1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትንሳኤ በዓል አከባበር እና ድባቡ

እሑድ፣ ሚያዝያ 27 2016

የዚህ ዓመት የትንሳኤ በዓል ኢትዮጵያ ዜጎቿ ከአቅም በላይ እየናረ ኑሮን በሚፈታተን ገበያ እና ግብይት እየተቸገሩ ባሉበት፣ ሰላም ደፍርሶ በትጥቅ የታገዘ ደም አፋሳሽ ግጭት በተለይ አማራ እና ኦሮሚያ በሰፈነበት አውድ ውስጥ የተከበረ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/4fWKZ
መስቀል የያዙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቄስ
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮችን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ዛሬ የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሳኤ በዓል አክብረዋል።ምስል Sergi Reboredo/picture alliance

የትንሳኤ በዓል አከባበር እና ድባቡ

ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ዛሬ የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሳኤ በዓል አክብረዋል።

የክርስትና እምነት መሠረት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከመቃብር የተነሳበት እለት የሚታሰብበት ይህ ክብረ በዓል ከረጅም ቀናት ፆም ፣ ስግደት እና መንፈሳዊ ሥና ሥርዓቶች በኋላ የሚከበር ነው።

የዚህ ዓመት የትንሳኤ በዓል ኢትዮጵያ ዜጎቿ ከአቅም በላይ እየናረ ኑሮን በሚፈታተን ገበያ እና ግብይት እየተቸገሩ ባሉበት፣ ሰላም ደፍርሶ በትጥቅ የታገዘ ደም አፋሳሽ ግጭት በተለይ አማራ እና ኦሮሚያ በሰፈነበት፣ ጥላቻ፣ መናናቅ፣ በጎሳ እና በሃይማኖት እኛ እና እነሱ የሚሉ ችግሮች ጎልተው በሚታዩበት አውድ ውስጥ የተከበረው ሆናል።

ገበያው እና ግብይቱም ቢሆን አንድም በዋጋ መናር ፣ በሌላም በኩል ያለው የሰላም መታጣት ባስከተለው ድባቴ ጣዕሙን ያጣ ሆኖ አልፏል።

የትንሳኤ በዓል ክርስትያኖች በጽኑ ፆም፣ በፀሎት፣ በሥግደት፣ በምህላ እና በተማጽኖ ከፈጣሪያቸው ጋር ለሁለት ወራት ግድም ሲያደርጉት የቆዩትን ትስስር አጠናቀው የኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሳት በማሰብ በተቻላቸው ሁሉ በደስታና በተድላ የሚያሳልፉት ነው። በዓሉ ከመንፈሳዊ ክዋኔው ባለፈም በመረዳዳት፣ በመተጋገዝ ፣ በመተሳሰብ፣ በመጠያየቅ በቤት ውስጥ የሚከበር ነው።

የበዓል መዳረሻ ወጎች ፣ ልማዶች እና ትዝታዎቻቸው

ኢትዮጵያ አሁን በአንድ በኩል የእርቅ፣ የፍትሕ፣ የተጠያቂነት፣ የብሔራዊ ምክክር ጉዳዮች ጎልተው የሚደመጡባት የመሆኗን ያህል በሌላኛው ማእዘን ደግሞ በሁለት የሀገሪቱ ትልልቅ ክልሎች የዜጎችን ኑሮ፣ ሕይወት የሚያጎሳቁልና የሚያውክ የትጥቅ ግጭት ያየለባት፤ "ተማረኩ፣ እጅ ሰጡ ፣ ተደመሰሱ ፣ እርምጃ ተወሰደባቸው" ከሚሉ የእርስ በርስ መገዳደል ገላጭ መግለጫዎች ያልተላቀቀች ሀገር በመሆኗ የበዓሉ ድባብ ከዚህ ስሜት የሚላቀቅ አይሆንም።

ዶሮ በኢትዮጵያ የበዓል ገበያ
የኑሮ ውድነት የኢትዮጵያውያንን የበዓል አከባበር የሚፈታተን ጉዳይ ከሆነ ውሎ አደረ።ምስል Million Hailesilasie/DW

ይህም በመሆኑ ነው የክርስትና እምነት መሪዎች በየፊናቸው ለሕዝብ የሰላም፣ የእርቅ፣ የመተሳሰብ ጥሪዎችን በእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸው ውስጥ ማካተታቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰላም በራቃት ኢትዮጵያ እንኳን ለ2016 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል "በሰላም" አደረሳችሁ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

"ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ እያለፈች ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያም ሆኖ "በፈተና ውስጥ የቆመች ሀገር ግን አይደለችም" ብለዋል። አጭር ነው ያሉት ምን እንደሆነ ያላብራሩት "የኢትዮጵያ ሕማማት" አጭር ቢሆንም "ከባድ ነው" ይህንን ለማለፍ የሚያስችል ኃይል ግን አላት በማለት ጽፈዋል።

ከዚያ በኋላ "ረዥሙ የኢትዮጵያ ትንሣኤ የሚመጣ ነው" ሲሉም የመንግሥትታቸውን መሻትና ፍላጎት ከበዓሉ ምንነት ጋር አስተሳስረው ባስተላለፉት መልእክት ገልፀዋል።

የትንሳኤ በዓል በሚከበርበት በዚህ ወቅት ዘመድ ከዘመዱ በተለይ በተሽከርካሪ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መጠያየቅ  አሥጊ ነው። ሰዎችን አግተው ቤዛ የሚጠይቁት መበራከት ለዚህ አንዱ ምክንያት ነው።

የትንሳኤ በዓል ዝግጅት በአማራ ክልል

ጦርነት የቤተሰቡን አባል ያልጎዳበት ኢትዮጵያዊ ምን ያህል ነው? የሚለውም የበዓሉብ አወንታዊም ይሁን አሉታዊ ስሜት የሚወስን ነው። ኢንተርኔት የሌላቸው ፣ መብት ገዳቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀባቸው፣ አዲስ መፈናቀል የተስተዋለባቸው፣ ደሞዝ ሊከፈላቸው ያልቻሉ መምህራን ችግር የተደመጠበት፣ በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ሌላ ትኩስ ችግር የተስተዋለበት ሁኔታ አሁንም አልቀረም።

በሀገሪቱ የጎሳ እና የሃይማኖት ማንነት የፈጠሯቸው ውጥረቶች የሉም ማለት አይቻልም። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለበዓሉ ባወጣው የመልካም ምኞት መግለጫ "እንደ ሀገር ላልተግባባንባቸው እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችን በመለየት መመካከርና መግባባት ላይ መድረስ፣ የተግባባንበትንም መተግበር ይኖርብናል" ያለው ለዚህ ይመስላል።

የኢትዮጵያ ሥጋ
የትንሳኤ በዓል በየ መንደሩ ሰውን የሚያስተሳስሩት እንደ ቅርጫ ያሉ የጋራ ማእድ ሥርዓቶችም የተለዩት አይደለም።ምስል Habtamu Yilma

አዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎችም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት በጎላ መልኩ አስተላልፈዋል።

የትንሳኤ በዓል በየ መንደሩ ሰውን የሚያስተሳስሩት እንደ ቅርጫ ያሉ የጋራ ማእድ ሥርዓቶችም የተለዩት አይደለም።

የትንሳኤ በዓል ዋዜማ በመቀሌ ደምቋል

በሌላ በኩል በየ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚኖሩ ተፈናቃይ ዜጎች የተለያዩ ወጣቶች ያደርጉት የነበረው የገንዘብ፣ የምግብ እና የቁሳቁስ ማሰባሰብ በጎ ሥራ አሁን ብዙም አልተስተዋለም። ይህንን ያድርጉ ከነበሩ ሰዎች መካከል በእሥር ላይ የሚገኙም ፣ ከሀገር የወጡም አሉ። በአንፃሩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በ መሰል ክብረ በዓላት ላይ "መአድ ማጋራት" በሚል የሚያደርጉት ግብዣ ቋሚ የመሆን አዝማሚያ እየታየበት የመጣ ይመስላል። ይህ በትንሳኤው በዓልም ታይቷል። 

በበዓሉ ዋዜማ ሦስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን መሪዎች ታሥረው የነበረ ሲሆን ሁለቱ መፈታታቸው ተነግሯል። አንደኛው ግን አሁንም አልተፈቱም። እናት ፓርቲ ይህንን መነሻ በማድረግ "መንግሥት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና አባቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚያደርገውን ማሳደድና ሕገ ወጥ" ያለውን እስር በአስቸኳይ እንዲያቆም ጠይቋል።

ሰለሞን ሙጬ 
እሸቴ በቀለ