1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲቪል ድርጅቶች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎችን አስገቡ

ሐሙስ፣ ግንቦት 8 2016

በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጥላ ሥር የሚገኙ 367 ሲቪል ድርጅቶች የሕገ መንግሥትና ሕገ መንግስታዊነት ወይም አተገባበር እንዲሁም የሀብት እና የሥልጣን ክፍፍል ዋነኛ የሀገራዊ ምክክር ጉዳዮች እንዲሆኑ ጠየቁ

https://p.dw.com/p/4fwJk
Äthiopien Nationaler Dialog
ምስል Seyoum Getu/DW

ድርጅቶቹ ለምክክር ኮሚሽን ያስረከቧቸው ሀሳቦች ምንድን ናቸው?

በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጥላ ሥር የሚገኙ 367 ሲቪል ድርጅቶች የሕገ መንግሥትና ሕገ መንግስታዊነት ወይም አተገባበር እንዲሁም የሀብት እና የሥልጣን ክፍፍል ዋነኛ የሀገራዊ ምክክር ጉዳዮች እንዲሆኑ ጠየቁ ።

ሲቪል ድርጅቶቹ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአጀንዳነት ካስረከቧቸው 11 ዐበይት ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያን ለችግር አጋልጧል ያሉት የፌዴራል ሥርዓት ዐወቃቀር እንዲሁም የግጭትና ውዝግብ መንስኤ መሆኑን የለዩት የመሬት ሥሪትና አጠቃቀም እና የዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ጉዳዮች ይገኙበታል ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እነዚህ የተመረጡ ዋና ዋና ጉዳዮች በትክክል በምክክር ሂደቱ ላይ መነሳታቸውን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት ብሎም ያንን ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል ። 

ድርጅቶቹ ለምክክር ኮሚሽን ያስረከቧቸው ሐሳቦች ምንድን ናቸው?

በሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ በልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ከተሠማሩ 367 ጥምረቶች፣ ማኅበራት እና ሲቪል ድርጅቶች በአጀንዳነት የተሰበሰቡት ዐበይት የምክክር ርእሶች ውስጥ 11ጁ ተጨምቀው የወጡም ሲሆን በርከት ያሉ ሌሎች ጉዳዮችንም በውስጣቸው በተያያዥነት ስለማካተታቸው ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የፕሮግራም እና ልማት ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ሞገስ ደምሴ እንዳሉት ሲቪል ድርጅቶች የሰፊው ማኅበረሰብ ወካይ በመሆናቸው ርእሶቹ ከብዙ ምክክር እና ውይይት በኋላ የተለዩ ናቸው።  እነዚህ ድርጅቶች የምክክር ሀሳብ አድርገው የመረጧቸውን ጉዳዮች ትናንት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽ አስረክበዋል። የግጭት መንስኤ እየሆነ ነው የተባለው የኢትዮጵያ የመሬት ሥሪት ዳግም እንዲታይ የሚጠይቀው ሀሳብም ለኮሚሽኑ መግባቱን ዶክተር ሞገስ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

"በስፋት በሀገሪቱ የተስተዋለው የሰላም እጦት ችግርም በስፋት አለ። ስሉዚህ ዘለቄታዊ የሰላም ግንባታ ጉዳይ አጀንዳ መሆን አለበት።" የአጀንዳዎቹ አሰባሰብና ጥንቅር ገለልተኛ በሆነ አካል መከናወኑንም ኃላፊ ተናግረዋል። "የተሰበሰቡት አጀንዳዎች ብቁ አማካሪ ተቀጥሮ ገለልተኛ በሆነ መንገድ ተጠናቅረዋል"

የምክክር ኮሚሽኑ አስፈላጊነት እና የእስካሁን ጥረቶች

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በሀገራዊ ምክክሩ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች የሚያበረክቱትን አስተዋፅዖ ሲያስተዋው የቆየ ሲሆን አሁን  የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በይፋ አስረክቧል። "ያነሳናቸው አጀንዳዎች በትክክል በሂደቱ ላይ መነሳታቸውን ማረጋገጠ ይኖርብናል።"

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኢትዮጵያ ውስጥ በልሂቃን መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመኖሩ ፣ በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደቱን ፈታኝ አድርጓል በሚል አስፈላጊነቱ ታምኖበት የተቋቋመ ነው። ኮሚሽኑ በትጥቅ ግጭት ውስጥ የሚገኙ  አካላት ወደ ምክክር መድረኩ እንዲገቡ ጥሪ ቢያደርግም የተሳካ አይመስልም።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ