1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን እንዲፈታ አዲስ ጥሪ ቀረበ

ዓርብ፣ መስከረም 16 2007

ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) መሰረት ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን ለስደት በመዳረግ ኤርትራን ተከትላ ከአፍሪቃ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ መንግስት በአከራካሪው የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ጋዜጠኞችን ለእስር፤እንግልትና ስደት ይዳርጋል ሲሉ አለም አቀፍ ተቋማት ይተቻሉ።

https://p.dw.com/p/1DLfs
Symbolbild Zeitungen in Ketten
ምስል Vladimir Voronin - Fotolia.com

ተቋማቱ መንግስት ያሰራቸውን ጋዜጠኞች እንዲፈታ በተጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የታሰሩት በሙያቸው አለመሆኑን በመግለጽ ይከራከራል። የአፍሪቃ ጋዜጠኞች ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን እንዲፈታ አዲስ ጥሪ አቅርቧል።እሸቴ በቀለ ዘገባ አለው።

Symbolbild Spickzettel
ምስል Fotolia/lassedesignen

ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፤ አስማማው ሃይለጊዮርጊስና ኤዶም ካሳዬ ከዞን ዘጠኝ ስድስት የኢንተርኔት ጸሃፊያን ጋር በኢትዮጵያ የታሰሩት ሚያዝያ 17 / 2006 ነበር። በአወዛጋቢው የጸረ ሽብር አዋጅ ህገ መንግስቱን በሀይል ለመናድ በመሞከር ወንጀሎች በኢትዮጵያ መንግስት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች ለፍርድ ቤት ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሆኖ ዛሬም በእስር ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ፍትህ ሚኒስቴር አምስት የመጽሄቶችና አንድ ጋዜጣ አሳታሚዎችና ሥራ አስኪያጆችን ሃሰተኛ ወሬዎች በማውራት፣ ለአመፅ የሚያነሳሱ ፅሁፎችን ለህዝብ በማድረስ፣ በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርአቱ ላይ አመፅ ለማስነሳት ሞክረዋል በሚል መክሰሱን ተከትሎ በርካታ ጋዜጠኞች ተሰደዋል። እነዚህን ጨምሮ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ላይ የደረሰው እስርና ስደት የአለም አቀፍ የብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ማህበራት ዘንድ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ትችት እንዲሰነዘርበት አድርጓል። መቀመጫውን በሴኔጋል ዳካር ያደረገው የአፍሪካ ጋዜጠኞች ፌዴሬሽንም መንግስት በእስር ላይ ያሉትን ጋዜጠኞች እንዲፈታ የተሰደዱትም ወደ ሃገራቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻች ጥሪ አቅርቧል። በአዲስ አበባ ተገኝተው መንግስትና ጋዜጠኞችን ያነጋገሩት በዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን የአፍሪቃ ዳይሬክተር ጋብሬል ባግሎ የተመለከቱት የመገናኛ ብዙሃን ይዘት ለመንግስት ያደላ መሆኑን ይናገራሉ።

Karte Äthiopien englisch

''በአማርኛ የሚታተሙ ጋዜጦችን በማንበብ ይዘታቸውን መገምገም ባልችልም በእንግሊዝኛ ከሚታተተሙት ጥቂቶቹን ለመመልከት እድል አግኝቼ ነበር።ብዙዎቹ ከመንግስት የተለየ አቋም አልተመለከትኩባቸውም።የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችንም አነጋግሪያለሁ።በጥቃቅን የተጠያቂነት ጉዳዮች ጋዜጠኞች ለእስርና ስደት እየተዳረጉ በመሆኑ ደስተኞች አይደሉም።ለዚህ መፍትሄው መንግስት መገናኛ ብዙሃንን ማሳተፍ ይኖርበታል።ሁለቱም ለአንድ ሃገር የሚሰሩ በመሆኑ የጋራ መግባባት መኖር አለበት።መንግስትም የመገናኛ ብዙሃንን ህግ በመረዳት ስራቸውን እንዲሰሩ ሊፈቅድ ይገባል።''

ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን የሙያውን ስነ-ምግባር በማክበር መስራትና መንግስትን መተቸት ይችላሉ የሚሉት ጋብሬል ባግሎ ውይይትና ንግግር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

''ጋዜጠኞች የሙያውን ስነምግባር እንደማያከብሩ የኢትዮጵያ ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ባለስልጣናት ነግረውናል።እኛም በተጠያቂነት ስም ጋዜጠኞችን በሙሉ ወደ እስር ቤት መላክ እንደማይቻል ነግረናቸዋል።በአንድ ሃገር ማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውይይት ሊኖር ይገባል።ጋዜጠኞቹም ተስፋ ባይኖር እንኳ መንግስት የመገናኛ ብዙሃንን ጥቅም እስኪረዳ ድረስ የመንግስት አካላትን በማሳተፍ ውይይቱን ማሳደግ አለባቸው። የጋዜጠኛ ቦታ እስር ቤት ሳይሆን የዜና ቢሮው ነው።''

Symbolbild Zensur Pressefreiheit
ምስል picture alliance / Stefan Rupp

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የጋዜጠኞች ማህበራት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን የሚደርስባቸውን እስርና ስደት አስመልክተው በተደጋጋሚ መንግስትን የሚተቹ መግለጫዎች አውጥተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የታሰሩት በጋዜጠኝነታቸው ምክንያት አለመሆኑን እና አንድም ጋዜጠኛም አለመሰደዱን በተለያዩ ጊዜያት ሲናገር ተደምጧል።በኢትዮጵያ ሊቋቋም ነው የተባለውን የሚዲያ ካውንስል እኛም እንደግፋለን የሚሉት ጋብሬል ባግሎ አሁንም የታሰሩት ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ይጠይቃሉ።

''ሰዎች ከመግስት አቋም ጋር ያለመስማማት እንዲያውም የመተቸት መብትም አላቸው።ይህ በየትኛውም ሃገር የተለመደ ነው።በእስር ላይ ያሉት ሰዎች መንግስት እንደሚለው ጋዜጠኞች ባይሆኑ እንኳ የታሰሩት ሃሳባቸውን በነፃነት በመግለጻቸው ነው ማለት ነው።ሰዎች ሃሳባቸውን ስለገለጹ ሊታሰሩ ይገባል ብለን አናምንም።እናም የኢትዮጵያ መንግስት የታሰሩትን ጋዜጠኞች እንዲፈታ፣ የተሰደዱትም ተመልሰው ለሃገራቸው እንዲሰሩ እንዲፈቅድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።''

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ