1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬንያ የሚገኙ ስደተኞች ሮሮና የ«ዩኤንኤችሲአር» አስተያየት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 16 2006

ኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ችግር እየተባባሰ መሄዱን እዚያ የሚገኙ ስደተኞች አስታወቁ ። የኬንያ መንግሥት ስደተኞች በሙሉ በሃገሪቱ ወደሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እንዲገቡ ካዘዘ ወዲህ በተለይ በከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የፍርሃትና የስጋት ህይወት እንደሚገፉ ለዶቼቬለ አስታውቀዋል ።

https://p.dw.com/p/1Bo6U
Kenia Dadaab, Somalische Flüchtlinge
ምስል Getty Images

በኬንያ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ በበኩሉ በከተሞች ኑሮአቸውን ሲገፉ የቆዩት ስደተኞች ጉዳይ መፍትሄ እንዲፈለግለት ለኬንያ መንግሥት ማሰሰቡን መቀጠሉን አስታውቋል።ድርጅቱ ችግሩ መፍትሄ ያገኛል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግም ተናግሯል ።ኬንያ ከ3 ሳምንት በፊት ያወጀችው አዲሱ ህግ በሃገሪቱ የሚገኙ ስደተኞች በሙሉ በሁለቱ የስደተኞች መጠለያዎች ማለትም በምሥራቅ ኬንያው የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ወይም ደግሞ በሰሜን ምዕራቡ በከካኩማ መጠለያ እንዲገቡ ያዛል ። ይህ ህግ ከታወጀ አንስቶ በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን «ዩኤንኤችሲአር»እውቅና የሰጣቸውም ሆነ ገና እውቅና ያላገኙት ስደተኞች መብታቸው መጣሱና መንገላታታቸውም መባባሱን ኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለዶቼቬለ አስታውቀዋል ።የኬንያ መንግሥት ስደተኞች በሙሉ ወደ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲገቡ ቢያዝም ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞችም እንደሚሉት መንግሥት ስደተኞች ይሰብሰቡ የሚልባቸው መጠለያዎች በሰዎች የተጨናነቁ የጤናና የፀጥታ ችግሮች ያሉባቸው ናቸው።

Flüchtlingslager Dadaab Kenia
ምስል AP

እነዚህ ችግሮች ጎልተው በሚታዩባቸው መጠለያዎች መግባት እጅግ አደገኛ ነው እንደ ኢትዮጵያውያኑ በአዲሱ ህግ ምንክንያት ደግሞ ናይሮቢን በመሳሰሉ ከተሞችም መኖር አስቸጋሪ ሆኖባቸዋልበዚህ የተነሳም ስደተኞቹ ምንም እንኳን በቀደመው አሰራር ናይሮቢ መቆየት የሚያስችል ፈቃድ ቢኖራቸውም ከዛሬ ነገ እንያዛለን በሚል ስጋትና ፍርሃት ውስጥ ይገኛሉ ። ችግራቸውንም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ለሚሏቸው አካላት ለማሳወቅ እየሞከሩ ነው ።ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች አንዱ የሆነውየተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን «ዩኤንኤችሲአር» ስደተኞቹ ለሚገኙበት ሁኔታ ምን መላ እየፈለገ እንደሆነ ከዶቼቬለ ቬለ ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው መልስ ችግሩ መኖሩን እንደሚያውቅ ለመፍትሄውም የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል ።በኬንያ የ«ዩኤንኤችሲአር» ቃል አቀባይ ኢማኑዌል ኔባራ«ይህ እኛን የሚያሳስበን ጉዳይ ነው።

Kenia Kakuma Flüchtlingslager
ምስል dapd

አንዳንድ ስደተኞች በየከተሞች አካባቢ ከህበረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንደሚኖሩ እናውቃለን ።አንዳንዶቹም እዚያ ተመዝግበው ልጆቻቸውም ትምህርት ቤት ይሄዳሉ ። እስካሁን ኑሮአቸውን በተረጋጋ ሁኔታ ይመሩ ነበር አሁን ግን ህይወታቸው ተናግቷል ።ስለዚህ እኛ በዚህ ጉዳይ ላይ የስደተኞችም ፍላጎት ከግምት ውስጥ እንዲገባ ከመንግሥት ጋር አዘውትረን በመምከር ላይ ነን ።»«ዩኤንኤችሲአር» ችግሩን ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ቢያሳውቅም ስደተኞቹ አሁንም ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ነው የሚናገሩት ።

የ«ዩኤንኤችሲአር» ቃል አቀባይ ኔቤራ ችግሮች የሚያጋጥማቸው መስሪያ ቤታቸው እውቅና የሰጣቸው ስደተኞች የደረሰባቸውን በደል ለ«ዩኤንኤችሲአር» ማመልከት እንደሚኖርባቸውም ተናግረዋል

«ወደ ኛ ቢሮ መምጣት የሚችሉ ወደ ቢሮአችን መምጣት አለባቸው ። የደረሰባቸውን ማንኛውንም በደል ማመልከት አለባቸው ። በየፖሊስ ጣቢያውም ሆነ በየስታድዮሙ የስደተኞች መብትሲጣስ ጣልቃ ገብተው ጉዳዩን የሚያነሱ ባልደረቦች አሉን ። ወረቀት ካላቸው መታወቂያ ካላቸው የኛን ባልደረቦች ማግኘት አለባቸው ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ