የተፈናቃዮች ቅሬታ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 10 2016ባለፈው ሳምንት እሁድና ሰኞ በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በነበረ ግጭት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች እርዳታ እንዳላገኙና ህፃናትንና እናቶችን ጨምሮ በየዛፉ ስር መቀመጣቸውን ነው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬሌ የተናገሩ ተፈናቃዮች የገለፁት፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ ፈለጉ አንድ አስተያየት ሰጪ የሚከተለውን ብለዋል፡፡
“...ህዝብ በሙሉ መኮድ የሚባለውን መንደር ለቅቆ ማለት ነው፣ ማሮልና ባዜል ወደሚባል ቦታ ነው ያለው፣ ህፃናት በዛፍ ስር ነው ያሉት፣ ከብቶቻቸውም ተዘርፈዋል፣ ተፈናቃዮቹ ወደ 10 ሺህ ይደርሳሉ፣ ምንም እርዳታ አልቀረበም፣ መንግስት እስካሁን ምላሽ አልሰጠም፣ ከእሁድ እለት ጀምሮ የተደረገ ድጋፍ ምንም የለም፣ አሁን ግጭቱ ቆሟል፣ አንፃራዊ ሰላም በአካባቢው ይታያል፡፡” ነው ያሉት፡፡
ሌላ አስተያየትሰጪ ደግሞ ተፈናቃዮቹ ዘመድ ከሚሰጣቸው የእለት ምግብ ውጪ የደረሰላቸው አካል የለም ብለዋል፡፡
አንድ የኢታንግ ወረዳ ነዋሪም ለተፈናቃዮቹ አስቸኳይ እርዳታ ባለመቅረቡ በችግር ላይ እንደሆኑ ጠቁመዋል፣ መንግስት ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ አልሰተም ሲሉም ወቅሰዋል፡፡
“... እስካሁን እርዳታ አልደረሰላቸውም፣ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ እርደታ እየፈላለግን ነው ቢሉም እስካሁን የመጣ ነገር የለም፣ መንግስት ጥረት እያደረገ አይደለም፡፡” ሲሉ ከስሰዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋድቤል ሙን በነበረው ግጭት ከ11ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንና በሶስት የተለያዩ አካባቢዎች እንደሰፈሩ አመልክተዋል፣ ሁኔታውም ከባድ እንደሆነ ነው ስረዱት፡፡
“11 ሺህ 370 ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ ተፈናቃዮቹም ዶሮንግ፣ ባዜልና ኢታንግ ኪር በሚባሉ አካባቢዎች ተጠልለዋል፣ ሁኔታው ከባድ ነው፣ዝናብ ሲጥል ይቸገራሉ፣ ባገኘነው መረጃ መሰረት በቅርብ እርዳታ እንዲደርሳቸው ይደረጋል፡፡” ብለዋል፡፡
የጉዳቱን መጠን የሚያሳይ ሪፖርት እንደደረሳቸው ጠቁመው ያን መሰረት በማድረግ እርዳታ እንዲቀርብላቸው ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በፊትም በጋምቤላ ክልል በጆር ወረዳ በነበረ ግጭት በተመሳሳይ በርካቶች መፈናቀላቸውንና የእለት ድጋፍ ሲጠይቁ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር