1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አነጋጋሪዉ የስም አወጣጥ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 21 2006

« በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያዊ ሕጻናት ስሞችን ስንመለከት በአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ይዘት እንደሌላቸዉ እንረዳለን፤ አብዛኞች ስሞች ቅላጼያቸዉ ለጆሮ እንዲጥሙ እንጂ ፤ ታሪኩ ምን ማለት ነዉ ብለን ጠይቀን ለልጆቻችን ስም ስንሰጥ አንታይም። ይህ ደግሞ የባህል ወረራ እንዳያመጣብን እሰጋለሁ»

https://p.dw.com/p/1A9eT
ምስል UNO

ያሉን በቅርቡ የስም ነገር በሚል ሰፋ ያለ ፅሁፍ ለአንባብያን ያቀረቡት ጦማሪ ኤፍሪም እሸቴ ናቸዉ። ከቅርብ ግዜ ወዲህ የመጠርያ ስሞች ለአፍ እንዲጥሙ አልያም ዘመናዊ ቅላፄን እንዲይዙ መሰጠታቸዉ፤ ስያሜዎቹ ግን ኢትዮጵያዊነትን ያልተላበሱ መሆናቸዉ ብዙዎችን ሲያነጋግር ይታያል።

የጥንት የኢትዮጵያውያንን ስም አወጣጥ ስንመለከት ሃይማኖት ትልቅ ድርሻ እንደነበረው የታሪክን ሀሁ የሚያውቅ ማንም ሰው ሊገነዘበው ይችላል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በሃይማኖት የመጣላትን ሁሉ በጅምላ አልተጫነችም። ከእስልምናውም ይሁን ከክርስትናው ዓለም ያገኘችውን በራሷ መለክያ “ኢትዮጵያዊ” አድርጋ፣ አገርኛ ጸጋ አላብሳ፣ የራሷን አሻራ ትታ፣ አገራዊውን ባህል መንግላ ሳትጥል አስማምታ ነው፤ ሲሉ በስያሜ ላይ ሰፋ ያለ ጽሁፋቸዉን አደባባይ በተሰኘዉ ድረ-ገጻቸዉ ያስነበቡት ጦማሪ ኤፍሪም እሸቴ ለዚህ ጽሁፋቸዉ ያነሳሳቸዉን ነገር፤ ገልጸዉልናል።

Argobba - Tollaha Dorf
ምስል DW

ደራሲና ጋዜጠኛ ታደለ ገድሌም የጦማሪ ኤፍሪም እሸቴን ሃሳብ ይጋራሉ፤ ደራሲ ታደለ እንደሚሉት አንድ ሕጻን ሲወለድ ታሪካዊና ቤተሰባዊ ሁኔታን ለማስታወስ ስም ይሰጠዋል። ነገር ግን አሁን አሁን ለህጻናት የሚሰጠዉም ሆነ የድርጅቶች መጠርያ አዉሮጳዊ ብቻ ሳይሆኑ፤ አንዳንዶቹ ብዙ እንግሊዘኛ ወይም ሌላ የአዉሮጳ ቋንቋ ተናጋሪ በሌለበት በኢትዮጵያ የአዉሬ ስም ሁሉ የሚመስል ስም ሆኖ ይታያል። በዩናይትድ ስቴትስ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኤፍሪም እንደሚሉት አሜሪካም ብትሆን የራስዋ የሆነ የስም አጠራር ያላት የምትገርም ሀገር ናት። የአሰያየም የቆየ ባህላችን ኢትዮጵያዊነትን ጠብቆ ከአባት ከናቶቻችን እንደተቀበልን ሁሉ፤ በኛ ዘመን ከሥሩ ተነቅሎ ሳይጠፋ ለትዉልድ ተሻግሮ እንዲደርስ፤ ኢትዮጵያዊ ባህላችንን መርሳት የለብንም ያሉንን፤ ጦማሪ ኤፍሪም እሸቴን እና ደራሲና ጋዜጠኛ ታደለ ገድሌን እናመሰግናለን። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ዘገባ መስምያዉን በመጫን ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ