1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዉሞ ሠልፍ፤ ድብደባና እስራት በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 2 2007

አሳካሪ-እና ግልፅ ያልሆነ ፖለቲካ።ለአዲስ አበባ በርግጥ እንግዳ አይደለም።ጥንት እንደ ቅዳሜዉ ነበረች።የዛሬ አርባ አመት የጥንት ሥርዓቷ መለወጡ በታወጀ፤ ያለምንም ደም የኢትዮጵያ እንከን እንዲወድም በተዘመረባት ማግስትም በደም ኩሬ ተነከረች።በ1983 ያቺ ጉደኛ ከተማ የሠላም፤ ዲሞክራሲን ጉዞ መጀመሯ ተነግሮባት ሳያበቃ በሌላ ደም ጨቀየች።

https://p.dw.com/p/1E15o
ምስል picture alliance/landov

አዲስ አበባ እንደገና ሠላማዊ ሠልፍ በሐይል ተበተነ ወይም ታገደባት።ለሠላማዊ ሠልፍ አደባባይ የወጡ ሠላማዊ ነዋሪዎችዋ፤ ሠላማዊ ነዋሪዎችዋን ለሰላማዊ ሠልፍ የጠሩ የሠላማዊ ትግል አቀንቃኝ ፖለቲከኞችዋ በፖሊስ ቆመጥ ተቀጠቀጡ፤ተፈነከቱ፤ተሰባበሩባትም።የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር-አቶ ስለሺ ፈይሳ። መቶዎች ታሠፈሱ-ታሰሩባትም።አዲስ አበባ፤የአፍሪቃ መዲና።የቅዳሜዉን ክስተት አስታከን የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ እዉነት ላፍታ እንቃኛለን።

ዶክተር ደመቀ አጪሶ የፖለቲካ ሳይንስ አጥኚ።አሳካሪ-እና ግልፅ ያልሆነ ፖለቲካ።ለአዲስ አበባ በርግጥ እንግዳ አይደለም።ጥንት እንደ ቅዳሜዉ ነበረች።የዛሬ አርባ አመት የጥንት ሥርዓቷ መለወጡ በታወጀ፤ «ያለምንም ደም የኢትዮጵያ እንከን እንዲወድም » በተዘመረባት ማግስትም በደም ኩሬ ተነከረች።በ1983 ያቺ ጉደኛ ከተማ ድፍን ኢትዮጵያን ይዛ የ17 ዓመቱን የደም ኩሬ መሻገሯ፤የሠላም፤ የዲሞክራሲ ጉዞ መጀመሯ ተነግሮባት ሳያበቃ በሌላ ደም ጨቀየች።1997 ነፃ ምርጫ አስተናገደች።ወዲያዉ ግን አስከሬን ይለቀም፤ ቁስል ይጠቀለል፤ እስረኛ ይታፈስባት ገባ።ሐቻምና አምናም ብዙ የተለየ ታሪክ የላትም።ቅዳሜ ተደገመባት።ሮብ-በርሊን።የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፅሕፈት ቤታቸዉ ዉስጥ የኢትዮጵያዉን ጠቅላይ ሚንስትር ሐይለ ማርያም ደሳለኝን ሲያነጋግሩ ፅሕፈት ቤቱ አጠገብ ተሰልፈዉ የነበሩት ኢትዮጵያዉያን የጮኹ፤ የፈከሩለት፤የተናገሩ ያወገዙበት ጉዳይ በርግጥ አዲስ አይደለም።

ከኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እስከ ሐይማኖት መሪዎች፤ ከተራዉ ኢትዮጵያዊ እስከ ኢትዮጵያዉን፤ አንዳንዴም የዉጪ ጋዜጠኞችና ምሑራን፤ ከዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች እስከ መያዶች ለተከታታይ ዓመታት የታገሉ፤ የጮኹ፤ የዘገቡ፤የተቹ፤ የመከሩ፤ ያሳሰቡበት ጉዳይ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያክብር፤ መብቶቹን እንዲያከብር ምዕራባዉያን መንግስታት ግፊት ያድርጉበት የሚል።

Demonstration der Semayawi-Partei in Addis Ababa Äthiopien 22.09.2013
ምስል DW

ሰሚ እንጂ አድማጭ ያጣ ጩኽት፤ ግን የማያቋርጥ ደማቅ ጩኸት።የበርሊን ሰልፈኞችም የማያቋርጠዉን ጩኽት ጮሁ።ሮብ።ወይዘሮ እንጌላ ሜርክል የመብት ትግል፤ ጥያቄ ጩኸቱን ተደጋጋሚነት፤ ሰሚ እንጂ አድማጭ ያጣበትን ምክንያት፤ የማያቋርጥነቱን ከአቶ ሐይለማርያም፤ ከበርሊን ሠልፈኞች ወይም ከኢትዮጵያዉያንና የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚከታተሉ ወገኖች እኩል ምናልባትም አቶ ሐይለማርምን ከመጋበዛቸዉ ከብዙ ዓመታት በፊት ያዉቁታል።

አቶ ሐይለ ማርያምን በርሊን ድረስ የጋበዙት የሚያዉቁትን ለማሳወቅ እንዳልሆነ ማወቁ በርግጥ የሌላዉ ፋንታ ነዉ።ይሁንና ሜርክል «ብዙዎች ብዙ ጊዜ የሚሉ ወይም የሚፈልጉትን በል፤ ግን አንተንና ወገኖችሕን የሚጠቅመዉን አድርግ» አይነት ፖለቲካዊ መርሕን በሚያቀነቅነዉ የምዕራባዉያን ፖለቲካዊ-ዲፕሎማሲያዊ ሥልት ባይካኑ ኖሩ የአዉሮጳን የምጣኔ-ሐብት መዘዉር ሐገርን ለዘጠኝ ዓመት ቀርቶ ለዘጠኝ ቀን መምራት ባልቻሉ ነበር።

ሥለ ኢትዮጵያም ብዙዎች የሚሉ-የሚፈልጉትን እንደሚያዉቁ፤ አሳዉቀዉ-የሚፈልጉትንአደረጉ። «ፖለቲካዊ ግንኙነቶቻችን በጣም ጥልቅና ጥብቅ ናቸዉ።ሐሳብን በነፃነት (የመግለፅ መብትን)ና ሥለ መያዶች ሥራም ተነጋግረናል።ባጠቃላይ ግን አግባቢ የሐሳብ ልዉዉጥ ነዉ ያደረግነዉ-ማለት ይቻላል።»

አቶ ሐይለማርያ ሁሌም እንደሚያደርጉት በርሊን ድረስ የተከተላቸዉን ተቃዉሞ፤ ጥያቄና ጩኸት ማድመጥ አይደለም መስማት እንኳን አልፈለጉም።የሜርክል የግድምድሞሽ ጥቆማም «ካንገት እንጂ ካንጀት» እንዳልሆነ መረዳቱ አላቃተቸዉም።እና ተቃዉሞ ጩኸቱም፤ ተዘዋዋሪ-ጥያቄ ጥቆማዉም የሌለ ያክል ሐገራቸዉ አስተማማኝ ሠላም እና መረጋጋት የሠፈነባት መሆኗን አስታወቁ።

«ዛሬ እዚሕ የመጣሁት ተጨማሪ የጀርመን ኩባንዮች ወደ ሐገሬ እንዲመጡና ወረታቸዉን ሥራ ላይ እንዲያዉሉ ለመጋበዝ ነዉ።ምክንያቱም የጀርመን ኩባንዮች ሐገሬ ዉስጥ እንዲሰሩ የሚረዱ ምቹ ሁኔታዎች አሉ።ኢትዮጵያ በጣም የተረጋጋች፤ ሠላማዊና የጀርመን ባለሐብቶች ከኛ ጋር ለመስራት የሚችሉባት ሐገር ናት።»

ጠቅላይ ሚንስትሩ በርሊን ላይ ኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት የሠፈነባት መሆኗን ደጋግመዉ ሲናገሩ እዚያዉ አዲስ አበባ ዉስጥ የመንግሥታቸዉና የተቃዋሚዎቹ ፖለቲከኞች በሠላማዊ ሠልፍ ማድረግ እና መከልከል ሰበብ ይወዛገቡ ነበር።

Äthiopischer Ministerpräsident Hailemariam Desalegn zum Staatsbesuch in Deutschland
ምስል DW/Ludger Schadomsky

ግጥምጥሞሹ።

የኮሚንስቱ ርዕዮተ-ዓለም የማረካቸዉ ኢትዮጵያዉያን ተማሪዎች ዘዉዳዊዉን ሥርዓት ለመቃወም አንድ ሁለት በሚሉበት ዘመን የኢትዮጵያዉ ንጉሠ ነገሥት አፄ ሐይለ ሥላሴ ቦንን ጎብኝተዉ ነበር።«እኛ የኮሚንስት ሥጋት የለብንም።» አሉ (1954 እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር።) አፄ ሐይለ ሥላሴ የለም ያሉትን ኮሚንስታዊ ርዕዮተ-ዓለም የሚያቀነቅኑ ኢትዮጵያዉያን ጎራ ለይተዉ የሚጋደሉበት ዘመን አብቅቶ ወይም ማብቃቱ ተነግሮ በ1997 በአንፃራዊ መመዘኛ የመጀመሪያዉ ነፃ ምርጫ በተደረገ ማግሥት ዉጤቱ በቀሰቀሰዉ ግጭት፤ ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ ዉስጥ ሰዉ በሚገደል፤በሚታሰርባት መሐል የያኔዉ የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለሥ ዜናዊ ወደ ቦን መጥተዉ ነበር።ጥቅምት ማብቂያ 1998።«በእነዚሕ ሥራ አጥ ወጣቶች አምስት የእጅ ቦምቦች ፖሊስ ላይ ተጥለዉ የተወሰኑ ፖሊሶች ተገድለዋል፤ ቆስለዋልም።ሁለት ጠመንጃዎች ከፖሊስ ተቀምተዉ ነበር።አንዱን ሐሙስ አገኘነዉ።ሐሙስ ነገሮች ተረጋግተዋል።በመሐሉ ግን ብዙ ኢትዮጵያዉን ሞተዋል።ሞቱ ያሳዝነኛል ግን የተለመደዉ አይነት ሠልፍ አልነበረም።»

በዚያ ግጭት መንግሥት እንዳመነዉ-197 ሰዎች ተገድለዋል።የሟች-ቁስለኛዉን ትክክለኛ ቁጥር በርግጥ ቤቱ ነዉ የሚያዉቀዉ።ሺዎች ታስረዋል።ከዚያ በኋላም የኦሮሞ ተማሪዎች ተቃዉሞ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብሰባና ሰልፍ የሙስሊሞች ጥያቄ በተነሳ ቁጥር ሰዎች በጅምላ መደብደብ፤መታፈስ መታሰራቸዉ የአዲስ አበባ ፈሊጥ ሆኗል።

አዲስ አበባን የዉዝግብ፤ ግጭት ማዕከል ያደረገዉ የኢትዮጵያን ፖለቲካን «የተሳከረ» የሚሉት የፖለቲካ አዋቂ ዶክተር ደመቀ አጪሶ ለመሳከሩ ከገዢዉ ፓርቲ እኩል ተቃዋሚዎችንም ይወቅሳሉ።ጥሩዉ ግን አልሆነም።በመጪዉ ግንቦት ሊደረግ ለታቀደዉ ምርጫ የጋር ትብብር የመሠረቱት የዘጠኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብርና የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ሮብ የገለፁት ዉዝግብ አጉዞ አጉዞ በቅዳሜዉ ድብደበና እስራት አሳረገ።በድብደባ-እስራቱ መሐል ሌላም ነገር ተፈፅሞ ነበር።

Karte Äthiopien englisch

የሠማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ እንደሚሉት ፖሊስ እና የሥለላ ባልደረቦች የዘጠኙን ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እና አባላትን ማሰር-ማስፈራራት የተጀመሩት ከቅዳሜ በፊት ነዉ።ቢያንስ አምስት የሠማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት ከሳምንት በፊት ታስረዋል።ለሠላማዊ ሠልፍ የሚደረገዉ ዝግጅት ግን አልተቋረጠም ነበር።

የዘጠኙ ፓርቲዎች ማስተባባሪያ ወይም የሠማዊ ፓርቲ ፅሕፈት ቤቱን ሁኔታ ደግሞ አቶ ስለሺ እንዲሕ ይገልጹታል።የታሰሩትም ሆነ የተደበደቡት ሰዎች ትትክክለኛ ቁጥር አይታወቅም።የጉዳቱ መጠንም እንዲሑ።የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ የፌደራል ፖሊስ፤ የኮሚኒኬሽን ጉዳይ ፅሕፈት ቤት ባለሥልጣናትን በሥልክ ለማነጋገር ያደረግነዉ ሙከራም አልተሳካልንም።

የታሰሩት ግን አቶ ሥለሺ እንደሚሉት በየሥፍራዉ ተከፋፍለዉ ነዉ።በዶክተር ደመቀ አገላለፅ «አሳካሪዉ» የኢትዮጵያ ፖለቲካ እስከመቼ እንዳሳከረ ይቀጥላል ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ