1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaእሑድ፣ ሚያዝያ 27 2016

https://p.dw.com/p/4fWdw

 

በሀላባ ዞን በደረሰ የጎርፍ መጥለቅለቅ የአምስት ሰዎች ህይወት አለፈ።

 በዞኑ ዌራ ዲጆ ወረዳ ትናንት ቅዳሜ  የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ከሞቱት አምስት ሰዎች የሶስት ሰዎች አስክሬን መገኘቱን የዞኑን አስተዳደር ጠቅሶ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ ጽፏል። የሁለት ሰዎች አስክሬን ገና አልተገኘም፡፡ በጎርፍ አደጋው በሰዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በንብረት ላይም ጉዳት አድርሷል ነው የተባለው ። በዞኑ በተከታታይ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲወስድ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን አሳስበዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሞኑ መዲናዪቱ አዲስ አበባን ጨምሮ ለበርካታ ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ የጎርፍ አደጋዎች እየታዩ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በደረሰው የጎርፍ አደጋ አምስት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

 

በኬንያ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ግድብ በደረመሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ የሟቾች ቁጥር 228 ደረሰ።

በሀገሪቱ በቀጣዮቹ እስከ ቀጣዩ የግንቦት ወር ድረስ ይዘንባል ተብሎ የሚጠበቀው ወጀብ አዘል ኃይለኛ ዝናብ ሌላ ብርቱ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የመሬት መንሸራተት እንዳያስከትል ያሰጋል ሲል የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። ሚኒስቴሩ እንዳለው በተለይ፤ «በቆላማ ፤የተፋሰስ እና ሸለቋማ አካባቢዎች ኃይለኛ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ሊያጋጥማቸው ይችላል» ብሏል። ባለፈው እሁድ ለሰኞ አጥቢያ ወጀብ የቀላቀለ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ስምጥ ሸለቆውስጥ በምትገኝ አንዲት ከተማ አቅራቢያ የነበረ ግድብ ደርምሶ እስካሁን የ228 ሰዎች አስክሬን ሲገኝ አሁንም ድረስ በርካታ ሰዎች የት እንደደረሱ አለመታወቁን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል። በጎርፍ አደጋው 164 ሰዎች ተጎድተዋል፤ በርካታ ቤቶች ተጠራርገው ተወስደዋል፤ መንገዶች እና ድልድዮችን ጨምሮ የመሰረተ ልማቶች ላይ ብርቱ ጉዳት ደርሷል።

 

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ በደረሰ ጥቃት 15 ሰዎች ተገደሉ። ሌሎች 35 ሰዎች ደግሞ በጸና ቆሰሉ።

በስደተኞቹ መጠለያ ጣቢያ ላይ ባለፈው ዓርብ ፍንዳታ ያስከተለ ጥቃት መድረሱን የሰሜናዊ ኪቩ ባለስልጣናትን ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የኮንጎ ጦር ኃይል ቃል አቃባይ በበኩላቸው ለጥቃቱ M23 የተባለውን ታጣቂ ቡድን ተጠያቂ አድርጓል። ቃል አቃባዩ እንዳሉት የመንግስት ኃይሎች ባለፈው ዓርብ ጠዋት የአማጽያኑን የጦር መሳሪያ ማከማቻ ማውደሙን ተከትሎ አማጽያኑ በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ የብቀላ ጥቃት ፈጽመዋል። ከባለፈው የታህሳስ ወር አንስቶ በአካባቢው በመንግስት ኃይሎች እና በM2 ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለውን  ዉግያ በመሸሽ ከ250 ሺ በላይ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ኪንሻሳ M23 ታጣቂ ቡድንን በመደገፍ ርዋንዳን ስትከስ ፤በአንጻሩ ርዋንዳ ታስተባብላለች።

 

በወታደራዊ ሁንታ የሚመራው የኒጀር መንግስት አዳዲስ የሩስያ ወታደራዊ አማካሪዎች መቀበሉን የሀገሪቱ መንግስታዊ የመገናኛ ብዙኃን ዘገቡ ።

ኒጀር ከወታደራዊ አማካሪዎች በተጨማሪ ከሩስያ የተላኩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችንም ተቀብላለች። ወታደራዊ አማካሪዎቹ ኒጀርን ለቀው በሚወጡ የአሜሪካ ወታደሮች ምትክ የመጡ ናቸው ተብሏል። ሩስያ የባላንጣዋን ወታደሮች እግር ተክታ የኒጀርን ጦር እንዲያማክሩ 100 አማካሪ ወታደራዊ መኮንኖች በዚህ ወር መጀመሪያ ወደ ኒያሜይ ልካለች። ከወታደሮቹ በተጨማሪ በሶስት የወታደራዊ ቁሳቁሶች የተሞሉ የጭነት አውሮፕላኖች ኒያሜይ ደርሰዋል ነው የተባለው። የሩስያ ወታደሮች የአሜሪካ ወታደሮች ሰፍረው በሚገኙበት የኒያሜይ አውሮፕላን ማረፊያ ጎን ለጎን መስፈራቸው ማረጋገጣቸውን የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር ልሎይድ ኦስቲን ተናግረዋል።

በጎርጎርሳውያኑ ሀምሌ 2023 በ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተረከበው የኒጀር ወታደራዊ ሁንታ  በሀገሪቱ የሚገኙትን የፈረንሳይ ወታደሮችን ካባረረ በኋላ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የተደረገውን የወታደራዊ ትብብር ስምምነትም ውድቅ አድርጓል። ዋሽንግተን  እርምጃውን «በአንድ ወገን »  የተወሰደ እርምጃ ስትል ውድቅ አድርጋ ነበር ። ነገር ግን ዘግየት ብሎ አሜሪካ 1,000 የሚጠጉ ወታደሮቿን ከሃገሪቱ ለማስወጣት በቅርቡ ከስምምነት ደርሳለች። ወታደሮች ኒጀርን ለቀው በሚወጡበት ሁኔታ ላይም ንግግር እየተደረገ ነው።

 

የፍልስጥኤማውያኑ ታጣቂ ቡድን ሃማስ ከእስራኤል ጋር ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንዳለው መሪው እስማኤል ሃንያ አስታወቁ።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ በበኩላቸው  የሃማስን የተኩስ አቁም ፍላጎት ሊቀበሉ እንደማይችሉ ተናግረዋል። የሃማስ መሪ እስማኤል ሃንያ ዛሬ ካይሮ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ቡድናቸው «እስራኤል በጋዛ የምታደርሰውን ጥቃት እንድታቆም ፣ ከጋዛ እንድትወጣ እና የታጋቾች ልውውጥ ማድረግ እንዲቻል ከአጠቃላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ፍላጎታቸው ነው። ነገር ግን የታጣቂ ቡድኑ መሪ በመግለጫቸው «ግጭቱን በማስፋፋት እና በተለያዩ አሸማጋዮች የሚደረጉ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥረቶች እንዳይሰምሩ አድርገዋል» በማለት  የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔትያናሁን ከሰዋል። ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔትያናሁ በበኩላቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ መንግስታቸው «የሃማስን ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ጥሪ » አይቀበልም ብለዋል።

«የሃማስ ታጣቂዎች ከተደበቁበት ወጥተው ፤ የወታደራዊ መሰረተ ልማታቸውን እንዲጠግኑ እና ለእስራኤላውያን በድጋሚ ስጋት እንዲሆኑ አንፈቅድም » ብለዋል። ኔታንያሁ ጠንከር ባለ ንግግራቸው ለሀማስ ጥያቄ 'እጅ መስጠት' ለእስራኤል 'አሳፋሪ ሽንፈት' ነው በማለት ነበር የገለጹት። በግብጽ እና ቃጣር በሚመራው የማሸማገል ሂደት ላይ ለመገኘት የሃማሱ መሪ ካይሮ ናቸው ። በ10ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ደግሞ  የታገቱ ሰዎች እንዲመለሱ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ቴልአቪቭ ውስጥ አካሂደዋል። የእስራኤል ባለስልጣናት የጋዛውን ጦርነት ለማቆም የፍላጎት ፍንጭ አላሳዩም።

 

የእስራኤል መንግስት ዓለማቀፉን የቴሌቪዥን ጣቢያ አልጀዚራ በእስራኤል ምድር እንዳይሰራ ዘጋ።

የእስራኤል መንግስት ካቢኔ ዛሬ አልጀዚራን የሀገሪቱ «የብሔራዊ ደህንነት ስጋት» በማለት እንዲዘጋ ወስኗል።

የእስራኤል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትርም ዉሳኔው  «ወዲያው ተፈጻሚ እንዲሆን» መመሪያ ማስተላለፋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ውሳኔው  እስራኤል ውስጥ የሚገኘውን የአልጀዚራ ቢሮ እንዲዘጋ፣ የስርጭት አቅራቢ ኩባንያዎች ስርጭቱን እንዲያቋርጡ ፣እንዲሁም የቴሌቪዥን ጣቢያውን ንብረቶች እንዲወረሱ ያዛል።

ዉሳኔውን ተከትሎም የእስራኤል የሳተላይት እና የባለገመድ የስርጭት አቅራቢ ኩባንያዎች የአልጀዚራን ስርጭት አቋርጠዋል። አልጀዚራ በበኩሉ የእስራኤልን መንግስት ውሳኔ  «የወንጀል ድርጊት» በማለት ሲያጣጥል ፤ የቀረበበትን ክስ ደግሞ ጋዜጠኞችን አደጋ ላይ የሚጥል «አደገኛ እና አሳፋሪ ዉሸት» በማለት ውድቅ አድርጎታል። «የመገናኛ ብዙኃኑን አፍ ለማስያዝ» የተደረገ ሙከራ ያለውን የእስራኤልን መንግስት እርምጃ ያወገዘው አልጀዚራ ማንኛውንም ህጋዊ መንገድ ተከትሎ መብቱን እንደሚያስከብርም ገልጿል።

የቴሌቪዥን ጣቢያውን በገንዘብ የሚደግፈው የቃጣር መንግስት በእስራኤል መንግስት ዉሳኔ ላይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም። በጎርጎርሳውያኑ 1996 የተመሰረተው የአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ በእስራኤል እና ሃማስ መካከል በጋዛ ሰርጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በተለይ በንጹሃን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በቀጥታ በመዘገብ ይታወቃል።

 

ሩስያ ዛሬ ሌሊቱን በምስራቃዊ ዩክሬን ዶኔትስክ ግዛት ያስወነጨፈችው ሮኬት ሁለት ሰዎች ገድሎ በትንሹ ሌሎች ስድስት ሰዎች አቆሰለ።

የዩክሬን ጦር በበኩሉ ሩስያ ካስወነጨፈቻቸው 24 ኢራን ሰራሽ ሮኬቶች ውስጥ 23ቱን መትቶ መጣሉን አስታውቋል። በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ አንዲት ህጻን እንደምትገኝበት የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በሩስያ ጥቃቱ የመድረሱ ዜና  የተሰማው ሁለቱ ተፋላሚ ሃገራት በድምቀት በሚያከብሩት የትንሳኤ በዓል ዋዜማ ነው። ፖክሮቭስክ በተሰኘችው ከተማ በደረሰው በዚሁ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ባልተጠቀሰ መኖሪያ ቤቶች ላይም ብርት ጉዳት ደርሷል። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልዶሚር ዜሌንስኪ የትንሳኤ በዓልን አስመልከተው በቅድስት ሶፍያ ካቴድራል በተከናወነው የጸሎት ስነስረዓት ላይ መታደማቸውን በቪዲዮ ያሰራጩት መረጃ ያመለክታል። ፕሬዚዳንቱ ለወትሮ ከሚታዩበት ወታደራዊ መለዮ በተለየ ባህላዊ ልብስ ለብሰው ታይተዋል።

 

በቼክ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ፕራግ በተካሔደ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ አሸነፉ።

በሴቶች በተካሔደው 29ኛው የፕራግ ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ በዳቱ ሒርጳ ውድድሩን በ2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ

በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆናለች። ኬንያዊቷ ዶርካስ ጄፕቺርቺር ሁለተኛ ስትወጣ ኢትዮጵያውያኑ ሸዋረጌ አለነ እና ጸግነሽ መኮንን ሦስተኛ እና አራተኛ ሆነው ጨርሰዋል። በሴቶች በተካሔደው ውድድር ከሦስት እስከ ሰባት ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት አምስት ኢትዮጵያውያን በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

በወንዶች በተካሔደው ውድድር ለሚ ብርሀኑ በ2 ሰዓት ከ8 ደቂቃ ከ44 ሰከንዶች ውድድሩን በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆኗል። ኬንያውያኑ ኪፕሮሞ ኪፕኬሞይ እና ጆሹዋ ኪፕኬምቦይ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥቷል። ለሚ ብርሀኑ ባለፈው ጥር በሙምባይ በተካሔደ የማራቶን ውድድር አሸናፊ ነበር። 

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።