1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ ሚኒስትሮች ሹመት

ዓርብ፣ ሰኔ 28 2005

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት የሰየሟቸዉን የአዳዲስ ሚኒስትሮች ሹመት ዛሬ ምክር ቤት አጸደቀ። በአዲሱ ሹመት መሠረትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር አማካሪ ሚኒስትሮች ተሹመዋል።

https://p.dw.com/p/192NM
ምስል DW

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጌታቸዉ ረዳ በዚህ አዲስ በተፈጠረዉ የሥራ መስክ ተሿሚዎቹ የካበተ ልምዳቸዉን ተጠቅመዉ መንግስትንም አገርንም የበለጠ ያገለግላሉ ተብሎ እንደሚታመን ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን እና የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩት አቶ ኩማ ደመቅሳ ሁለቱም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር አማካሪ ሚኒትሮች ሆነዋል። አቶ ጌታቸዉ ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የባለስልጣናቱ ሥራ በዓላማዉ ብቻ ነዉ የሚመሳለሰለዉ ይላሉ።

Äthiopien Ministerpräsident Hailemariam Desalegn
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝምስል Getty Images

አንዳንድ ዘገባዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ካቢኔ አወቃቀር ቀጣይ ሹም ሽሮች እንደሚጠበቁ ያመለክታሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጌታቸዉ ረዳ በበኩላቸዉ የተወሰኑ የፌደራል መንግስት የስልጣን ቦታዎች ብቻ ሊሞሉ እንደሚችሉ በማመልከት እንዳስፈላጊነቱ የሚሾም ካለም ይሾማል የሚሻርም ካለ እንዲሁ ነዉ ባይናቸዉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ከያዙ ከስምንት ወራት በላይ ተቆጥረዋል። ካቢኔያቸዉን ያዋቅራሉ እየተባለ ቢጠበቁም የተወሰኑ ሚኒስትሮችን ከመሾምና ከመሻር በስተቀር የአሁኑ ዓይነት በርካታ ሹመት አልሰጡም። የአሁኑ ሹም ሽር አለመዘግየቱን የገለጹት አቶ ጌታቸዉ ጊዜዉ የሚወሰነዉ ሽግሽጉ በሚፈለግበት ወቅት መሆኑን አመልክተዋል።

በዚሁ መሠረትም በአቶ በረከት ቦታ አቶ ሬድዋን ሁሴን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትርነቱን ተረክበዋል፤ በአቶ ኩማ ደመቅሳ ምትክ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሚሆኑት ደግሞ በአዲስ አበባዉ ምክር ቤት በፊታችን የሳምንት መጨረሻ እንደሚመረጡ አቶ ጌታቸዉ ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ