ ተለይተዉ እንደማይታዩ፥ ዶክተር መሐመድ ሙርሲ ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ።የዚያኑ ያሕል የጦር ሐይሉን እርምጃና አገዛዝ በመቃወም ተሕሪሪ አደባባይን ያጨናነቀዉን ሕዝብ ፍላጎት ለማርካት ሲባል ሁሉንም ጄኔራሎች ከሥልጣን ማስወገዱም በጦር ሐይሉ ዘንድ የሚያስከትለዉን ቁጣ አዲሱ ፕሬዝዳት አላጡም።

ድንገት የሐገር መሪ የሆኑት ኢንጂነር ልክ እንደሳቸዉ ሁሉ ባጋጣሚ ቤተ-መንግሥት ከገቡ በኋላ ፖለቲከኛ ለመሆን ከሚፍጨረጨሩት ጄኔራሎች መሐል ከሙባራክ አገዛዝ ራቅ፥ ከፖለቲካዉ ፈንገጥ፥ በእድሜ ወጣት የሆኑትን ሲያፈላልጉ ብዙ አገኙ።የሙስሊም ወንድማማቾች የረጅም ጊዜ አባል የሆኑትን ኢንጂነር ልብ ለማማለል ግን የእሳቸዉን ያክል የለም።ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል-ሲሲ።ሶላት፥ ጦማቸዉ አይዛነፍም።ሐይማኖተኛ ናቸዉ።

ሐይማኖተኛ በመሆናቸዉ እንዳድ የግብፅ መገናኛ ዘዴዎች በወታደራዊዉ ምክር ቤት የሙስሊም ወንድማማቾች ተወካይ በማለት እስከ መዉቀስ ደርሰዉም ነበር።ሰዉዬዉ ግን እንዲያ አልነበሩም። ብሪታንያም አሜሪካም የተማሩ በመሆናቸዉ ለግብፅ ጦር በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ ሰወስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በምታንቆረቁረዉ በአሜሪካ ዘንድ ተወዳጅ ናቸዉ።ሐምሳዎቹን የእድሜ ክልል ያጋመሱ ግን ባንፃራዊ መመዘኛ ከግብፅ ወጣት ጄኔራሎች አንዱ ናቸዉ።

ነሐሴ-አስራ ሁለት።ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት። የግብፅ ፕሬዝዳት እና የጦር ሐይል የበላይ አዛዥ መሐመድ ሙርሲ እኚያን ጄኔራል የግብፅ ጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና የሐገሪቱ መከላከያ ሚንስትር አድርገዉ ሾሟቸዉ።የሁለቱ ጠላቶች ወዳጅነት ፀና።ወይም የፀና መሠለ።

«ከዚች ሐገር ሕዝብ ጋር ሆኜ ለሐገሪቱ የሚበጀዉን ሁሉ ለማድረግ አበክሬ ጥሬአለሁ።ባንዳዶቹ ትክክለኛ ነበርኩ፥ በሌሎቹ ተሳስቼአለሁ።»

አሉ መሐመድ ሙርሲ በቀደም።እኛን ዝምተኛ፥ አይናፋር፥ የጦር ሐይሎች የመረጃ ጄኔራል እንደ ወዳጅ ማቅረብ መሾማቸዉ ምናልባት ከብዙ ስሕተታቸዉ አንዱ ሊሆን ይችላል።ሆነም አልሆነ ወዳጆች የመሰለዉ ጠላትነት ፈጥጦ ለመዉጣት አመት አልፈጀም።አል-ወጠን የተሰኘዉ የግብፅ ጋዜጣ የሁለቱን «ወዳጆች» የመጨረሻ የጠላትነት ጭዉዉት በከፊል እንዲሕ አሠፈረዉ።

ፕሬዝዳንት ሙርሲ፥ ጦር ሐይሉ የመንግሥታቸዉን ሕጋዊነት የማስከበር ሐላፊነት እንዳለበት ጄኔራሉን ጠየቁ።
«የምን ሕጋዊነት?» መለሱ ጄኔራሉ ጥያቄዉን በጥያቄ፥ አከሉም፥- «ጦሩ የሕዝቡን ፍላጎት ነዉ የሚከተለዉ።በደረሰን ዘገባ መሠረት አብዛኛዉ ሕዝብ እርስዎን አይፈልግም።»

«የኔ ደጋፊዎችም ብዙ ናቸዉ።አርፈዉ አይቀመጡም።» አሉ ፕሬዝዳንቱ።ፈርጠም ብለዉ።

«ጦር ሐይሉ ሐገሪቱን የሚያፈርስ ማንንም ቢሆን አይታገስም» ዛቱ ጄኔራሉ።
«ሥልጣን አለቅም ብልስ?» ጠየቁ ፕሬዝዳንቱ አሁን ተለሳልሰዋል።
«የተወሰነ ጉዳይ ነዉ» መለሱ ቆፍጣናዉ ጄኔራል።

ከዚያ በሕዋላ ሙርሲ እስር ቤት ተወረወሩ።

ሐምሌ 1952 የተቀጣጠለዉን፥ የሐምሌ ሃያ-ሰወስቱ አብዮት የተሰኘዉን የግብፅ የጦር መኮንኖች አመፅ የመሩና ያስተባበሩት ኮሎኔል ገማል አብድ ናስር ነበሩ።ናስር የመሩት አመፅ የእስከያኔዉን የግብፅ ንጉስ ፋሩቅን ዙፋናዊ አገዛዝ ሲገረስስ፥ ናስር፥ ጄኔራል መሐመድ ናጉብን ፕሬዝዳት ብለዉ ግብፅን ከኋላ ሆነዉ ይዘዉሩ ገቡ እንጂ እራሳቸዉ ናስር ተሽቀዳድመዉ ቤተ-መንግሥት አልገቡም።

አል-ሲሲ እንደብዙዎቹ የግብፅ ጄኔራሎች ገማል አብድናስርን እንደ ጀግና ያድንቁ፥ ያወደሱ፥ እንደ ብሔረተኛ ይዉደዷቸዉ እንጂ ናስር አይደሉም።በቀደም ግን በርግጥ ናስር መሠሉ።የመሐመድ ሙርሲን መንበር አልያዙም።ናጉባቸዉን ፈለጉ።ዳኛ አድሊ መንስሩን አገኙ፥ ቤተ-መንግሥቱን ከጊዚያዊ ፕሬዝዳትነት ቅፅል ጋር አስረከቧቸዉም።

«ሕግና ሕገ-መንግሥቱን ለማስከበር እና ሐገሪቱን በተገቢዉ መንገድ ለማስተዳደር በፈጣሪ ሥም ቃል እገባለሁ።»
ዳኛ መንሱር የሚያስከበሩት ሕገ-መንግሥት የለም።በሿሚያቸዉ ጄኔራል ተሽሯል።በሕዝብ የተመረጠዉ ፓርላማ ተበትኗል።የሚያስተዳድሩት መንግሥትም ቢያንስ እስካሁን የለም። ወትሮም ካደባባይ ያልተለየዉ የግብፅ ሕዝብ ግን እሁለት ተገምሶ-ይወዛገብ ይጋጭል፥ በፖሊስና በጦር ሐይሎች ይገደል ገባ።ካይሮ አርብ።

«ሁለት የፖሊስ መኪኖች ወደኛ መጡ እና አስለቃሽ ጋዝ ረጩብን።ወዲዉ ብዙ ሰዎችን ይደበድቡ ያዙ። ጥይትም ተኮሶብን።አስራ-ስምንት ሰዉ ተገደለ።»

ይላሉ ከቀድሞዉ ፕሬዝዳት ደጋፊዎች አንዱ።ሐሙስ ወደ ሃያ የሚጠጋ ሰዉ መገደሉ ተዘግቦ ነበር።ግድያዉ ቅዳሜምና እሁድም ቀነስ ብሎ ግን ቀጥሏል።ዛሬ በረመዳን ዋዜማ ደግሞ ጄኔራል አል-ሲሲ የሚያዙት ጦር ለግብፅ ሕዝብ ሲበዛ-ሐምሳ ሰወስት ሲያንስ አርባ-ሁለት አስከሬን ለረመዳን ስጦታ አቅርበለት።

አብዛኞቹ ሟቾች የሙስሊም ወድማማቾች ደጋፊ ወይም አባላት ናቸዉ።ሙስሊም ወድማማቾች ግድያዉን «ጭፍጨፋ» በማለት ሲያወግዘዉ፥ የሙርሲን ከሥልጣን መወገድ ደግፎ የነበረዉ የሳላፊስቶቹ ቡድን ደግሞ ግድያዉን በመቃወም የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ከሚደረገዉ ድርድር ራሱን አግልሏል።ጦር ሐይሉ በሰጠዉ መግለጫ ግን የተገደሉትን «ታጣቂ አሸባሪ» ብሏቸዋል።

የደማስቆ መንግሥት ላለፉት ሁለት ዓመታት የሚደጋግማት ሐረግ-ካይሮም ታቃጭል ያዘች። ከእንግዲሕ? እዚሕ ቦን በሚገኘዉ ዓለም አቀፉ ጥናት ተቋም የግጭት ጉዳዮች አጥኚ አሕመድ ኸሊፋ እንደሚሉት የግብፅ የከእንግዲሕ ጉዞ ለፖለቲካ አዋቂ ትንታኔም ግራ-አጋቢ ነዉ።

«(የወደፊቱን) ማወቅ አይቻልም።ትናንት (ቅዳሜ) የሙስሊም ወድማማቾች ደጋፊዎች ተሰልፈዉ የነበሩበትን አካባቢ ለቀዉ ነበር።በየአዉራ መንገዱም መረጋጋት ነበር።ይሕ ግን ከትልቅ ማዕበል በፊት የሚታይ ሠላም-ይሁን፥ አይሁን አይታወቅም።»

የሚሆነዉ ሲሆን፥ ለማወቅ ያብቃን።ለዛሬዉ ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

CAIRO, EGYPT - JULY 08: Following a day of massive rallies against the ousted Egyptian President and an early morning shooting of pro Mohamed Morsi supporters outside a Presidential Guard barracks, members of the Egyptian military and their supporters guard a bridge near Tahrir Square on July 8, 2013 in Cairo, Egypt. Egypt continues to be in a state of political paralysis with scores of people having been killed and many injured in recent days as the Egyptian military attempts to restore order across the country following their ousting of Morsi. (Photo by Spencer Platt/Getty Images)
የሙርሲ ደጋፊዎች በታንክ መሐልምስል Getty Images
An Egyptian man carries portrait of army chief and Defense Minister Gen. Abdel Fattah al-Sisi outside the presidential palace in Cairo calling for the ouster of President Mohamed Morsi on July 1, 2013. Egypt's armed forces warned that it will intervene if the people's demands are not met within 48 hours, after millions took to the streets to demand the president's resignation. AFP PHOTO / KHALED DESOUKI (Photo credit should read KHALED DESOUKI/AFP/Getty Images)
የጄኔራሉ አድናቂዎችምስል Khaled Desouki/AFP/Getty Images
Protesters, who are against Egyptian President Mohamed Mursi, react in Tahrir Square in Cairo July 3, 2013. The head of Egypt's armed forces General Abdel Fattah al-Sisi issued a declaration on Wednesday suspending the constitution and appointing the head of the constitutional court as interim head of state, effectively declared the removal of elected Islamist President Mohamed Mursi. REUTERS/Suhaib Salem (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST)
የሙርሲ ተቃዋሚዎችምስል Reuters
A poster of deposed Egyptian President Mohamed Mursi is seen during a protest in Cairo July 7, 2013. Thousands of supporters of Egypt's ousted President Mohamed Mursi protested outside his place of detention in Cairo on Sunday while a military-driven plan to resolve the political crisis remained mired in mistrust and confusion. REUTERS/Mohamed Abd El Ghany (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST)
ዘንድሮ የሙርሲ ደጋፊዎችምስል Reuters
Members of the Muslim Brotherhood and supporters of Egypt's President Mohamed Mursi hold pictures of him as they react after the Egyptian army's statement was read out on state TV, at the Raba El-Adwyia mosque square in Cairo July 3, 2013. Egypt's armed forces overthrew elected Islamist President Mursi on Wednesday and announced a political transition with the support of a wide range of political, religious and youth leaders. A statement published in Mursi's name on his official Facebook page after head of Egypt's armed forces General Abdel Fattah al-Sisi's speech said the measures announced amounted to "a full military coup" and were "totally rejected". REUTERS/Khaled Abdullah (EGYPT - Tags: POLITICS CIVIL UNREST TPX IMAGES OF THE DAY) - eingestellt von gri
ዘንድሮ የሙርሲ ደጋፊዎችምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ





























ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ