1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃውያን ስደተኞች በስፓኝ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2007

በሜዲቴራንያን ባህር በኩል ወደ ኢጣሊያ ለመግባት በሚያደርጉት ሙከራ በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ስደተኞች ህይወት ያልፋል ። አፍሪቃውያኑ በባህር የሚሰደዱት ወደ ኢጣልያ ብቻ ሳይሆን ስፓኝን ወደ መሳሰሉ ሌሎች የደቡብ አውሮፓ ሃገራትም ጭምር ነው ።

https://p.dw.com/p/1FGn6
Melilla Zaun Flüchtlinge 28.05.2014
ምስል picture-alliance/dpa

ከአንድ ሳምንት በፊት በሊቢያ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ሜዴትራንያን ባህር ውስጥ የደረሰው የስደተኞች እልቂት እዚህ አውሮፓ አሁንም መነጋገሩ ቀጥሏል ። እነዚህ ቁጥራቸው ከ800 በላይ የተገመተ ስደተኞች ህይወታቸው ያለፈው ወደ ኢጣልያ በማቅናት ላይ ሳሉ ነበር ። ስደተኞች በብዛት የሚጎርፉባት አውሮፓዊት ሃገር ኢጣልያ ብቻ አይደለችም ።ለሰሜን አፍሪቃ የምትቀርበው ስፓኝም በርካታ አፍሪቃውያን የሚሰደዱባት ሃገር ናት።
ወደ ስፓኝ የተጓዘው የዶቼቬለው ጋይ ሄደጌኮ እንደዘገበው በጎርጎሮሳውያኑ 2014 ፣ 20 ሺህ የሚደርሱ አፍሪቃውያን ከሞሮኮ ተነስተው ሰሜን አፍሪቃ የባህር ዳርቻ ወደሚገኙት ሴዉታና ሜሊላ ወደ ተባሉት የስፓኞቹ የወደብ ከተሞች ገብተዋል ። አልጀሲራስ ደቡባዊ ስፓኝ ጫፍ አቅራቢያ የምትገኝ የወደብ ከተማ ናት ። ከዚህ ስፍራ ሆነው ከሜዲቴራንያን ባሻገር በስተደቡብ ሲመለከቱ በጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ የሰሜን አፍሪቃ የባህር ዳርቻ ይገኛል ። በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ከሰሜን አፍሪቃ የባህር ጠረፍ ተነስተው ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት ወደ ስፓኝ ይገባሉ ። ብዙዎቹ ስፓኝ የሚሄዱት የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው ።ስደተኞቹ ስፓኝ የሚደርሱት በተለያየ መንገድ ነው ። አንዳንዶቹ ዋናው የስፓኝ ምድር የሚገቡት በትናንሽ ጀልባዎች ነው ።ሌሎች ደግሞ በሞሮኮ የባህር ዳርቻ አድርገው የስፓኝ ግዛት ወደ ሆኑት ወደ ሰሜን አፍሪቃዎቹ የወደብ ከተሞች ሴዉታና ሜሊላ ይደርሳሉ ።አንዳንዶች ደግሞ በመኪና ተደብቀው ድንበር ድረስ ይመጣሉ ወይም ደግሞ ሞሮኮን ከስፓኞቹ የወደብ ከተሞች ከሴዉታና ከሜሊላ የሚለየውን 6 ሜትር ርዝመት ያለውን አጥር ዘለው ለመግባት ይሞክራሉ ።ስደተኞቹ እነዚህ ከተሞች ከገቡ አውሮፓ እንደደረሱ ነው የሚቆጠረው ።
ሴዉታ ከሚገኙ የቀይ መስቀል ሠራተኞች ዋነኛ ተግባራት አንዱ ለአፍሪቃውያን ስደተኞች የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ ማድረግ ነው ። በከተማይቱ የቀይ መስቀል ተወካይ ጀርሚናል ካስቲሎ አፍሪቃውያኑ የሚሰደዱት ያለ ምክንያት አይደለም ይላሉ።
«በርካታ ስደተኞች ከጀልባዎች እንደወረዱ መሬት ይስማሉ ። ምክንያቱም ምናልባት ለሞት የሚዳርጉ ሁኔታዎችን በቅርብ አይተው ይሆናል ። እያንዳንዱ ፊት ላይ ተስፋ መቁረጥ ይታያል ። አንዳቸውም ቢሆኑ ያለ አንዳች ምክንያት በትናንሽ ጀልባዎች ወይም ደግሞ በመኪናዎች ውስጥ ተደብቀው አይመጡም ። የተሻለ ህይወት ይፈልጋሉ ። እነርሱም እንደኛ መኖር ይፈልጋሉ ።»
ካስቲሎ እንደሚሉት በአውሮፓ ሃገራት ህገ ወጡ ስደት እየተጠናከረ የሄደው በቅርብ ዓመታት ባጋጠመው የኤኮኖሚ ውድቀት መንስኤ የአውሮፓ ሃገራት ለዓለም ዓቀፍ የትብብር መርሃ ግብሮች የሚመድቡት በጀት እያነሰ በመሄዱ ምክንያት ነው ።ስፓኝ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሃገርዋ የሚገቡ ስደተኞችን ለመከላከል የምትጥር መሆኑን የተናገሩት ካስቲሎ ሆኖም ስደተኞች እንዳይመጡ ማስቆም እንደማይቻል ነው የሚያስረዱት ።
«ስለ ስደተኞች ማዕበል ስንነጋገር እንሳሳታለን ።በድንበሩ አጥር ላይ ስለሚደርሰው ጥቃትም ስንነጋገር እንሳሳታለን ። የቋንቋ አጠቃቀማችን የተዛባ ነው ። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ወደ ዚህ የሚመጡትን ሰዎች እንደ ሰው ልጅ እንዳናያቸው ያደርገናል ።ስደት ስለሚያስከትለው ችግር እንናገራለን ። ይሁንና የሰው ልጅ ከአንድ ቦታ የተሻለ ወደ ሚለው ሌላ ቦታ መሰደዱ ያለ ነው ።ለኛ ፍልሰት ችግር ሳይሆን ሁሌም ያለ እውነታ ነው ።»
ከሴዉታ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ የስደተኞች ጊዜያዊ ማቆያ ይገኛል ።ሴዉታ የሚደርሱ ስደተኞች በሙሉ ወደ ዚህ ስፍራ ነው የሚወሰዱት ። ቀጥሎ የሚወሰዱበት ቦታ እስኪወሰንላቸው ድረስ በመጠለያው ምግብና ልብስ እንዲሁም የመኝታ ስፍራ ይሰጣቸዋል ። ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ ወደ ዋነኛው የስፓኝ ምድር ይሸጋገራሉ ።አቡበከር ባባ በቅርቡ ከሞሮኮ በጀልባ ሴዉታ የገባ ስደተኛ ነው ።
«ከጊኒ ኮናክሪ ነው የመጣሁት ። ህይወቴን በጣም ጥሩ ና ቀላል በሆነ መንገድ ለመምራት እዚህ የመጣሁት ። እድሜዬ 18 ነው ። እዚህ እንድገባ እግዚአብሔር ረድቶኛል ። በጣም ደስተኛ ነኝ »
ከጊኒኮናክሪ መምጣቱን የሚናገረው ሌላው ስደተኛ ሞሀመድ ሲሶኮ ደግሞ ሴዉታ በጀልባ ከመምጣቱ በፊት አፍሪቃ ውስጥ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ተጉዟል ።
«የተነሳሁት ከኮናክሪ ማሊ ነው ከማሊ ሞሪቴንያ ከሞሪቴንያ ሞሮኮ ገባሁ ።ሞሮኮ ከደረስኩ በኋላ ዞድያክ በተባለችው ጀልባ ከ9 ሰዓት ጉዞ በኋላ ሴዉታ ገባሁ ።»
የሞሀመድ ወላጆች በጎሳ ግጭት ተገድለዋል ።ያቋረጠውን ትምህርቱን አንድ ቀን እንደሚቀጥል ተስፋ ያደርጋል ። በስደተኞች ማቆያው ስፍራ 5 ወራት ያሳለፈው መሃመድ መቼ ወደ ዋናዋ ስፓኝ ምድር እንደሚወሰድ አያውቅም ።»
በስደተኞች መጠለያ ህይወት ቀላል ባይሆንም የሚገኝበትን ሁኔታ ተቀብሎ ህይወቱን እንደምንም እየገፋ መሆኑን መሀመድ ይናገራል ።
ኤል ታራጃል ሴዉታና ሞሮኮ ድንበር መሃል የምትገኝ ስፍራ ናት ።በዚህ ቦታ የዛሬ ዓመት በጥር ወር መጨረሻ ግድም በዋና ሴዉታ ለመድረስ ከሞከሩ ስደተኞች ቢያንስ የ13ቱ ህይወት ማለፉ እስካሁን በአሳዛኝነቱ የሚነሳ ጉዳይ ነው ።ስደተኞቹ የሞቱት በድንበር ጠባቂዎች የፕላስቲክ ጥይቶች ና አስለቃሽ ጢስ ሲተኮስባቸው ተደናግጠው በመስጠማቸው መሆኑ ነው የሚነገረው ። የሲቪል ድንበር ጠባቂዎች የወሰዱት ይህ እርምጃ እስካሁን ይወገዛል ።በህይወት ከተረፉት አንድ ስደተኛ ድንበር ጠባቂዎቹ በስደተኞቹና ባጠለቁት መንሳፈፊያ ላይ አነጣጥረው መተኮሳቸውን ለስፓኝ ጋዜጣ አስታውቋል ።ይኽው ቻልርስ የተባለው ስደተኛ ሰዎቹን የገደሉት የሲቪል ዘቦቹ ናቸው ይላል ። በእርምጃው ተጠያቂ የተባሉ የ16 ዘቦችን ጉዳይ አንድ ዳኛ እያጣሩ ናቸው ። ጁዋና አንቶንዮ ዴልጋዶ የድንበር ጠባቂዎቹ የሠራተኛ ማህበር ቃል አቀባይ ናቸው ። በርሳቸው አስተያየት ድንበር ጠባቂዎች ይህን መሰሉን ድርጊት የሚፈፅሙት ከበላዮቻቸው ከፍተኛ ጫና ስለሚደርግባቸው ነው ።
«እውነቱን ለመናገር ዘቦቹ የፈጸሙት ዘግናኝ ስህተት ነው ። እጅግ ከፍተኛ ጫና ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው የምንሰራው ። ጫናው አስከፊ ነው ። ዋና ከተማይቱ ማድሪድ ያሉት ባለሥልጣናት በእዝ ሰንሰለቱ ጠንካራ ግፊት ያደርጋሉ ። ታች ያለው ሰው እጅግ ከፍተኛ ለሆነ ጫና ይዳረጋል ። ምክንያቱም ከርሱ በላይ ያሉት አንድ ስደተኛ እንዲገባ አይፈልጉም ።»
ዴልጋዶ እንደሚሉት ሴዉታ ያሉት የሲቪል ዘቦች አቅም አነስተኛ ነው ። የአውሮፓ ህብረትም ይህን ችግር ለረዥም ጊዜ ሰምቶ እንዳልሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎታል ።
«ሁለት ክፍለ ዓለማት አሉ አንዱ ድሃ ሌላኛው ባለፀጋ ናቸው ። አንደኛው የተሻለ ዓለም ፍለጋ ላይ ያሉ በርካታ በማንኛውም ዓለም እንደሚገኝ ሰው ያሉ ጥሩ የሚባሉ ሰዎች አሉት ።ሆኖም የአውሮፓ ህብረት ለዚህ ጉዳይ ደንታም የለውም ። ምክንያቱም አውሮፓ የስደትና ስደተኞች ችግር ስፓኝን ወይም ኢጣልያን ብቻ የሚመለከት አድርጎ ነው የሚያስበው ። ይሁንና ችግሩ በሁሉም ዘንድ መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባ ነገር ነው ።»
በስፓኝዋ ደሴት ሴዉታ በርካታ አፍሪቃውያን ስደተኞች ላይ ታች ሲሉ ይታያል ። እነዚህ እንደ እድል ሆኖ በሰላም የደረሱ ሰዎች ናቸው ።ሆኖም ባለፈው ዓመት በኤል ታራጃል እንደ ሞቱትና ከዚያም ቀደም ሲል በላምፔዱዛ አቅራቢያ በተደጋጋሚ ጊዜያት በቅርቡም በሊቢያ የባህር ዳርቻ እንዳለቁት ያሰቡበት ሳይደርሱ በየመንገዱ የውሃ ሲሳይ ሆነው የሚቀሩ በርካቶች ናቸው ። ይህ መሰሉን እልቂት ማስቆም በሚቻልበት መንገድ ላይ የመከሩት የአውሮፓ መንግስታት ባለፈው ሳምንት ባካሄዱት አስቸኳይ ስብሰባ መፍትሄ ያሏቸውን የድርጊት መርሃ ግብሮች ቀርፀዋል ። ከመካከላቸው በባህር ላይ ሰዎች እንዳያልቁ የነፍስ አድኑን ተግባር ማጠናከር ፣ ስደተኞችን በባህር የሚልኩ ደላሎችን ተከታትሎ መያዝ ጀልባዎቻቸውንም ማውደም የሚሉት ይገኙበታል ። ምንም እንኳን እነዚህ እቅዶች ችግሩን ለማቃለል እገዛ ማድረጋቸው የሚታመን ቢሆንም ካለፈው ልምድ እንደታየው በዘላቂነት ተግባራዊ መሆናቸው ግን ማጠያየቁ አልቀረም ። ብዙዎች እንደሚስማሙት ጦርነት የመብት ጥሰትና የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ካሉባቸውየአፍሪቃ ሃገራት በአደገኛ ጉዞ ወደ አውሮፓ የሚደረግ ስደት እንዲህ በቀላሉ የሚገታ አይመስልም ። መፍትሄው ችግሩን ከምንጩ ማድረቁ ነው የሚሉም ብዙዎች ናቸው ።ሰሞኑን ከህገ ወጥ ስደት ዋነኛ ተጠቃሚ በሆኑ ደላሎች ላይ ኢጣልያን በመሳሰሉ ሃገራት የተጀመረው ዘመቻ ተዘናክሮ ቀጥሏል ። ከየአቅጣጫው ልዩ ልዩ መፍትሄዎች በሚሰነዘሩበትና ችግሩን ለማቃለል እርምጃዎችም መወሰድ በጀመሩበት በዚህ ወቅት ላይ ስደተኞች በአደገኛ የባህር ወደ አውሮፓ መሰደዳቸው ቀጥሏል ።

Spanien Ansturm auf Grenze von spanischer Exklave Melilla
ምስል picture-alliance/AP
Spanien Enklave Flüchtlinge werden von versorgt
ምስል DW/G. Hedgecoe
Flüchtlinge in Melilla
ምስል Reuters
Flüchtlinge in Melilla 28.02.2014
ምስል picture-alliance/dpa

ጋይ ሄደጌኮ /ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ