1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካናዳ ኩባንያና የኦብነግ ማስጠንቀቂያ

ረቡዕ፣ የካቲት 13 2005

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር፣ ኦብነግ፣ አንድ የካናዳ የነዳጅ ዘይት አውጪ ኩባንያ በኦጋዴን እንዳይሰማራ አስጠነቀቀ። ኦብነግ ባለፈው ሰኞ ባስተላለፈው መግለጫው ኩባንያው በስፍራው ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ሥራውን መጀመር የለበትም ብሏል።

https://p.dw.com/p/17iKn
ምስል picture alliance/dpa

የኢትዮጵያ መንግስት ግን ይኸው የኦብነግ ማስጠንቀቂያ፣ ግንባሩ ስለተዳከመ፣ ሊያደርስ የሚችል ችግር የለም ሲል ማስጠንቅያውን አጣጥሏል። የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር፣ ኦብነግ፣ አፍሪካ ኦይል ኮርፖሬሽን የተሰኘው ኩባንያ በኦጋዴን የዘይት ሐብት ፍተሻ ከመጀመር እንዲቆጠብ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የግንባሩ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሐሰን ሙዓሊን እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ መንግስትና በኦብነግ መካከል ውጊያ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ኩባንያዎችን አስመጥቶ በኦጋዴን የተፈጥሮ ሐብት ለመጠቀም አቅዶዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ይህን የኦብነግ ማስጠንቀቂያ ተራ ማስፈራርያ ሲል አጣጥሎታል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለዶቼቬሌ እንደተናገሩት በኦጋዴን እየታየ ባለው ልማት ምክንያት የተነሳ፣ በአካባቢው ለኦብነግ ያለው ድጋፍ እየቀነሰ መጥቶዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ከኦብነግ ጋር ለማድረግ ያቀደው የሰላም ድርድር አልተሳካም። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት አንዳንድ የኦብነግ አንጃ ቡድኖች ትጥቅ ፈተው ከመንግስት ጋር በሰላማዊ መንገድ እንዲሰሩ በማድረጉ፣ የኦብነግ ኃይል እንደተዳከመ ተገልጿል። እንደ አቶ ሐሰን ሙዓሚን ግን የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር፣ ኦብነግ አሁንም በፖሊቲካው እና በጦር ኃይል ጠንካራ ነው፣

የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር፣ ኦብነግ በተለያዩ ጊዜያት የውጭ ኩባንያዎች የኦጋዴንን የተፈጥሮ ሐብትን እንዳይነኩ አስጠንቅቋል። ኦብነግ በኦጋዴን በተሰማራው የቻይና የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ሰራተኞች ላይ እአአ በ2007 በጣለው ጥቃት ከሰባ በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

Dürre in Ostafrika: Äthiopien
ምስል AP

ገመቹ በቀለ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ