1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ምርጫና ዉዝግቡ

ሰኞ፣ ግንቦት 17 2007

ኢትዮጵያን ለአስራ-አራት ዓመት የመራዉ የቀድሞዉ አማፂ ቡድን ኢሕአዴግ ጠመጃ-መትረየሱን አስቀምጦ (ባንዳዶች አገላለጥ ደብቆ) የምርጫ ካርድ የጨበጠበት፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ክፍፍል ንትርካቸዉን ሸፍነዉ ባንድ የቆሙበት፤ ጋዜጠኞች፤ የመብት ተሟጋቾች፤የሲቢል ማሕበራት ድንከመታቸዉን በጥንካሬ-የከደኑበት-ታሪክ።ያኔም ታዲያ ግንቦት ነበር።

https://p.dw.com/p/1FWHF
ምስል DW/Y.-G. Egziabhare

[No title]

ኢትዮጵያዉያን መረጡ።አልመረጡምም።ትናንት።ታሪክ ለሞላባት፤ ከታሪክ ብዙም ለማትጠቀመዉ፤ ምንም ለማትማረዉ ግን ታሪክ ለማትጠግበዉ ሐገር ሌላ-ታሪክ።

እነሱ ድምፅ ሰጡ።መረጡ።እነዚሕኞቹም ድምፅ ሰጥተዋል።ግን አንድም አልመረጡም።ሁለትም መራጭ፤አስመራጩ ፈጣሪ ነዉ ባይ ናቸዉ።

እነሱ አልመረጡም።ግን ተመረጠላቸዉ።እሷ በርግጥ መርጣለች። ሌሎቹንም ታሳስባለች። በእንግሊዝኛ-አማርኛ ቅይጥ ቋንቋዋ። ማሳሰቢያዉ ለነሱ ነዉ።ለ ወጣቶቹ።

Wahltag in Äthiopien
ምስል DW/T. Haile-Giorgis

እሳቸዉ ፖለቲከኛ ናቸዉ። የምክር ቤት እንደራሴ። ኢትዮጵያ መረጠች፤ አልመረጠችም። ወይስ ተመረጠላት።ከትናንት የተረፈን ጥያቄ። ግንቦት 1983 እስከ ዛሬ ላልተመለሰ ጥያቄ-የዳረገ ታሪክ ተፈፅሞባት ነበር።የአስራ-አራተኛ ክፍለ-ግዛትዋ ነፃነት ከአዲስ አበባ የተፈቀደበት፤ወደብ አልባነቷ የተረጋገጠበት-ታሪክ።

አስራ-ሰባት ዘመን የፀናዉ ወታደራዊ፤ ሶሻሊስታዊ መንግሥት በእስከያኔዉ አማፂ ቡድን የተተካበት፤ የሠላም፤የዴሞክራሲ፤ የፍትሕ ተስፋ የተንዠቀዥቀበት-ታሪክ።በርግጥም የተስፋዉን ያክል አይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከቀድሞ አካሏ-ከአዲስ ጎረቤትዋ ጋር መቶ ሺዎችን ካረገፈዉ ጦርነት እስከተዘፈቀችበት ድረስ አንፃራዊ ሠላም ሰፍኖባታል።ያኔም ግንቦት ነበር።1990

ከጦርነቱ በፊት ብቅ ያለዉ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት፤ የፕረስ ነፃነት፤የፍትሕ ዴሞክራሲያ መርሕ በጦርነቱ መሐልም፤ በጦርነቱ ማግሥትም ብልጭ ድርግም እያለ አዝግሞ ታሪካዊቱን ሐገር ለሌላ ታሪክ አቀበለ።ለ1997ቱ።

ኢትዮጵያን ለአስራ-አራት ዓመት የመራዉ የቀድሞዉ አማፂ ቡድን ኢሕአዴግ ጠመጃ-መትረየሱን አስቀምጦ (ባንዳዶች አገላለጥ ደብቆ) የምርጫ ካርድ የጨበጠበት፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ክፍፍል ንትርካቸዉን ሸፍነዉ ባንድ የቆሙበት፤ ጋዜጠኞች፤ የመብት ተሟጋቾች፤የሲቢል ማሕበራት ድንከመታቸዉን በጥንካሬ-የከደኑበት-ታሪክ።ያኔም ታዲያ ግንቦት ነበር።1997።የሠላም፤ የዴሞክራሲ፤ የፍትሁ ተስፋ-ከተስፋ አልፎ በገቢር ብልጭ ያለበት ምርጫ።ግን-በ1983ቱ ግንቦት የሠፈረባት ዛር-ምሥ- ግብሩ ደም ሆነና-1997ቱን ምርጫ ያጀበዉ ቦረንትቻም ዉል ስቶ-በዉስዝግብ፤ ግጭት፤ግድያ፤ እስራት እመቃ፤ ክፍፍል አሳረገ።

በአምስተኛ ዓመቱ፤ በ2002 ሌላ ምርጫ ሲደረግ በ1997 እንደ ተወርዋሪ ኮኮብ ተግ-ቦግ፤ብሎ ባፍታ ጥፍት-ድርግም ያለዉ ተስፋ በርግጥ ትዝታ ነበር።ግን እንደገና ግንቦት።እንደገና ምርጫ።እንደገና አዲስ ታሪክ።ምናልባትም የሉሲን በመሠለ ቅርሷ፤ ቀይ ቀበሮን በመሰሉ አራዊቶችዋ፤ የአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎችን ድል በመንሳት ጀግንነቷ፤ በዓለም የምትደነቀዉ ሐገር።በ2002ትም ነፃ ምርጫ አስተናገደች ተብላ ለገዢ ፓርቲዋ ኢሕአዴግ የ99,6 በመቶ ድል አስመዝግባ ዓለምን አስደነቀች።

Stimmauszählung in Äthiopien Hosaena
ምስል DW/Y.-G. Egziabhare

በያኔዉ ምርጫ-ለምክር ቤት እንደራሴነት የበቁት ብቸኛዉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል አቶ ግርማ ሠይፉን ሥለ ትናንቱ ምርጫ እንዲነግሩን «ሐሎ» አልናቸዉ ዛሬ።

የመረጠም፤የተመረጠለትም፤ ምርጫ የለም ብሎ ተስፋ የቆረጠዉም ኢትዮጵያዊ ተቃራኒ ስሜት የተንፀባረቀበት የትናንቱ ምርጫ ሌላ ዕዉነትም ታይቶበታል።ዕዉነት አንድ፤- የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠንካራ መሪ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከሞቱ ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነዉ።ዕዉነት ሁለት፤ ከዚሕ ቀደም የተደረጉ ምርጫዎችን በተለይም የ1997ቱን እና 2002ቱን በቅርብ የተከታተሉት የአሜሪካዉ የካርተር ማዕከል እና የአዉሮጳ ሕብረት ታዛቢዎች ሒደቱን አልተከታተሉትም።

የካርተር ማዕከል የዘንድሮዉን ምርጫ ያልታዘበበትን ምክንያትን በግልፅ እናዉቅም።የአዉሮጳ ሕብረት ግን ታዛቢዎቹን ላለመላኩ-የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ የሰጡት ምክንያት የሐብታሙ ማሕበር «የገንዘብ፤ በጀት እጥረት» ሥላለበት የሚል ነበር።የአዉሮጳ ሕብረት ባለሥልጣናት ግን በሰወስት ወር ዉስጥ ሰወስት ምክርንያቶችን ተናግረዋል።የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ-ያስታዉሰዋል።

በትናንቱ ምርጫ ድምፁን ለመስጠት 37 ሚሊዮን ሕዝብ ተመዝግቦ ነበር።ከተመዘገበዉ ድምፁን የሠጠዉን ሕዝብ ቁጥር ለማወቅ ትንሽ ጊዜ ይጠይቃል።የምርጫዉ ዉጤም እንዲሁ።አቶ ግርማ ግን መራጩንም-ዉጤትንሙ መገመቱ አይገድም ባይ ናቸዉ።

Stimmauszählung in Äthiopien Hosaena
ምስል DW/Y.-G. Egziabhare

የትናንቱን የድምፅ አሰጣጥ ሒደት የተከታተሉት ፖለቲካ ተንታኝ ሳንዴ ኦኬሎ እንደሚሉት ከምርጫዉ ዘመቻ ጀምሮ ደከማ የነበሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከትናንቱ ምርጫ «ተዓምር ሊጠብቁ አይገባም» ባይ ናቸዉ።

«በምርጫ ዘመቻዉ ወቅት ገዢዉን ፓርቲ በቅጡ የፈተኑ፤ ጠንካራ ተቃዋሚዎች በእዉነቱ አላየሁም።ይሁንና አንዳዶቹ ተቃዋሚዎች ሐሳቦቻቸዉን በግልፅ ለማሳየት የሞከሩ ነበሩ።ብዙ ቁጥር ያለዉ ድምፅ በማግኘት ግን ገዢዉን ፓርቲ የሚያሰጉ አይደሉም።»

ቁጥር-የመቶኛ ሥሌቱ ባናዉቀዉም ኢሕአዴግ ማሸነፉ እርግጥ ነዉ።እና ኢትዮጵያን መምራቱን ቢያንስ ለአምስት ይቀጥላል።ኢትዮጵያ ከዉጪ በተለይም ከምዕራባዉያን ጋር የሚኖራት ግንኙነትም በነበረበት መቀጠሉ የማይቀር ነዉ።ገበያዉ

ወደፊት ይታያል።ኢሕአዴግ ሥልጣን የያዘበት 30ኛ ዓመት በዓልም ከስድስተኛዉ ብሔራዊ ምርጫ ጋር ሲከበርም እናይ ይሆናል።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ